Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክብሔራዊ ባንክ ተቆጣ የግል ባንኮቹም ደስ አላቸው

ብሔራዊ ባንክ ተቆጣ የግል ባንኮቹም ደስ አላቸው

ቀን:

የ2008 ዓ.ም. የመልካም አስተዳደር ዓመት ቢባል ጥሩ ገላጭ ነው፡፡ ዓመቱ እንደገባ መንግሥት ካሉበት ችግሮች የከፋው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው በሚል የህልውናው ጉዳይ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ መንግሥት ሕዝብ አገልጋይ በሆኑ ሴክተሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠንክሮ እንደሚሠራ፣ ያጠፉ በሕግ የሚቀጡበት፣ አላሠራ ያሉ መዋቅሮች የሚስተካከሉበት፣ ሕዝቡ በመንግሥት ሥራ (ዕቅድ፣ ትግበራና ግምገማ) የሚሳተፍበት እንደሚሆን ቃል ገብቶልናል፡፡ የመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ሰኞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመሠረትም ዝርዝር የመንግሥትን ዕቅዶች የምንሰማ ይሆናል፡፡ ምንም ጠያቂና ተፎካካሪ ተቃዋሚ በሌለበት ቀጣዩ ምክር ቤት መንግሥት በራሱ አነሳሽነትና ገምጋሚነት ሊሠራ እንደሚገባ መካሪ አይፈልግም፡፡ መንግሥት በግሉ ዘርፍም ያለው መሠረታዊ ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን በመገንዘብ በአክሲዮን በተደራጁ ማኅበራት በተለይም በግል ባንኮች ላይ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የቆረጠ ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት የፀደቀው የባንኮች የኩባንያ አስተዳደር መመርያ የዚህ ቁርጠኝነት መገለጫ ነው፡፡ የ20 ዓመታት ዕድሜ ያለው የግሉ የፋይናንስ ሴክተር የሕዝብ ገንዘብ የሚያስተዳድር እንደመሆኑ የመልካም የኩባንያ አስተዳደሩ በሽታ ካልታከመለት የመንግሥት ጥረት ምሉዕ አይሆንም፡፡

ከመመርያው በፊት ለዘመናት ስንሰማቸው የነበርናቸው ችግሮች እልባት የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፍ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ በየጋዜጣውና ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን በየዕለቱ የምንሰማው የግል ባንኮችን ክፍተትና የኃላፊዎችን መነሳት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ የቦርድ አባልና የዓለም አቀፍ ባንኪንግ ኃላፊ መነሳታቸውን ሰምተናል፡፡ ምክንያቱም ከውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጋር በተያያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት አዋሽ ባንክ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱን ያሰናበተበትን ዜና እስኪሰለቸን ሰምተናል፡፡ የንብ ባንክ በጅግጅጋ አካባቢ በተፈጸመ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ የኃላፊዎቹ የወንጀል ጉዳይ በምርመራ ላይ መሆኑን ከሰማን ቆየን፡፡ ፖሊስ አጣርቶ ለዓቃቤ ሕግ መዝገቡን ያስተላለፈው፣ ይዝጋው መረጃው ለሕዝብ ባይገለጽም፡፡ በብርሃን ባንክም ከቦንድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ እንደነበሩና ባንኩም ጉዳት ደርሶበት ፍርድ ቤት እንደሚከራከር ዜና መስማታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በየባንኩ መሰል ጉዳዮች ቢፈተሹ ቁጥራቸው ከፍ እንደሚል ይታመናል፡፡

በባንክ ሥራ እንደ ውጭ ምንዛሪና ብድር ያህል ለሙስና የተጋለጠና የአደባባይ ወንጀል የሚፈጸምበት ‹‹ቢዝነስ›› ያለ አይመስልም፡፡ በጨረታ፣ በግዥ፣ በቦንድ፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በውል አፈጻጸም፣ ንብረት አስተዳደር፣ አክሲዮን ሽያጭና አስተዳደር፣ ወዘተ ከዚህም የከፉ የአሠራር ክፍተቶች ቢኖሩም የውጭ ምንዛሪና ብድር ያህል ገንነው ሲወጡ አይስተዋልም፡፡ እነዚህ ሁለት የባንክ ሥራዎች በአንድ በኩል የተወሰኑ የግል ባንኮችን የቦርድ አባላት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችና ሠራተኞች ያላግባብ ያከበሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የባለአክሲዮኑን መብትና የመንግሥትን ገቢ እጅጉን ጐድተዋል፡፡ ውጭ ምንዛሪና ብድር ላይ የሠራ በአጭር ጊዜ  ባለፎቅ፣ ባለመኪና፣ ባለሰፊ ንግድ መሆን የሴክተሩ መገለጫ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሥራዎች ላይ የሚመደቡት ሰዎችም ከሊቅ እስከ ደቂቅ በደምና በጥቅም የተሳሰሩ ስለመሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡

አሁን የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ እነዚህ በባንክ ውስጥ የሚታዩ ያልተገቡ ድርጊቶችን ሊታገስ እንደማይችል ብሔራዊ ባንክ ቁርጠኝነቱን ያሳየበት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ አመረረ፣ ተቆጣ፣ ቆረጠ ሲሉ አንዳንዶች ከመመርያው መውጣት በኋላ የገለጹት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የመመርያውን መውጣት የነገረኝ አንድ ባንክ ውስጥ የሚሠራ ባልንጀራዬ ‹‹መመርያው ብሔራዊ ባንክ ትዕግስቱ አልቆና ተቆጥቶ ያወጣው›› እንደሆነ ገልጾ ‹‹ብሔራዊ ባንኩ መመርያዎችን የማስፈጸም ብቃቱ አለመጠንከር፣ ውስብስብ አሠራር በግል ባንኮቹ ውስጥም ለመተግበር ባንኮቹ አቅምና ፈቃደኝነት እንደሌላቸው ስለሚያውቁት እነሱንም አያስከፋም፤›› ሲል ተቃርኖ በተሞላበት የምጸት ቃል መመርያውን ገለጸልኝ፡፡ መመርያው የእውነትም ቢሆን ጠቃሚ ነጥቦችን እንደመያዙ ካልተፈጸመ የወረቀት ላይ ነብር መሆኑ አይቀርም፡፡ ለመሆኑ መመርያው ባንኮቹን የሚጠቅሙ ምን ዓይነት መርሆችንና አሠራሮችን ይዟል? የመመርያው መውጣት ለባንኮቹ ያለው ጠቀሜታስ ምንድነው? ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ለማስፈጸም ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ይገጥሙታል? የሚሉትንና ተያያዥ ነጥቦች በዚህ ጽሑፍ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የመመርያው ብስራት

መመርያው ያካተታቸው ብዙዎቹ መርሆች አዲስ አይደሉም፡፡ የተወሰኑት ጥሩ ተሞክሮ ባላቸው የግል ባንኮች ሲተገበሩ የቆዩ ሲሆን፣ በባንክ ሙያም የታወቁና ለሁሉም የተገለጡ ናቸው፡፡ የባንኮች የኩባንያ አስተዳደርን በተመለከተ የባዜል ኮሚቴም በተለያዩ ጊዜያት ለባንክ ቁጥጥር ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸውን መርሆች ዘርዝሯል፡፡ አገሮች የኮሚቴውን ሐሳብ መነሻ በማድረግ በየአገራቸው ዐውድ መተግበር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የእኛ አገር ግን መመርያዎቹና መርሆቹ ቀድመው ሳይዘጋጁ ባንኮቹ ፈቃድ ስለተሰጣቸው፣ ሥራም ስለጀመሩ መርሆቹን ተግባራዊ የሚያደርግ መመርያ ዘግይቶም ቢሆን አስፈልጓል፡፡

በባዜል ኮሚቴ መመርያ መሠረት ለባንኮች ተፈጻሚ የሚሆን የኩባንያ አስተዳደር የባንኮቹ የዳይሬክተሮች ቦርድና ሥራ አስፈጻሚዎች የባንኮቹን ተቋማዊ ዓላማና ሥራ ሲተገብሩ ሊመሩበት የሚገባውን ሁኔታ የሚደነግግ ነው፡፡ የባንኮቹን ዓላማዎች በዝርዝር መቅረፅ፣ የዕለት ተዕለት ሥራውን ማከናወን፣ የባለድርሻ አካላት ፍላጐትን ግንዛቤ ማስገባት፣ ተገቢነት ያላቸውን ሕግጋትና ደንቦች መሠረት አድርጐ ባንኮችን ከሥጋት ነፃና ጤናማ አሠራር እንዲኖራቸው ማድረግና የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ መርሆችን እንዲያካትት ይጠበቃል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ያወጣውም መመርያ ይህንኑ የሚዳስስ ነው፡፡ ዓላማው የፋይናንስ ሥርዓቱን ደኅንነት መጠበቅ የባለአክሲዮኖችንና ሌሎች ጥቅም ያላቸውን ባለድርሻ አካላት ዘለቄታዊ ጥቅም ማስጠበቅና ባንኮች ጤናማና በዕውቀት የተመሠረተ አስተዳደር እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ተግባራዊ ለማድረግ መመርያው የዳይሬክተሮች ቦርድም ሆነ ማንኛውም ሠራተኛ የባንኩን የብድር ፖሊሲ እንዳይጥስ፣ የጥቅም ግጭት እንዲያርቅ፣ ማንኛውንም የብድርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥን በየወሩ ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም፣ ዝርዝር የብቃት፣ የችሎታና የሥልጠና መስፈርቶች እንዲሟሉ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መጠንና ስብጥር እንዲወሰን፣ በውክልና የሚሰጥ ድምፅ እንዲገደብ፣ የቦርድ ስብሰባዎች በጥብቅ ክትትል እንዲከናወኑ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ዘመናቸውን ሲጨርሱ የማጠቃለያ ሪፖርት እንዲያቀርቡ፣ ወዘተ በዝርዝር ደንግጓል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አካላትና ሥራ አስፈጻሚዎች መመርያውን ከጣሱ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ተጠያቂ ከሚሆኑት በተጨማሪ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች (መታገድ፣ ብድር መከልከል፣ እንዳይመርጡ መከልከል፣ የሥራ ዋጋ እንዳይከፈል፣ ወዘተ) እንደሚወሰዱባቸው መመርያው የሕግ መሠረቱን ጥሏል፤ የነበረውንም አስፍቷል፡፡

መመርያው ለብሔራዊ ባንኩ ያለው ፋይዳ

መመርያው ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ የተሰጠውን ዓላማዎችና ተግባራት እንዲያስፈጽም በተሻለ ይረዳዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ዓላማ የተረጋጋ የዋጋና የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስፈን፣ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት መገንባትና ለኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ ልማት አመቺ የሆኑ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ማከናወን ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኩ የግል ባንኮችን የኩባንያ አስተዳደር በአግባቡ እንዲመራ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማግኘቱ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደኅንነቱ እንዲረጋገጥና ጤናማ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ከአውሮፓውያን ልምድ ለመገንዘብ እንደምንችለው የኢኮኖሚ ቀውስ የባንኮቹን ውድቀት ተከትሎ የሚመጣው ከኩባንያ አስተዳደር ክፍተት ጋር የተያያዙ የቁጥጥር ጉድለቶች፣ የአደጋ/ጉዳት ትንተና (Risk Analysis) እንዲሁም ያልተገባ የካሳ ክፍያ የሚያመጣው ጣጣ መሆኑን ነው፡፡ የመመርያው መውጣት ብሔራዊ ባንክ አሁን ያለው የግል ባንኮች ችግር ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን፣ በስፋት ሳይቃጠል በቅጠል እንዲያስተካክል ይረዳዋል፡፡

መመርያው ለብሔራዊ ባንክ የባንኮችን የኮርፖሬት አስተዳደር በመጣስ ጥፋት የፈጸሙ ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ባንኩን ለመቅጣት የሕግ መሠረት ይሰጠዋል፡፡ መመርያው ዝርዝር ነጥቦችን በማካተቱ የብሔራዊ ባንኩን ቁጥጥር የተሻለ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ባንኩ ቀደም ሲል የባንኮችና የፋይናንስ ደኅንነትን ለመጠበቅ፣ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም ለማስከበር፣ ጤናማ የባንክ ሥርዓት እንዲኖር፣ ወዘተ በሚሉ ጠቅላላ ምክንያቶች የሚያደርገውን ቁጥጥር ግልጽና ዝርዝር ባሉ ሁኔታዎች ሥልጣኑን እንዲጠቀም ያስችለዋል፡፡ ለምሳሌ የአንድ የግል ባንክን የብድር ፖሊሲ በመተላለፍ ያልተገባ ብድር ያፀደቀ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የባንኩ የውስጥ አስተዳደር (Autonomy) አካል ነው በሚል በብሔራዊ ባንክ እንዳይጠየቅ መከላከያ አይሆነውም፡፡

የግል ባንኮቹ ደስታ

የመመርያው መውጣት ለግል ባንኮቹ ዕድገት፣ ጤናማ ውድድር ውጤታማነት ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመመርያው መውጣት ሁሉንም አስደስቷል ማለት አይቻልም፡፡ በባንክ ውስጥ ለግል ጥቅማቸው የሚሮጡ፣ መፈረም እንጂ ሥራ መሥራት ለማይወዱ፣ የባንክ ሙያ ሲያልፍ ላልነካቸው ሰዎች መመርያው መርዶ ነው፡፡ መመርያው በሚረቀቅበትና ለውይይት በቀረበበት ወቅት በተደረጉ ምክክሮች አንዳንድ ከባንክ የተወከሉ ሰዎች መመርያው የማያሠራና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ስለመሆኑ ተገቢ ያልሆነ ትችት ያቀረቡ አልጠፉም፡፡ መጽሐፉ መለየትን/ሃጥያትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል እንዳለው ነው፡፡ መስረቅ ልማዱ ለሆነ ሰው ሌብነት ማስቀጣቱ ብቻ ሳይሆን የመጸወተ መሸለሙን ሲሰማ ደስ አይለውም፡፡ ሕግ፣ ደንብ፣ መመርያ፣ ፖሊሲ፣ ፍርድ ቤት ወዘተ. ለእነዚህ ሰዎች የማይወዷቸው ጠላቶቻቸው አድርገው ይቆጥሩዋቸዋል፡፡ መመርያ ካለ ያለመመርያ በመሥራት የሚያገኙት ጥቅም ይቋረጥባቸዋል፡፡ የባንኮቹ የኩባንያ አስተዳደር ጠቃሚነትን ያልተረዱ አንዳንድ ግለሰቦች መመርያው በአስገዳጅነት ተግባራዊ በሆነበት በዚህ ወቅትም መቃወማቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሆኖም ውሾቹ ሊጮሁ፣ ግመሎቹ ሊጓዙ ግድ ነው፡፡

ጸሐፊው መመርያው ለግል ባንኮቹ ደስታ ነው ሲል የገለጸው ባንኮቹን እንደ ተቋም፣ የባንኪንግ ኢንዱስትሪውን እንደ ሴክተር፣ ባለአክሲዮኑንና ገንዘብ አስቀማጩን እንደ ተጠቃሚ በመውሰድ ነው፡፡ ለእነዚህ አካላት የመመርያው መውጣት ትልቅ የአዲስ ዓመት ስጦታ ነው፡፡ የተወሰኑ ጥቅሞቹን እናንሳ፡፡ መመርያው ግልጽነትና ተጠያቂነትን በባንኮች ያሰፍናል፡፡ ባንኮች ግብይታቸውንና ሚስጥር ያልሆነውን መረጃቸውን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ፣ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ስላለባቸው ማን፣ ምን፣ እንዴትና መቼ እንደሠራ ግልጽ ይሆናል፡፡ ያጠፉትንም በሕግ ለመጠየቅ መረጃዎቹ ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ባንኮችም ትርፋማነታቸው ይጨምራል፡፡ በየባንኩ ያልተፈለጉ ወጪዎች (ኮሚሽን፣ ያልተገባ ግብዣ፣ ያልታወቀ ግብይት) ስለሚቀር ባንኮቹ ትርፋቸው ይጨምራል፡፡ የግል ባንኩ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ዕውቀትና ሥልጠና ባላቸው፣ ከፍ ባለ የሥነ ምግባር ደንብ በሚገዙ የዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመራ ባንክ ተወዳዳሪነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ መመርያው የባንኮች ቦርድ የጥቅመኞች ጥርቅም ሳይሆን ለአገሪቱ የፋይናንስ ዕድገት ሰፊ ራዕይ ባላቸው ስብጥር ባለሙያዎች እንዲደራጅ ያስችላል፡፡ የፋይናንስ ሴክተሩም ጤናማና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የሚሆነው መመርያው ከመውጣት ባለፈ ሲፈጸም ነው፡፡ የኩባንያ አስተዳደር ባልጠነከረባቸው አገሮች ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት፣ ሙስና፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመሰል፣ ወዘተ ዓይነት ለፋይናንስ ሴክተሩ ብቻ ሳይሆን ለአገር ደኅንነት አስጊ የሆኑ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ መመርያው እነዚህን ወንጀሎች በመከላከል የፋይናንስ ሴክተሩ ጤናማ እንዲሆን ያስችላል፡፡

በመመርያው መውጣት ባለአክሲዮኖችና ለወደፊቱ በባንክ ሴክተሩ ኢንቨስት ለማድረግ ላሰቡ ዜጐች ሰፊ ጥቅም አለው፡፡ የኩባንያው አስተዳደር በአግባቡ መተግበር በባለአክሲዮኑና በባንኩ ሥራ አስፈጻሚ መካከል በሚፈጠር የጥቅም ግጭት ምክንያት ባለአክሲዮኖች የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች የባለአክሲዮኖች ወኪል ቢሆኑም የራሳቸውን ጥቅም በማሯሯጥ የባለአክሲዮኖችን ጥቅም ቸል ሊሉት ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግርን ለመቅረፍ ባለአክሲዮኖች ጠንካራ የቦርድ አባላትን በመምረጥና በመቆጣጠር መሠረታዊ ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ይሠራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር መመርያው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ በተወሰኑ ግለሰቦች ተፅዕኖ እንዳይወድቅ የውክልና ገደብ ማስቀመጡ፣ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ በቋሚነት እንዲዋቀር በአስገዳጅነት መደንገጉና ባለአክሲዮኖች ተገቢው መረጃ እንዲሰጣቸው መደንገጉ የባለአክሲዮኖችን መብቶች በተሻለ እንዲከበሩ ይረዳል፡፡ በባንከ ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ጥቅመኞችን በመመልከት በባንኮች አክሲዮን ለመግዛት (ኢንቨስት ለማድረግ) ለሚፈሩም መልካም የኩባንያ አስተዳደር የራስ መተማመን ይሆናቸዋል፡፡ መልካም የኩባንያ አስተዳደር ባንኮች ከውጭ ምንጭ የሚያገኙት ፋይናንስ እንዲጨምርና የካፒታል ወጪ እንዲቀንስ ስለሚረዳ የስቶክ ገበያ በሌለባት አገራችን ባንክ ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን መተማመን ይሆናሉ፡፡ መልካም አስተዳደሩ ጥሩ በሆነ ባንክ በትልቅ ፕሪሚየም አክሲዮን የሚገዛ፣ ገንዘቡን በቁጠባ መልክ የሚያስቀምጥ ለሚፈልገው የንግድ ዓላማ የሚበደር ባለሀብት ምርጫ መሆኑ አይቀርም፡፡

የመመርያውን ፍሬ ለመብላት

መመርያ ማውጣት በራሱ በመመርያው ያሉ መልካም መርሆች እንዲተገበሩ ዋስትና አይሆንም፡፡ ለመመርያው አለመፈጸም ብዙዎች የሚያነሱት ምክንያት የብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ያለመሆን ነው፡፡ በጽሑፉ መግቢያ ዋቢ ያደረግነው የባንክ ባለሙያ እንደተናገረው አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች በመመርያው መውጣት የማይደነቁት ብሔራዊ ባንከ አያስፈጽመውም ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ጥንካሬው አሁን ያሉትን የግል ባንኮች ከመቆጣጠር አንፃር መመዘን አለበት፡፡ ብሔራዊ ባንኩ አደረጃጀቱን ካላሰፋ፣ የሰው ኃይሉን በቁጥርም በብዛትም ካላበቃ፣ አሠራሩን ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ካላደረገ መመርያውን ለመፈጸም ይከብደዋል፡፡ ፊሊት በቤት ውስጥ ያሉ ነፍሳትን የሚገድለው በቤቱ ግድግዳ ላይ ስለተንጠለጠለ ሳይሆን፣ ጥሩ ባለሙያ ከግድግዳው አውርዶ፣ ሌላውን ዕቃ እንዳይበክል አድርጎ ነፍሳትን ሲገድልበት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም ከባንኮቹ መረጃ በየወሩ ቢደርሰው፣ ጥፋቶች በየወቅቱ ቢጠቁሙት፣ አሠራሩንና አደረጃጀቱን ካላጠናከረ መመርያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለማስቻል ይከብደዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የሴትልመንትስ ባንክ የተወሰኑ የተቆጣጣሪውን ድርሻዎች ይዘረዝራል፡፡ በዚሁ መሠረት ተቆጣጣሪው ባንክ ጤናማ የኮርፖሬት አስተዳደር መልካም ተሞክሮዎችን ማሳየት፣ መልካም አስተዳደር የገንዘብ አስቀማጩን የሚጠብቅ መሆኑን ማስረጽ፣ ባንኮች የቀረጹት መልካም አስተዳደር ፖሊሲ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ፣ በባንክ ውስጥ የሚገኙ የኦዲትና የቁጥጥር ሥራዎች ጥራትን መገምገም፣ በባንኮች ውስጥ የሚዋቀሩ አደረጃጀቶችን ውጤት ማጥናት፣ በባንኮች ላይ ችግሮች በምርመራ በተገኙ ጊዜ ለቦርድና ለሥራ አስፈጻሚ በማሳወቅ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የመመርያው መውጣት ለብሔራዊ ባንኩ ትልቅ ስኬት ቢሆንም ዋናው ፈተና የመመርያውን ይዘት በፍጥነትና በምልዓት ማስተግበሩ ላይ ነው፡፡ መመርያው ሲተገበር የብሔራዊ ባንክም ቁጣ ይበርዳል፣ የግል ባንኮችም ደስታ ፍጹም ይሆናል፡፡                         

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...