የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ የተስተጓጐለ ስብሰባውን በቀጣዩ ሳምንት በግብፅ ካይሮ እንደሚቀጥል ተጠቆመ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) 70ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኝበት በዚህ ሳምንት፣ በጐንዮሽ ስብሰባ የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ውይይት በሚጀምርበት ጉዳይ ላይ መነጋገራቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡
የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ለመገናኘት ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች በኒውዮርክ ያደረጉት ውይይት ቀጠሮው እንዲያጥር ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚሁ መሠረት የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴው እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 5 ቀን 2015 በካይሮ ይገናኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ስምንተኛ ዙር ጉባዔ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ተገናኝቶ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጥናት ከተመረጡት ሁለት ኩባንያዎች መካከል፣ የፈረንሣዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 5 ቀን 2015 እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቶት ነበር፡፡
ኩባንያው በተባለው ቀን ፕሮፖዛሉን ያላቀረበ ሲሆን፣ የዚህ ምክንያቱ በተባባሪ ኩባንያነት ከተመረጠው ከኔዘርላንዱ ዴልታ ሬዝ ኩባንያ ጋር ባለመግባባቱ መሆኑ ታውቋል፡፡ የተሰጠው ቀጠሮ ካበቃ በኋላ ደግሞ የኔዘርላንዱ ኩባንያ ራሱን ከጥናት ሥራው ማግለሉን በይፋ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ራሱን ባገለለበት ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት፣ በብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው የተዘጋጀው ምክረ ሐሳብ ጥናቱን በነፃነትና በጥራት ለማከናወን እንደማያስችለው መግለጹ ይታወሳል፡፡
ከዚህ መግለጫ በኋላ የግብፅ ባለሥልጣናት ቢአርኤል የተባለው የፈረንሣይ ኩባንያ ጥናቱን እንዲያካሂድ እንደማይፈልጉ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ውጥረት ውስጥ የተጠራው የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ቀጣይ ውይይት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡