Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቱን አስገብተን የቱን እናስወጣ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹ንፋስ ሲነሳ እሳት አይጫርም›› ይሉን ተማምኘ በባሻዬ ደጅ ሳልፍ ‹‹ደህና አምሽተዋል?›› ብላቸው፣ ‹‹የሌባው ሲገርመን የንፋሱ ባሰን›› አሉኝ። እኔ ደግሞ ነገር አይገባኝ። ቢገባኝ ይኼኔ ስንት ፎቅ በስሜ አቁሜ ነበር። የአቋቋሙ ‘ፓስወርድ’ አልገባን ብሎ አንጂ እውነት ማን ነው አሁን ጉርሻ ላይ እንደሚግደረደረው፣ ‘ጡብ ደርድረህ ኪራይ ሰብስብ’ ቢሉት እንቢ የሚለው? ኧረ ተውኝ! ይልቅ ባሻዬ እንዴት ያለ የአዛምድ ‘ኮርስ’ ቢወስዱ ነው ንፋስና ሌባን ያገናኙዋቸው ብዬ፣ ‹‹የምን ሌባ?›› ብዬ ስጠይቃቸው፣ ‹‹አልሰማህም እንዴ! የኮሎኔል (የቀድሞ ናቸው ደግሞ) እከሌን ቤት የውኃ ቆጣሪ ነቅለው ሊሰወሩ ሲሉ እኮ ነው እጅ ከፍንጅ አፈፍ የተደረጉት፤›› ብለው በቁማቸው ከጠመጠሙት ብርድ ልብስ ሌላ የወሬ ሙቀት መፍጠር ጀመሩ። ‹‹እነማ?›› ብዬ እኔም የነሁላላ ጥያቄ መጠየቅ። ‹‹ሌባ ደግሞ ምን ስም አለው? ያው ሌባ ነው፤›› ብለው ጥቂት አሰቡና ‹‹ለነገሩ ዘንድሮ የክርስትና ስማቸውን እየጠራን ካልሆነ በደቦ ስም መጠቅለሉ አላዋጣም፤›› ሲሉ እንደ ፀሐይ ግርዶሽ በስንት ጊዜ አንዴ የሚያስሉት የትንታ ሳል ተከሰተ። ሳላቸው እንዳይባባስ ትንፋሼን ዋጥ።

በረቀቀ ዘዴ ዶላር እየዋጡ በሆድ ዕቃቸው የሚያዘዋውሩ እያሉላችሁ፣ የእኔ ትንፋሽ አዋዋጥ ምን ይደንቃል እስኪ አሁን? ባሻዬ ጋብ ሲልላቸው፣ ‹‹እንዲያው ካልጠፋ ነገር የውኃ ቆጣሪ ይሰረቃል?›› ብላቸው፣ ‹‹አንተ ደግሞ ውኃ ሳይኖር ቆጣሪ ምን ይሠራል?’ ብለው ይሆናላ፤›› ሲሉኝ ተራውን እኔኑ ትን አለኝ። ‹‹ውኃ ይገደባል እንጂ ይቆጠራል እንዴ?’ የሚል ጥያቄ እንዳላዘጋጀሁ በውስጤ ተኖ ቀረ። የዘነበ እንደሁ አንድ ቀን ፀበል ትቀዱ ይሆናል ብዬ እኔም እንደረሳሁት ቀረሁ። መርሳት ያቃተን ቀን ግን እንዴት ልንሆን ነው? ብዬ ማሰብ ጀመርኩና ተውኩት፡፡ ስንቱ ቃል የተገባ ነገር ተረስቶና አስታዋሽ አጥቶ የእኛ እንዴት? እንዴት? ማለት ምን ይፈይዳል?

አንዳንዴ ግሪ የሚያጋባ ምሳሌ ሲገጥማችሁ ምን ትላላችሁ? አንዴ ‘እንዴት ተባለ?’ ብዬ ብጠይቅ የሚነግረኝ ሰው አጣሁ። ልፋ ብሎኝ እንጂ የዛሬ ዘመን ሰው እንኳን ተረትና ምሳሌ ታሪክ የተመሠረተበትን ጥንተ ነገር ሊነግረኝ፣ አጥንቱ ድረስ የሚሰማውን ስሜቱን በቅጡ አፍታቶ መናገር እንደተሳነው ማስታወስ ነበረብኝ። እንዳልኳችሁ ታዲያ ብዙ ነገር ይረሳል። እንኳን በሽታ የመድኃኒት ሰዓትም እንረሳለን እኮ እኛ። ብዬ ብዬ ሲደክመኝ ታዲያ ወዲያ ወዲህ ተንገላውጄ ደከመኝና ለሻይ ለቡና አረፍ ወደምልባት ካፌ ጎራ አልኩ። በምናብ የመመነን መብቴን ለመጠቀም። ይገርማችኋል አንዳንዴ ሕገ መንግሥታችን ያፀናልልን መብቶች የትም ድረስ ገፍተን ለመጠቀም ሳንሞክር ‘ፌስቡክ’ የመጠቀም ነፃነቴን ገደበው ብለን ‘ኔትወርኩን’ የምንራገም ሰዎች ነገር ያሳስበኛል። ይኼም ታዲያ የማሰብ መብቴ ነው፣ እንዳትጋፉኝ። ከግፊያ ነው እንዴ ተጠፍጥፈን የተሠራነው? አያስብልም አንዳንዴ?

እና አንድ ጎተራው የሞላለት እህል የበረከተለት ገበሬ ነበር። የእህሉ ጎተራ ብቻ ሳይሆን ጥበብ ሞልታ የተረፈችውም ነው። መቼም ጥበብ በሕይወት ተሞክሮ ጭምር እንጂ በቀለም ብዛት ብቻ አትገኝም። ‹‹የምትገኝ እየመሰላቸው ግን ቀንድ የሚያስበቅሉ ቀንዳሞች የሚያስቀምጡም አልሆነ ዘንድሮ፤›› ይላሉ ባሻዬ አዘውትረው ስለጥበብ ሲሰብኩ። አሁን አካሄዴ እንዳይበላሽብኝ የባሻዬን ስብከት ለባሻዬ እተወዋለሁ። መተውን የመሰለ ነገር ምን አለ? እ? እናም ጠቢቡ ገበሬ ሞልቶ ከፈሰሰው የእህል ጎተራው ወረቱን መድቦ፣ ድርቅ ቢከሰት ቤተሰቡ እንዳይራብ የሚቀብረውን ቀብሮ፣ የተረፈውን ገበያ ሊያወጣው ያስባል። ሊሸጠው ያሰበው እህል ብዙ ነበርና ያሉት አህዮች አልበቁትም። የሀብቱን ቅጥ ማጣትና የእህሉን መትረፍረፍ ያየ ሰነፍ ጎረቤቱ ‘እህም!’ ይልና ባለፀጋው ለጭነት የሚሆኑ ተጨማሪ አህዮች ሊለምን ወንዝ ተሻግሮ ባደረበት ሌት እህሉን በታታሪው ገበሬ አህዮች ጭኖ ገበያ ሲያወጣው ተይዞ፣ ‹‹የማን እህል ነው?›› ቢሉት ደንግጦ ‹‹የአህያ ለማኙ!›› — ‹‹እንዴት ጫንከው?›› ይሉታል ‹‹አህዮቹን አባብዬ!›› እንዲያው ፍረዱማ በአገራችን ዱላ እንጂ ሽንገላ አህያን ይገዛል?! ኦ! ለካ ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል›› ተብለናል!

ጨዋታን ጨዋታ ያመጣው አይደል? መብራት ነው በጩኸትም በጨዋታም የማይመጣው። አትሉም? ለማንኛውም ሁሉም በጊዜው ይመጣል። ‹‹በመንገድ ሥሪት ጣልቃ አትግቡ›› ይላሉ መንገዱን የተመላለሱበት። ‹‹እንዴት?›› ሲባሉ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ’ የሚለውን መጽሐፍ አንብብ፤›› ብለዋችሁ ይቀየሳሉ። ሰውም እንደ መንገድ ባገኘው አጋጣሚና አቅጣጫ የሚቀየስ ሆኗላ። ታዲያ ሰሞኑን ከአንድ ደላላ ወዳጄ ጋር ተደራጅተን ሦስት ያገለገሉ ‘ስካኒያ’ ተሳቢዎች ልናሻሽጥ ወዲያ ወዲህ ስንል ነበር። እንደ ዝንጀሮ ከአንዱ ግንድ ወደ ሌላው አንዘል ነገር እንኳን በዝላዩ በሩጫውም ውጤታችን እያሽቆለቆለ ነው። እንደ አገር ሳይሆን እንደ ግለሰብ ነው የማወራው። በአገሬ የዝላይ ውጤት አንድም ሰው እንዳይመጣብኝ የቀረኝ ነገር ቢኖር ‘አትምጡብኝ’ የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቲሸርት መልበስ ነው። በነገራችን ላይ ቲሸርቱ ማሠራቱን አስቤበት ብሩኋ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹መንታ ትርጉም ደረትህ ላይ ለጥፈህ ስትዞር መንታ ጥፊ አይቀርልህም፤›› ብላ አስተወችኝ። ‘መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል’ ብላ ስትቀጥል ‘ስለቲሸርት ነው ያወራኋት ስለመደብ ትግል?’ እያልኩ ዞረብኝ። ‘ኤኒ ዌይ!’ ያለው የባሻዬ ልጅ ነው ለካ?

‘ሃይ ዌይውን’ እርሱትና ጨዋታዬን ልቀጥል። ከወዳጄ ጋር ብዙ ቦታ መዟዟር ነበረብን። ታክሲ ጠፋ። ‹‹ባቡር የጀመረው ታክሲ እንዳይጠፋ አልነበር እንዴ?›› አለኝ። ‹‹እኔ ደላላ ነኝ እንጂ ሕዝብ ግንኙነት ነኝ?‹‹ በሸቅኩኝ። ደርሶ ለምን ሽቅብ ሽቅብ እንደሚለን የሚነገርን የለም ግን እናንተ? ‹‹ምን ያናድድሃል?›› ጠየቀኝ። በመናደዴ እየተናደድኩ ሳለሁ ንዴቴን ልብ እንዳለው በማየቴ የበለጠ ተናድጄ ‹‹የቀላል ባቡር ሥራው እኮ አላለቀም። ገና በሌሎች አካባቢዎች ሐዲድ የማንጠፍ ሥራው ይቀጥላል፤›› ብዬ ታጠፍኩበት። ካልተጣጠፍን ተራራው የሚገፋ ነው? ልከኛ ጥያቄ ነው!

ኋላ አስበን አስበን ባቡር ተሳፈርን። ወዳጄ፣ ‹‹በፊልም እንዳየሁት ልሁን። ወግ ይድረሰኝ፤›› ብሎ ከመሳፈራችን በፊት ከአዟሪ ጋዜጣ ገዝቷል። ሸብልሎ ብብቱ ውስጥ እንደያዘው ቀረ እንጂ። ‹‹አይ ሞኙ! ተበላሁ ብሬን…›› ይለኛል አሥር ጊዜ። ‹‹መቼ?›› ስለው ያሾለኩት መስሎኝ፣ ‹‹እንኳን ጋዜጣ ማንበብ ቆመህስ እግርህ መቼ በቅጡ ይዘረጋል?›› አለኝ። ‹‹በኋላ ታነበዋለሃ፤›› ስለው፣ ‹‹እኔ እኮ ዓላማዬ ማንበቡ አልነበረም። ‘ባቡር ውስጥ ጋዜጣ ሳነብ መውረጃዬን አለፍኩት’ ብዬ ለማውራት እንጂ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? በአንድ በኩል ጉራውን ከሚቸረችርባቸው ሰዎች መሀል አንዱ ስላላደረገኝና ግልጹን ስለነገረኝ ደስ አለኝ። በሌላ በኩል ግን ሥልጡንነት መሠረት የሌለው ኩረጃና ማስመሰል ላይ ተንጠላጠሎ ገጽታውን እየገነባ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? እያልኩ ታመምኩ።

ስለጋዜጣ አነባበባችን ረስተን መረጃን በአግባቡና በሥርዓት ሊያቀብሉን የሚችሉ ጽሑፎች እንዴት ይበራከቱ? እኛስ እንዴት ለንባብ እንትጋ? ብለን መወያየት ሲኖርብን፣ ስለምናሽከረክረው ቅንጡ ዘመናዊ ሞዴል መኪና ነግቶ እስኪመሽ እንቀረድዳለን፡፡ ይኼንን ቅርደዳ ትተን ስለማሽከርከር ብቃታችንና ስለመንገድ አጠቃቀም ሥርዓታችን መወያየት ሲገባን፣ ‘የፌስቡክ አካውንት’ ባለቤት መሆን ከቁጠባ አካውንት ባለቤትነት በላይ ደረት እያስነፋን ስናይ ‘እንዴት ሰው እንሁን?’ መባባል ሲገባን፣ በንድፍ ተጀምረን በንድፍ መጠናቀቃችን እያበገነኝ መጣ። ይኼኔ ነበር ታክሲ ላይ የለመደበት አንዱ ‹‹ወራጅ አለ!›› ብሎ የጮኸው። ሰው በሳቅ ሲፈርስ መልሶ ደገመው። ከእሱ በተሻለ ብዙ የገባቸው ያለ የመሰላቸው ተሳፋሪዎች ‹‹መልስ ተቀብለሃል?›› እያሉ ሲያሾፉ ሳይ ደግሞ ወዳጄ ባቡር ውስጥ ጋዜጣ ዘርግቶ መታየቱን ለምን አጥብቆ እንደፈለገው ልግባህ አለኝ። የቱን አስገብቼ የቱን ላስወጣው?

በሉ እንሰነባበት። ሁለቱ ስካኒያዎች ተሸጡልን። አንዱን ይኼው ይዘነዋል። ‘ኮሚሽኔ’ ከበድ ያለ ስለነበር ለማንጠግቦሽ ከወትሮው ጨመርመር አድርጌ ለአስቤዛዋ ብቆርጥላት ቁርስ ምሳ እራቱን ክትፎ ብቻ አደረገችው። ‹‹ምነው?›› ስላት ‹‹መስቀል ነዋ!›› ሆነ መልሷ። ምን ላድርጋት? ‘ተገኘ ብሎ መዛቅ እኮ ዛሬ ዛሬ ለሆድ ብቻ አይደለም ጦሱ። ጎረቤትም ያያል። ስቀለውም ይከተላል’ እንዳልላት ያው ለእኔው ደስታ ስለሆነ ዝም አልኩ። የባሻዬን ልጅ አዘውትረን ወደምንገናኝባት ግሮሰሪ ይዤው ሄጄ የማንጠግቦሽ ‘ክትፎ ክትፎ’ ማለት እንዳሰጋኝ ስነግረው፣ ‹‹ሞኝ ነህ አንዳንዴ እኮ?›› ብሎ አላገጠብኝ። ሞኝነቴን ሲተነትን፣ ‹‹አንተ ብቻህን ያጡ የተቸገሩትን አስበህ፣ አንተ ብቻህን ለዓለም ሰላም መክረህ ዘክረህ፣ ሙስና ላይ ዝተህ፣ ለዴሞክራሲ ፎክረህ አይሆንማ፤›› አለኝ።

ይኼን የሰማ ደግሞ ቀበል አደረገና፣ ‹‹ኧረ ሰብሰብ ብለህስ ፎክረህ መቼ ሆነ?›› አለው። ‹‹እንዴት?›› ይላል ሌላው። ‹‹ይሰበሰባሉ ይበተናሉ። ያው ችግር፣ ያው ረሃብ፣ ያው ጦርነት መልክና ዓይነቱን እየቀየረ አለ። ጭራሽ ዘንድሮ 70ኛ ቅብጥርስ ብለው የዓለም መንግሥታት ተሰብስበው ባሩድ ባሩድ ኑክሌር ኑክሌር የሚሸት ንግግር እያሰሙ ይቀመጣሉ። ለመነጋገር ከተሰባሰቡ ላለመስማማት ግትር አቋም ይዘው ለምን የትብብር ማኅበር አባል ይሆናሉ?›› ብሎ እያንዳንዳችን ላይ አፈጠጠብን። ‹‹ልጄ ያየውን ሁሉ ግዛ እያለ የሚያፈጥብኝ አይበቃኝም? ምን ያፈጥብኛል?›› ይላል ከባሻዬ ልጅ አጠገብ የተሰየመ ጎርደን በደረቁ የሚጨልጥ። ይኼኔ ተራውን ሌላ ሰው ተነስቶ፣ ‹‹አንድ ጊዜ ብቻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክር ቤት ማይክ ቢሰጠኝ . . .  ‘የሰው ዜጋ የሰው ወገን መሆን ይቅደም። ፖለቲካና ኬላ ወደኋላ!’ የሚል አጭር፣ ድርጅቱ በታሪኩ ሰምቶት የማያውቅ ታሪካዊ ‘ስፒች’ አደርጌ እወርድ ነበር። እዚህ ንግግር ባስረዘመ እየመሰላቸው የሰው ልጆችን የምድረ በዳ ኑሮ ያራዝማሉ። ጠጡ በቃ! እኔም አሳጥራለሁ ብዬ ከማስረዘሜ በፊት!‹‹ ብሎ ሲቀመጥ ግሮሰሪያችን በሳቅ ተናጋች። ‹‹ፖለቲካና ኬላ ወደኋላ?!›› ነው ያለው? እንደ ቃልህ ይሁን በሉታ። እንዲያው ለመሆኑን የቱን አስገብተን የቱን እናስወጣ? መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት