ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በማፈራረስና ኦሮሚያ ክልልን የመገንጠል ፖለቲካዊ ዓላማ በመያዝ፣ ዓላማውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ፡፡
በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር፣ ኅብረተሰቡን በማስፈራራትና የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ ከሚጠራው ድርጅት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉት ተከሳሾች ቶሎሳ በየነ፣ ቱሉ ሞኦ አቤቱና መገርሳ መሸሻ የሚባሉ መሆናቸውን የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ በኦነግ አማካይነት ‹‹የኦሮሞን ብሔር ከመንግሥት ጫና ለማላቀቅና ነፃ ለማውጣት መታገል አለብህ፤›› ተብሎ የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቀበል አባል መሆናቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡
ተከሳሾቹ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የንግድ ቤቶች ከኦነግ አባላት ጋር በመገናኘት፣ ድርጅቱ የሚሰጠውን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ኤርትራ መጓዛቸውንም ክሱ ያክላል፡፡ ኤርትራ አገር ከደረሱ በኋላ ኢን ተብሎ በሚጠራው ማሠልጠኛ ካምፕ፣ ከሌሎቹ የድርጅቱ አባላት ጋር በመሆን ወታደራዊ የአካል ብቃት ሥልጠና መውሰዳቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ የጦር መሣሪያ አገጣጠም፣ ዒላማ ተኩስ፣ ቦምብ አፈታት፣ አገጣጠምና አወራወር ያካተተ ወታደራዊ ሥልጠና ለተከታታይ ሦስት ወራት መውሰዳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
በቁጥጥር ሥር ካልዋሉት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክና የውኃ መስመሮችን መቁረጥ፣ የመኪና መንገዶችን በድንጋይ መዝጋትና የኦሮሞ ገበሬዎች እህል ወደ ገበያ እንዳያወጡ ለማድረግ ተልዕኮ በመቀበል፣ በተለይ ቶሎሳ በየነ የተባለው ተከሳሽ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ተብሎ 8,000 ብር ተቀብሎ ከኤርትራ በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር 2007 ዓ.ም. መግባቱንም ጠቁሟል፡፡
ተከሳሾቹ ቁጥሩን በማያሳይ ‹‹UN KNOWN›› በሚል ስልክ በመደዋወል የጦር መሣሪያ ይቀባበሉ እንደነበርና ጥይቶቹን በፍራሽ ጠቅልለው በትራንስፖርት ሲያሳልፉ እንደነበሩ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ቱሉ ሞኦ አቤቱ የተባለው ተከሳሽ ከኤርትራ ወደ ጂቡቲ ከዚያም በሚሌ አድርጐ ወደ ኮምቦልቻ ከሄደ በኋላ፣ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ነቀምት በመሄድ አንደኛ ተከሳሽ አባት ቤት ውስጥ ክላሽኒኮቭ ጠመንጃውን ከ60 ጥይቶች ጋር መደበቁን ክሱ ይገልጻል፡፡ ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር ተቀብሎት የነበረው ተልዕኮ፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ለመግደል እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ በአጠቃላይ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32(1ሀን) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ በፈጸሙት በሽብርተኛ ድርጅት ተግባር ውስጥ በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የቀረበባቸውን ክስ ለመስማት ለጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ተረኛ ችሎቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡