Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከበቅሎ ጭነት ንግድ ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት

ከበቅሎ ጭነት ንግድ ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት

ቀን:

ተተኪ ትውልድና የዕድሜ ባለፀጐች እየተመካከሩ፣ እየተራረሙ፣ እየተደጋገፉ የሚኖሩ የቅርብ ጎረቤቶች ናቸው፡፡ አረጋውያን በዘመን የካበተ በጥበብ፣ በማስተዋልና በክህሎት የታነፀ ዕውቀታቸውን ለትውልድ ሳያስተላልፉና እንደእነሱ ተምሳሌት የሚሆን ትውልድ ሳይተኩ እንደዋዛ እንዳያልፉ፣ ትውልዱ ቅርስና ተምሳሌት አልባ ሆኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ መደረግና የዕውቀት ሽግግር መኖር አለበት፡፡

የዕውቀት ሽግግር ሊኖር የሚችለው ተተኪ ትውልድንና አረጋውያንን የሚያገናኝ ድልድይ ሲሠራ ነው፡፡ ለዚህም በትውልዱና በአረጋውያን መካከል የዕውቀት፣ የልምድ፣ የጥበብ ቅብብሎሽና ትስስር እንዲኖር መድረክ መፍጠር አንዱ መፍትሔ ነው፡፡

የተተኪ ትውልድና የዕድሜ ባለፀጐችን የዕውቀት ትስስር ለማጠናከር ‹‹የአረጋውያን የሕይወት ተሞክሮ›› በሚል ርዕስ አሳታፊ የሆነ የውይይት መድረክ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተካሂዷል፡፡ በግዮን ሆቴል በተከናወነው በዚሁ የውይይት መድረክ፤ የ73 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ወልደሔር ይዘንጋው፣ የሕይወት ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡ በዕለቱ ለተገኘው ታዳሚ ካካፈሉት ተሞክሮአቸው መካከል ስኬታማ የንግድ ሥራቸውና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ይገኙበታል፡፡

አቶ ወልደሔር፣ በሰሜን ምሥራቅ ጎጃም ልዩ ስሙ ፈረስ ሜዳ በሚባል የገጠር ከተማ ጥር 5 ቀን 1935 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ዳዊት ደገሙ፡፡ ከዚያም ድቁና ተሰጥቷቸው በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት አድባራት ማገልገልን ተያያዙት፡፡ በዘመናዊ ትምህርትም 12ኛ ክፍል ማጠናቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡

በ13 ዓመታቸው በአካባቢያቸው የተቋቋመውን የውሀ ወፍጮና ሠራተኞችን የማስተዳደር ሥራ በኃላፊነት መምራት ጀመሩ፡፡ ይህ ዓይነቱንም ሥራ ትተው ከአባታቸው ጋር ድቦ በምትባል የገጠር ከተማ በሽርክና ንግድ ጀመሩ፡፡ በአንድ የኮርቻ በቅሎ ጭነት በመጫን ለብዙ ጊዜ ከነገዱ በኋላ ሌላ በቅሎ ተበድረው ይገዛሉ፡፡ እህል እየሸመቱ በበቅሎዎች ጭነው ደጀን ድረስ እየሄዱ መነገዱን በስፋት ተያያዙት፡፡

ንግዱም እየቀናቸው እሳቸውም እየጐረመሱ መምጣታቸውን የተመለከቱት አባታቸው፣ 18 ዓመት ሲሆናቸው ዳሯቸው፡፡ የያዙት ንግድ እየተስፋፋ በመሄዱ በአንድ ሰው አቅም ለማስተዳደር አስቸጋሪ እየሆነ መጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ወንድሞቻቸውን በሽርክና አስገብተው መሥራት ጀመሩ፡፡

እንደ አቶ ወልደሔር ገለጻ፣ በ1966 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከአንድ አርመናዊ ጋር የባቄላ ንግድ ያካሂዱ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አንድ ኩንታል ባቄላ ስምንት ብር ሲሆን፣ ቦሎቄ ደግሞ 200 ብር ነበር፡፡ የቦሎቄው ውድነት አነሳስቷቸው ወደ ሶደሬ መንገድ በመሄድ 70 ኪሎ ግራም ቦሎቄ ገዝተው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ይወስዳሉ፡፡ እዚያም እንደደረሰ አርሶ አደሮቹ ለሙከራ ያህል እንዲዘሩት ማግባባት ጀመሩ፡፡ አርሶ አደሮቹ በአካባቢያቸው ቦሎቄ ያልተለመደና የማይታወቅ በመሆኑ ለጊዜው ግር አላቸው፡፡ ከብዙ ጥረትና ግፊት በኋላ አርሶ አደሮቹ ቦሎቄውን ወስደው ዘሩት፡፡ በዚህም ጥሩ ምርትና ገቢ ተገኘ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የቦሎቄ አምራች አካባቢ ለመሆን በቅቷል፡፡

ደርግ ሲመጣ የሶሻሊዝምን ሥርዓት በአገሪቱ ላይ አወጀ፡፡ የሚከተለውም የንግድ ሥርዓት በማዕከላዊ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገለጸ፡፡ በወቅቱ የግል ባለሀብቱና ነጋዴው በጠላትነት ሲታዩ፣ በተለይም ነጋዴው የችግር ምንጭ ተደርጎ ተፈረጀ፡፡ በመሆኑም የምርቶችና የሸቀጦች ሥርጭት በሙሉ በሕዝባዊ ተቋማት ሥር ሆኑ፡፡ ደርግ አዲሱን ሕግ እንዳወጣ አቶ ወልደሔር ገጠር ሄደው ከስምንት ሕዝባዊ ድርጅቶች የውክልና ደብዳቤ አገኙ፡፡

እነዚህን የውክልና ደብዳቤዎች ሰብስበው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አዲስ የሥራ መስክ ይከፍታሉ፡፡ የፍጆታ ዕቃዎች ባሉባቸው የመንግሥት ማከፋፈያ ድርጅቶች እየተዟዟሩ የውክልና ደብዳቤውን በማሳየት፣ ሸቀጥ አውጥቶ መሸጥን መደበኛ ሥራቸው አደረጉ፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ ወደ አምራች የንግድ ዘርፍ ተሰማሩ፡፡

በደርግ ዘመን በመንግሥት ባለቤትነት ይተዳደር የነበረ አንድ የጣሊያን የሰም ፋብሪካ ለግለሰብ ለማከራየት ጨረታ ይወጣል፡፡ አንድ ሰው ተሳትፎ የጨረታው አሸናፊ ይሆናል፡፡ ሰውዬው ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ስላልነበረው አቶ ወልደሔር በሽርክና ፋብሪካውን ማንቀሳቀስ ይጀምራሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር የኪራይ ውል በስሙ የተፈራረመው ሸሪካቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ ባህሪ እያሳየ ይመጣል፡፡ አቶ ወልደሔር በሽርክና ተስማምተው ሥራ ሲጀምሩ ተማምነው እንጂ ምንም ፊርማ አልነበራቸውም፡፡ ሰውዬው ግን ይህንን ክፍተት እንደ ትልቅ ደካማ ጎን በመቁጠር በሥራ ላይ ተደጋጋሚ ችግር መፍጠር ይጀምራል፡፡

ሁኔታዎች በዚህ ላይ እንዳሉ ድርቅ ተከሰተ፣ ንቦቹም የሚሰጡት የማር ምርት እየተዳከመ መጣ፡፡ ይህም ሁኔታ የሰም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ ፋብሪካው ተዳከመ፡፡ አቶ ወልደሔር ግን መርካቶ አካባቢ አንድ ሱቅ በመግዛት የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች መሸጫ ይከፍታሉ፡፡ ከዚህም ጐን ለጐን ሌላ ነገር መፍጠር ግድ ሆነባቸውና በፖራፊን ዋክስ ጧፍ ማምረት ጀመሩ፡፡

በመካከሉ ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን መቆጣርና መምራት ጀመረ፡፡ በማዕከላዊነት ይመራ የነበረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ ለነፃ ገበያ ቦታውን ለቀቀ፡፡ በገበያ ሕግጋት የሚመራ ኢኮኖሚ ተደነገገ፡፡ ስለሆነም የቤተሰባቸው አባላት የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑበትን አምስት ኩባንያዎችን አቋቋሙ፡፡ ኩባንያዎቹ  ግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ግዮን ኢንዱስትሪያል ኬሚካል፣ ግዮን ጋዝ፣ ኮምፓልሳቶ፣ ምሥራቅ ዳቦ፣ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ስቲከር፣ ካርቶንና እንደ መድሃኒት የመሳሰሉ የተለያዩ ነገሮች ፓክ የሚያደርጉ ፋብሪካዎችን በገላን ከተማ አቋቁመዋል፡፡ እነዚህም ሦስት ፋብሪካዎች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር ሰምና ቡና ፕሮሰስ አድርጎ ወደ ባህር ማዶ መላክ፣ ትራንስፖርት፣ ወዘተ. አቋቁመው እንቅስቃሴውን ውጤታማ በሆነ መንገድ በስፋት ተያያዙት፡፡ የኬሚካሉ ፋብሪካ ደግሞ ከሚያመርታቸው መካከል ውሀ የሚያክም ኪኒን (ውሀ አጋር) እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቀድሞውና በአሁኑ ሥርዓቶች በውጭ ንግድ ዘርፍ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በቀደመው ሥርዓት ፋብሪካ ሲያቋቁሙ ከልማት ባንክ 80 ሚሊዮን ብር እንደተበደሩ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ታማኝ ተበዳሪ እንደሆኑና የተበደሩትንም በወቅቱ እንደሚመልሱ ተናግረዋል፡፡

ተወልደው ባደጉበትም አካባቢ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ (መሰናዶ) ትምህርት ቤት አቋቁመዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ የተወሰኑ ዓይነ ሥውራን ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍም ያደርጋሉ፡፡ በጊዜ ብዛት አርጅታ ልትፈራርስ የተቃረበችውንና በዩኔስኮ የተመዘገበችውን የመርጦ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ቆርቆሮ በማልበስና ተጠብቃ እንድትቆይ በማድረግ ትልቅ ቅርስ የማዳን ሥራም አከናውነዋል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኩዌት፣ ኮሪያ፣ ጃፓንና ጣሊያንን ሲጐበኙ ካስከተሏቸው አሥር ቀዳሚ ላኪዎች መካከል አቶ ወልደሔር ይገኙበታል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጉብኝት ላይ በየአገሮቹ ካሉት ገዥዎችና ላኪዎች ጋር የፊት ለፊትና የጋራ ውይይት በማድረግ ጥሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና ጠቃሚ ዕውቀትም ለመቅሰም እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበርን፣ ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ከመንግሥት ተቋማትና ከሌሎችም አካላት ጋር በመቀናጀት ለአራተኛ ጊዜ ባካሄዱት በዚሁ የውይይት መድረክ፣ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የግል ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...