ሠዓሊ ፍቃዱ አያሌው የተወለደው አዊ ዞን ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤት በገባበት ዕለት የሳለውን ዛፍ ዛሬ ድረስ ያስታውሳል፡፡ አድናቆት ያስገኘለት ሥዕል ነበር፡፡ ከዛ በኋላ አብዛኛውን ጊዜውን በመሳል ያሳልፍ ጀመር፡፡ ሥዕል በጣም ቢወድም እንዴት በሙያው ሠዓሊ እንደሚሆን አያውቅም ነበር፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራ፡፡ በውትድርናው ዓለምም ከሥነ ጥበብ ሳይለያይ፣ በሚያገኘው ክፍት ጊዜ ያገኘውን ቁሳቁስ ተጠቅሞ ሥዕል፣ ቅርጽም ይሠራ ነበር፡፡
በ1993 ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥቶ ሳለ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የሚያስተምር ወንድሙ፣ ትምህርት ቤቱን ካስጐበኘው በኋላ የሕይወቱ መስመር ተቀየረ፡፡ ‹‹የኔ ቦታ ይኼ ነው ብዬ ወደ መከላከያ ሠራዊት ሳልመለስ ቀረሁ፤›› ይላል፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ከአራት ዓመት ጥረት በኋላ ትምህርት ቤቱ ተቀብሎት የማዕረግ ተመራቂ ለመሆን በቃ፡፡
ረዘም ላለ ጊዜ በሥዕል፣ በሞዛይክ ይመራመር ነበር፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርትም ሰጥቷል፡፡ ከምርምር ባለፈ ሙሉ በሙሉ ለመሥራት ባኮበኮበበት ወቅት ግን ያልጠበቀው መሰናክል ተከሰተ፡፡ በ2004 ዓ.ም. አካባቢ እጆቹ እንደልቡ አልንቀሳቀስ አሉ፡፡ ከጊዜ በኋላ ቀኝ እጁ ፈጽሞ አልሠራ አለው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ጤናው እንደሚመለስ ቢነግሩትም የሰውነቱ ሁኔታ ተባባሰ፡፡ ‹‹በእጄ መሳል ባልችል ዕውቀቴን በማስተማር አስተላልፋለሁ፤›› ብሎ ሲነሳ፣ ይባስ ብሎ ድምፁ ተዘጋ፡፡ በሽታው ስሪንጆማልያ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በአገር ውስጥ በውጪ ቀዶ ጥገና ቢደረግለትም አቋሙ ሊመለስ አልቻለም፡፡
አሁን ሠዓሊው ከቤት ውሏል፡፡ ሰውነቱ እንደ ልቡ ባይንቀሳቀስለትም እንደምንም እየተፍጨረጨረ ብሩሽና ሸራውን ከማገናኘት አልቦዘነም፡፡ እጁ ላይ ብሩሽ ታስሮለት፣ ቀለም ተዘጋጅቶለት፣ ሸራ ተወጥሮለት ይስላል፡፡ ረዥም ሰዓት መሳልና ያሻውን ያህል የጠለቀ ሥራ ሸራው ላይ ለማስፈር ግን ይቸገራል፡፡ ‹‹የአቅሜን ያህል እየተንቀሳቀስኩ ነው፤›› የሚለው ሠዓሊው፣ ያለበት የጤና ሁኔታና የሥዕል ፍላጐቱ ባለመመጣጠኑ ያዝናል፡፡ ቀድሞ ሥዕልን ለስሜቱ ቢሠራም፣ አሁን መታከሚያ ገንዘብ ማግኘትንም ከግምት ያስገባል፡፡
ሕይወት ባልጠበቀው ጐዳና ቢወስደውም፣ ‹‹ካልሳልኩ፣ ስለሥነ ጥበብ ካላነበብኩ ያመኛል፤›› በማለት፣ ጥበብ ለእሱ ያለውን ትልቅ ቦታ ይገልጻል፡፡ የሰው ልጆች ከተሰጣቸው ሀብት ትልቁ ጥበብ እንደሆነ የሚያምነው ሠዓሊ ፍቃዱ፣ ያሻውን ዓይነት ጥበባዊ ሥራ በነፃነት የሚሠራበትን ቀን በተስፋ ይጠባበቃል፡፡ ባለበት ፈታኝ ወቅት አንዳች እፎይታ የሚለግሰውም ሥነ ጥበብ ነው፡፡
እንደ ሠዓሊው ሁሉ ድንገት በደረሰ ጉዳት አልያም ከልጅነት አንስቶ ባለ የአካል ጉዳት የሚፈተኑ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ይሁን ውጪ በተመሳሳይ ሁኔታ በሥነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማንነታቸውን፣ ታሪካቸውንና አመለካከታቸውን የሚገልጹበት ሥነ ጥበብ እፎይታቸውም ነው ለማለት ይቻላል፡፡
አካል ጉዳተኛ ሆኖ ሥነ ጥበባዊ ሥራ መሥራት ቢቻልም፣ የኅብረተሰቡ አመለካከት ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ የሚናገረው ሠዓሊ ተስፋዬ በቀለ ነው፡፡ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የሚያስተምረው ተስፋዬ፣ ለአካል ጉዳተኛነቱ ቦታ ባይሰጠውም፣ በኅብረተሰቡ የተዛባ አመለካከት ሳቢያ የገጠመውን አካፍሎናል፡፡
በሥነ ጥበብ የተሳበው በልጅነቱ ቢሆንም ከመሳል ባለፈ ሕይወቱን እንዴት በሥነ ጥበብ ማሳለፍ እንደሚችል አያውቅም ነበር፡፡ በጉራጌ ክልል አጨበር አካባቢ የተወለደው ሠዓሊው፣ የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ነበር ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና የመጣው፡፡ ሶኬሎሲስ በተባለ የአጥንት ሕመም ሳቢያ ራሱን ችሎ መቆም አይችልም ነበር፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች በክራንች ድጋፍ መንቀሳቀስ ካስለመዱት በኋላ መርካቶ አካባቢ ከሚኖሩት አያቱ ቤት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡
ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አካውንቲንግ ለመማር ቢሄድም አልዘለቀበትም፡፡ ጥሪው ጥበብ ነበርና ወደ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት አመራ፡፡ ራሱን ለመግለጽ ሁነኛ መንገድ ሆኖ ያገኘውን ሥነ ጥበብ ሲማር፣ አካል ጉዳተኛነቱ አንዳችም ቦታ እንዳልነበረው ይናገራል፡፡ ‹‹በሌላ ቦታ አይቻሉም የተባሉ ነገሮች በሥነ ጥበብ ተችለው አይቻለሁ፤›› ይላል፡፡
በትምህርት ቤቱ በመምህርነት እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቦለት ለመምህርነት ሲዘጋጅ ከሚያስፈልጉት አንዱ የጤና ምርመራ ማድረግ ነበር፡፡ ሕክምና ባደረገበት ወቅት የገጠመውንም አይረሳውም፡፡ የሕክምና ባለሙያው ሳይመረምረው፣ ‹‹እንዴት መቆምና መሥራት ትችላለህ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ አካል ጉዳተኛነትና መሥራት አለመቻልን አያይዞ አስቦ የማያውቀው ሠዓሊው ግራ ተጋባ፡፡ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንደሚችል እየተነገረው ያደገው ሠዓሊው፣ ከባለሙያው ጋር ይጋጫል፡፡ በስተመጨረሻ ይቅርታ ጠይቆት ሕክምናው ቢቀጥልም የኅብረተሰቡን አመለካከት ያየበት ቅጽበት ነበር፡፡
ተስፋዬ ቤተክርስቲያን ሲገባ የኔቢጤ መስሏቸው ገንዘብ የሰጡት ሰዎች አሉ፡፡ ስለሥራዎቹ ሰምተው ወይም በተለያየ አጋጣሚ አግኝተውት አብረውት ለመሥራት የፈለጉ ግለሰቦች አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ብቻ ‹‹አይችል ይሆን?›› ብለውታል፡፡ ዐውደ ርዕይ ያካሄደባቸው ትልልቅ ሆቴሎች በር ላይ ወደ ውስጥ እንዳይዘልቅ ተከልክሎ እሰጣ ገባ ውስጥ የገባበትን ጊዜም ያስታውሳል፡፡
‹‹ጥበብ እፎይታዬ ነው፤›› የሚለው ሠዓሊው፣ ሥዕል፣ ፐርፎርማንስ ወይም ሌላ ዓይነት ጥበብ በግል የሚሠራ መሆኑ ነገሮችን እንዳቀለለት ያምናል፡፡ ለሥራዎቹ መነሻ ከሆኑት አንዱ የሰውነቱ ሁኔታ ነው፡፡ እንደ ተፈጥሮና የሰው ልጅ ያሉ ሕይወት ያላቸው አካላትን ሕይወት ከሌላቸው ጋር በማነጻጸር ይሠራል፡፡ በቅርቡ ከራሱ በመነሳት በጀርባ አጥንት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡
አካል ጉዳተኞች ጉዳታቸውን ያላግባብ የሚጠቀሙበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል፡፡ በሁሉም ነገር ዕርዳታ የሚሹ ሆነው መቅረብ እንደሌለባቸው፣ ኅብረተሰቡም እንደ ተረጂ ማየት እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ የተስፋዬን ሐሳብ የምትጋራው ሠዓሊት ዓለም ገዛኸኝ ነች፡፡
ዓለም የ12 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር የነርቭ ችግር የገጠማት፡፡ የምትንቀሳቀሰው በዊልቸር ነው፡፡ ከደረሰባት የአካል ጉዳት በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ቤት ውስጥ ስለነበረች አብዛኛውን ጊዜ በመሳልና በማንበብ ታሳልፍ ነበር፡፡ ሥራዎቿን ያዩ ግለሰቦች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር ከጣሊያን ከመጡ አርቲስቶች ጋር አገናኟት፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርት ይሰጡ ከነበሩት አርቲስቶች ጋር ሆና ለሦስት ዓመት ተማረች፡፡ እንደጨረሰችም እዛው የመሥራት ዕድል ገጠማት፡፡ ለተማሪዎች ሥልጠና በመስጠት ለተወሰኑ ዓመታት ከቆየች በኋላ የራሷን ጋለሪ ከፈተች፡፡
በጋለሪው የራሷና የሌሎችም ሥዕል ለእይታና ለሽያጭ ከመቅረባቸው ጐን ለጐን፣ ወደ 100 ለሚሆኑ ልጆች የሥዕል ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ የጥበብ ሰው የተለያየ ችግር ቢገጥመውም፣ የአካል ጉዳት ሲደርስበት ችግሩ የተጠላለፈ ይሆናል፤›› ትላለች ሠዓሊቷ፡፡ ለአካል ጉዳተኞች መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ እየተኖረ የፈጠራ ሰዎች ከኅብረተሰቡ ድጋፍ ያገኛሉ ብሎ ማሰብ ከባድ እንደሆነ ታክላለች፡፡
እሷ እንደምትለው፣ አካል ጉዳተኞች ለአንድ ቦታ ይመጥናሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ዕድል አይሰጣቸውም፡፡ ሆኖም እንደ ማንኛውም ሰው ለአካባቢያቸው እንደሚጠቅሙ መታየት አለበት፡፡ ያለው አመለካከት እንዲቀየርም ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የደረሰብኝን ጉዳት ሳይሆን ማድረግ የምችለውን እያሰብኩ በኑሮዬ እደሰታለሁ፤›› የምትለው ዓለም፣ አካል ጉዳት ባይሆንም የተለያዩ ሁነቶች የሰው ልጅን ስለሚፈታተኑ በተለየ መታየት አይገባውም ትላለች፡፡
‹‹ሥነ ጥበብ ሕይወት የሚታይበትና የሚገለጥበት ነው፤›› የምትለው ዓለም፣ አካል ጉዳተኛ መሆኗ አዎንታዊም አሉታዊም ጎኖች እንዳሉት ታምናለች፡፡ በአንድ በኩል ሁኔታዎች አስገድደዋትም ቢሆን አንድ ቦታ ሆና ጊዜዋን ወስዳ በመሥራቷ አዎንታዊ ጐኑን ታየዋለች፡፡ አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላትና በሚያስፈልገው ጊዜ ሰዎችን ለማግኘት፣ ሥራዎቿን ለመሸጥም የምትቸገርባቸው ጊዜዎችን ትጠቅሳለች፡፡
ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ እንደ አብዛኞቹ ሠዓሊዎች ወደ ሥነ ጥበብ የገባው በልጅነቱ ነው፡፡ እንደ መነሻ የሚጠቅሰው እናቱ ከውጭ ሀገር ሲመጡ ባመጡት የጭቃ ቀለም መማረኩን ነው፡፡ በወቅቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ምስል እያየ ሲስል የተመለከቱት አባቱ፣ በሥዕል እንዲገፋ ያበረታቱት ጀመር፡፡ የአባቱ ድጋፍ ዘወትር አዳዲስ ነገር እንዲፈጥር አቅም ይሰጠው ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱም በየክፍሉ እንዲስል ይጠየቅ ነበር፡፡ የ12 ዓመት ልጅ እያለ በአንኪሎሲንግ ስፓንዲሊቲስ ሳቢያ ሰውነቱን ማንቀሳቀስ ይከብደው ጀመር፡፡ ከዓመታት በኋላ ሰውነቱ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ አቁሞ ቤት ዋለ፡፡
ለዘጠኝ ዓመታት ያህል አልጋ ላይ ሆኖ ራሱን ከሌሎች ጋር እያነጻጸረ ያዝን ነበር፡፡ ዋጋ እንደሌለው ያስብ ስለነበር ዘወትር ሞቱን ይመኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ፀበል ለመጠመቅ ወደ ቤተክርስቲያን አምርቶ በጽሞና ከራሱ ጋር የሚነጋገርበት ጊዜ አገኘ፡፡ ቀስ በቀስ ተስፋ የቆረጠው ልቡ እየተነሳሳ ወደ ሥነ ጥበብ ተመለሰ፡፡ ሰውነቱን ማንቀሳቀስ ስለማይችል አልጋ ላይ በሆዱ ተኝቶ መሳል ጀመረ፡፡
ሥራዎቹ ያተኮሩት በግል ሕይወቱ ላይ ሲሆን፣ ያለበትን ሁኔታ፣ የማንነት ጥያቄውን፣ ህልሙን፣ ለውጡንና አመለካከቱን በሥነ ጥበብ መግለጽ ጀመረ፡፡ ‹‹ወደ ራሴ ስመለስ በውስጤ ያለው ስሜት ወጣ፤›› ይላል ብሩክ፡፡ ቀጥሎ ዐውደ ርዕዮች ማዘጋጀት እንደጀመረና በሕይወቱ የገጠመውን ውጣ ውረድ በሥነ ጥበብ ማለፉን ይናገራል፡፡
ባለፈው ዓመት በተደረገለት ቀዶ ጥገና በከፊል መቀመጥና በድጋፍ መሄድ ችሏል፡፡ መንቀሳቀሱ ሥዕል በነፃነት እንዲሠራ አስችሎታል፡፡ ‹‹ሥዕል ህመሜንና መከራዬን የምረሳበት ነው፤›› ይላል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ሠዓሊያን ጋር የሚስማማበት ጉዳይ ሥነ ጥበብ የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ በሆነበት ማኅበረሰብ፣ አካል ጉዳተኛነት ሲጨመርበት የበለጠ እንደሚያስቸግር ነው፡፡ አንዳንድ ሥራዎች በአካል ጉዳተኛ ስለተሠሩ ብቻ አድናቆት ሲቸራቸው ይታያል፡፡ ሠዓሊውን ከሥራው ለይቶ መፈረጅ እንጂ በአካሉ ሁኔታ መገመት ተገቢ አይደለም ይላል፡፡