Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን ለደረስንበት ደረጃ ያበቃን አንዱ ትልቅ ነገር የአገሪቷ ዕድገት ነው››

 አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከ30 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ የግንባታ ሥራዎችን በጣሪያ ጥገናና በቀለም ቅብ የጀመረውን እንቅስቃሴ ወደ ትላልቅ ግንባታዎች ማሸጋገር ችሏል፡፡ ከግንባታው ዘርፍ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሠሩ ኩባንያዎችን እንዲፈጥር አስችሎታል፡፡ አሁን በተለያየ ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ አራት ኩባንያዎች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ አራት ኩባንያዎች በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሕንፃ፣ በመንገድና በሪል ስቴት ግንባታዎች ላይ በማተኮር የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ሰንሻይን ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ በሆቴል ልማት ዘርፍና በቅይጥ ሕንፃ አገልግሎት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ሰን ሲስተርስ ትሬዲንግ የተባለው ሦስተኛው ኩባንያ ደግሞ በልብስ ንፅህና መስጫ፣ በውበት ሳሎንና በሕንፃ ኪራይ አገልግሎት ላይ የሚሠራ ነው፡፡ አራተኛው ድርጅቱ ደግሞ በበጐ አድራጐት ሥራ ላይ የተሰማራው ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን የሚባለው ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአራቱም ድርጅቶቹ 6,200 ሠራተኞችን ይዟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰንሻይን በቢዝነስ ኩባንያ አማካይነት በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በመግባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከሁለት ዓለም አቀፍ የሆቴል ኩባንያዎች ጋር በመሆን እየሠራ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የማሪዮት ኤግዚኪዩቲቭ ሆቴል ገንብቶ ሥራ ሲያስጀምር፣ ከማሪዮት ጋር በመዋዋል የሚገነባው ሌላ ሆቴል አለ፡፡ ኩባንያው ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰም ነው፡፡ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እንቅስቃሴን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከዳዊት ታዬ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰንሻይን ከኮንስትራክሽን ግንባታ በተጨማሪ በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች ውስጥ ገብቷል፡፡ የኩባንያዎቻችሁ ወቅታዊ አቋም ምን ይመስላል?

አቶ ሳሙኤል፡- መጀመሪያ ላይ የተቋቋመው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የሚባለው ድርጅታችን ነው፡፡ ሥራ ሲጀምር በሕንፃ ግንባታዎች ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል፡፡ ቀጥሎ ወደ መንገድ ሥራ፣ ከዚያም ወደ ሪል ስቴት ልማት በመግባት ብዙ ሥራዎች አከናውኗል፡፡ አሁን ደግሞ መንግሥት የግል ባለሀብቱ ኢንዱስትሪ ላይ ማተኮር አለበት ባለው መሠረት፣ እኛም ወደ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ትኩረት በማድረግ ሰንሻይን ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባል ኩባንያ በማቋቋም የሆቴል ኢንቨስትመንቱን በመቀላቀል ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የሚባለውን የሆቴል ዘርፍ በመምረጥና ትኩረት ሰጥተን በትልልቅ የሆቴል ኢንቨስትመንት ግንባታዎች ውስጥ ገብተናል፡፡ ትልልቅ የሆቴል ግንባታዎች ግን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ እኛ ደግሞ በሆቴል ኢንቨስትመንት የመጀመሪያ ሥራችንን የጀመርነው ከማሪዮት ኢንተርናሽናል  ሆቴል ጋር የማኔጅመንትና የፍራንቻይዝድ ኮንትራት ስምምነት በማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስምምነታችንም የማሪዮት ኤግዚኪውቲቭ አፓርትመንት ሆቴል በመሥራት ነው፡፡ ይህም ሆቴል ግንባታው ተጠናቅቆ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት ተመርቆ ሥራ ጀምረንበታል፡፡ ሁለተኛው ስምምነታችን ደግሞ ኮርዲያል ማሪዮት ሆቴልን ለመገንባት ነበር፡፡ ኮርዲያል ማሪዮት የሚባለው የሆቴል ደረጃ አነስተኛና የቢዝነስ ሆቴል ስለሆነ በኮርዲያል ደረጃ ከመገንባት ይልቅ፣ በማሪዮት ኢንተርናሽናል ሆቴል ደረጃ ለመገንባት እንደገና በአዲስ ኮንትራት ስምምነት አድርገን በማሪዮት ኤግዚኪዩቲቭ ሆቴል ምረቃ ሥርዓት ላይ ተፈራርመናል፡፡ 

ይህ ሆቴል በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገነባ ነው፡፡ ሦስተኛው ሐዋሳ ላይ የምንሠራው ነው፡፡ ሐዋሳ ሒልተን ሪዞርትና ስፓ የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ የፍራንቻይዝድና የሆቴል አስተዳደር ሥራውን ለመሥራት ከሒልተን ኢንተርናሽናል ጋር በዚህ ሳምንት ተፈራርመናል፡፡ ከሒልተን ኢንተርናሽናል ጋር ያደረግነው የማኔጅመንትና የኮንትራት ስምምነት ነው፡፡ እኛ እንደ ባለቤትና ገንቢ ሆነን እንሠራለን፡፡ የሆቴል ሙያው ስለሌለን ሥራውን ለባለሙያ ሰጥተን የምናከናውነው ይሆናል፡፡ ይህንንም ማድረጋችን አገራችን በዚህ የሆቴል ሥራ ዘርፍ ልታገኝ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ጭምር የሚረዳ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ማሪዮት ከሁለት ሚሊዮን ያላነሱ ደንበኞች አሉት፡፡ እነዚህ ደንበኞች ከአገር አገር ሲዘዋወሩ አባል የሆኑበት ሆቴል ማረፍ የሚመርጡ በመሆኑ ጥሩ ገበያ ዕድል ይገኝበታል፡፡ የሒልተን ሆቴልም በተመሳሳይ የሚሠራበት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመረጡ ሆቴሎችን እዚህ ማምጣታችን አገርን ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ ደስተኞች ነን፡፡  

ሪፖርተር፡- የሐዋሳ ሪዞርትን ለመገንባት ከአንደ ዓመት በፊት ኮንትራት ፈጽማችሁ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ኮንትራቱ ደግሞ ከማርዮት ጋር የተፈረመ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሐዋሳውን ሪዞርት ከሒልተን ጋር እንገነባለን ብላችኋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ከዓለም አቀፉ የሒልተን ሆቴል ጋር የፈጠራችሁት ጥምረትስ ከአዲስ አበባ ሒልተን ጋር ግንኙነት ይኖረዋል?

አቶ ሳሙኤል፡- በሐዋሳ ሪዞርት ለመገንባት ስንነሳ ብራንድ ሳንለውጥ ሦስቱንም ሆቴሎች ከማሪዮት ጋር ብንሠራ ለማኔጅመንት ይጠቅመናል በሚል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ማሪዮት ሪዞርት ብለን የሐዋሳን ቦታ የወሰድነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ግን ማሪዮት አፍሪካ ውስጥ ምንም ዓይነት የሪዞርት ግንባታ ስለሌለውና ኢትዮጵያ ውስጥም ሪዞርት ቢዝነስ ውስጥ ለመሰማራት ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት መሆኑን በመግለጽ ይህንኑ በደብዳቤ ስላሳወቁን ነው፡፡ ይህ ከሆነ የግድ መገፋፋት ስለማይቻል ሌላ ምርጫ ውስጥ መግባት ስለነበረብን ከሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ ከሒልተን ኢንተርናሽናል ጋር ተስማምተናል፡፡ ሁለቱም የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ሒልተን ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ሪዞርቶች አሉት፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሒልተን ሆቴል በተገነባበት ወቅት የኮንትራት ስምምነቱ ላይ ምንም ዓይነት የሒልተን ሆቴል ኢትዮጵያ ውስጥ አይገነባም የሚል ገደብ ነበረበት፡፡ ከሒልተን ጋር ለመሥራት እየተነጋገርን በነበርንበት ወቅት ግን ዕድለኞች ሆነን በኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው ገደብ ተነሳ፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሁለት ሪዞርት መገንባት ትችላላችሁ በማለት የሒልተን ኢንተርናሽናል ሆቴል ቦርድ ፈቀደላቸው፡፡ ይህንን ዕድል በሐዋሳው ሪዞርት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ከተደራደርን በኋላ ተቀበልን፡፡ የሐዋሳውን ግንባታ ከማሪዮት ወደ ሒልተን የተለወጠበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ በዚሁ ለውጥ ምክንያት ግንባታውን የምናካሂደው ከሒልተን ኢንተርናሽናል ጋር መሆኑን ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አሳወቅን፡፡ ዲዛይኑም እንደገና ተለውጦ ተሠራ፡፡ ከአዲስ አበባ ሒልተን ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም፡፡ ምናልባት ማኔጅመንቱ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዲፓርትመንት ሥር ስለሚሆን፣ ሁለቱንም ሊቆጣጠር ከመቻሉ ውጪ የእኛና የአዲስ አበባ ሒልተን ግንኙነት የላቸውም፡፡ በእነዚህ የሆቴል ፕሮጀክቶቻችን ላይ ማሪዮትም ሆነ ሒልተን የባለቤትነት ድርሻ የላቸውም፡፡ ማኔጅመንቱን እነሱ ይሠራሉ፡፡ የምንጠቀምበት ስምና የአገልግሎት ደረጃ የእነሱ ነው፡፡ ለዚህ አገልግሎታቸው ሒልተንና ማሪዮት የሮያሊቲ ክፍያ ያገኛሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- የሐዋሳው ሪዞርት ከማሪዮት ወደ ሒልተን በመለወጡ ከማሪዮት ጋር በተስማማችሁበት ወቅት አሠርታችሁት የነበረው ዲዛይን ይለወጣል ማለት ነው? የሆቴሎቻችሁን ዲዛይን ማነው የሠራው?

አቶ ሳሙኤል፡- አዎ! ተለውጧል፡፡ በአዲስ ዲዛይን ነው የሚሠራው፡፡ የሐዋሳውን ዲዛይን የሠራው ዳይሜንሽን የተባለ የዱባይ ኩባንያ ነው፡፡ ያስመረቅነው የማሪዮት ኤክዚኪዩቲቭ ሕንፃ የመጀመሪያ ዲዛይን ግን የተሠራው በአገር በቀሉ ወሰን ኮንሰልታንት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማሪዮት ኤግዝኪዩቲቭ ሆቴል ግንባታ ረዥም ጊዜ ወስዷል፡፡ የአዲስ አበባውን ማሪዮትና የሐዋሳውን ሒልተን ሆቴሎች ግንባታ በሦስት ዓመት እንጨርሳለን ብላችኋል፡፡ በእርግጥ በተጠቀሰው ጊዜ ልትጨርሱ ትችላላችሁ?

አቶ ሳሙኤል፡- ልክ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሆቴል ከአምስት ዓመታት በላይ ፈጅቷል፡፡ መጀመሪያ ሕንፃው ሲሠራ ለቢሮ አገልግሎት ይውላል ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ እንደማንኛውም ዓይነት መደበኛ ሆቴል አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ድጋሚ አስተካክለን ሠርተነውም ነበር፡፡ በኋላ ግን በዓለም አቀፍ ሆቴል ደረጃ እንዲለወጥ ወሰንን፡፡ ይህንንም ለመለወጥ ብዙ ችግሮች ስለነበሩበት ጊዜ ወስዷል፡፡ ችግሩ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ሆቴሎች እጅግ ብዙ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ስለነበር ነው፡፡ ለሆቴሉ የምንጠቀምባቸው ግብዓቶች እያንዳንዱን ደረጃ ማሟላታቸውን ማረጋገጥ ስለሚገባ ሥራው ፈታኝ ነበር፡፡ አዳዲሶቹ ግንባታዎቻችን ግን ከመነሻውም ለሆቴል ተብለው ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ ትልቁ ነገር የሆቴል ፕሮጀክት የግንባታ ሲካሄድ ከሚያስፈልገው ግብዓት ውስጥ 70 በመቶ ያላነሰው ከውጭ የሚመጣ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለዚህ ዘርፍ መንግሥት የተለየ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ ሁለቱን ሆቴሎች በሦስት ዓመት ለመጨረስ አቅደናል፡፡ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ ችግር ካልኖረ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚሠራ ነው፡፡ በሦስት ዓመት ለመጨረስ ፕሮግራም አድርገናል፡፡ አንዳንዴ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም በጊዜ ገንብተን ለመጨረስ እናስባለን፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ደግሞ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ይህ ዘርፍ ስለሆነ፣ እገዛ ይደረጋል የሚል እምነት ያለን በመሆኑ ደግሞ ብዙም ሥጋት ላይኖር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ማሪዮት ኤግዝኪዩቲቭ የሚል መጠሪያ ያለው ሰሞኑን ያስመረቃችሁት ሆቴል ምን ያህል ወጪ ጠየቀ? አዳዲሶቹስ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃሉ ተብሎ ይገመታል?

አቶ ሳሙኤል፡- ማሪዮት ኤግዝኪዩቲቭ በሚል መጠሪያ አገልግሎት የጀመረው ሆቴል ወደ 45.5 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቷል፡፡ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገነባው ማሪዮት ሆቴልና የሐዋሳው ሒልተን ሪዞርት በዓለም አቀፍ የሆቴል ስታንዳርድ ደረጃ የሚገነቡ በመሆናቸው የኢንቨስመንት ወጪያቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የሆቴሎቹ የግንባታ ደረጃ በባለሙያዎች በተቀመረው ግምት መሠረት አዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገነባው ማሪዮት ሆቴላችን 75 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል፡፡ የሐዋሳው ሒልተን ደግሞ 41 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል፡፡ የሦስቱ ሆቴሎች አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ወጪ 161 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት 3.2 ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሰንሻይን ፋውንዴሽን ነው፡፡ ይህ ፋውንዴሽን ወቅታዊ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል?

አቶ ሳሙኤል፡- ከእኔ አስተዳደግ በመነሳት የ30 ዓመታት ጉዞዎችን ወደኋላ ማየት ይጠይቃል፡፡ ተወልጄ ያደግሁት ጨርቆስ ከምትባለው የ‘ቺስታዎች’ ሠፈር ስለነበር ከዚያ ተነስተን አሁን የደረስንበት ደረጃ ስንደርስ ማሰብ የሚኖርብን ነገር አለ፡፡ እንደ አገር የውጭ ድርጅቶች ብቻ የተጐዱ ወገኖቻችን መደገፍ የለባቸውም፡፡ ለበጐ አድራጐት ሥራ የውጭ ኩባንያዎችን ብቻ መጠበቅ ጥቅም የለውም፡፡ እኛም ሥራችን እያደገ ሲመጣና አንድ ደረጃ ስንደርስ ሰንሻይን ፋውንዴሽንን ለምን አናቋቁምም በሚል ተነሳሳን፡፡ ፋውንዴሽኑ ሲመሠረትም የመጀመሪያ ዓላማ አድርጐ የተነሳነው ቤተሰቦቻቸው ሊያስተምሯቸው የማይችሉ ችግረኛ ልጆችና ቤተሰቦቻቸውን በኤችአይቪ ያጡ ወገኖችን ዕርዳታ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን ዕቅድ ስናወጣ የሰንሻይን የመጀመሪያ ሕንፃን በማሰብ ነው፡፡ ይህ ሕንፃ በሚሠራበት ጊዜ ግንባታው የፈጀው 12 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ሕንፃው አሥር ጊዜ እጥፍ የሚሆን ወጪውን መልሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕንፃው በዓመት እስከ 15 ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል፡፡ ይህንን ገቢ ለፋውንዴሽኑ አድርገን ፋውንዴሽኑ ተቋቋመ፡፡ ይህንን ያደረግነው ፋውንዴሽኑ ችግር እንዳይገጥመው፣ የራሱ ገቢ ብቻ ኖሮት እንዲተዳደር ለማድረግ ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ሥራችንን ከየት እንጀምር በማለት የመጀመሪያው ሥራችን ሰፊ ሕዝብ ባለው ክልል እንጀምር ብለን የመጀመሪያውን የትምህርት ቤት ግንባታ በነቀምት ከተማ አደረግን፡፡ ለነቀምት ትምህርት ቤት ግንባታ 11 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ሥራ ጀምሯል፡፡ አሁን 360 ተማሪዎችን እያስተማርንበት ነው፡፡ ሁለተኛው ትምህርት ቤት ደግሞ በ2003 ዓ.ም. አክሱም ውስጥ እንዲሆን ተወስኖ የአክሱም ትምህርት ቤት በ11.5 ሚሊዮን ብር ገንብተን ሥራ አስጀምረናል፡፡ ሦስተኛውን ትምህርት ቤት የገነባነው በደቡብ ክልል አገና ከተማ ነው፡፡ ይህም ትምህርት ቤት 18 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ በዚህ ትምህርት ቤት ካሉ ተማሪዎች የተወሰኑት የአዳሪ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ግንባታውም ለዚህ አገልግሎት እንዲመች ተደርጐ የተሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሦስቱም ትምህርት ቤቶች 1,100 ተማሪዎች በሰንሻይን ፋውንዴሽን ድጋፍ እየተማሩ ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ ለእነዚህ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መክፈት ብቻ ሳይሆን፣ ለእያንዳንዱ ተማሪ በየወሩ 200 ብር ይሰጣል፡፡ ዩኒፎርማቸውንና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎቻቸውን በሙሉ ይሟላል፡፡

ሪፖርተር፡- ፋውንዴሽኑ የሚጠቀምበት ገንዘብ ከሰንሻይን ሕንፃ ኪራይ ገቢ ጋር ተያያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለእነዚህ ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ወጪ ታደርጋላችሁ?

አቶ ሳሙኤል፡- ቋሚ በጀት አላቸው፡፡ በወር 680 ሺሕ ብር መድበናል፡፡ 8.1 ሚሊዮን ብር በዓመት የተመደበ ገንዘብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የፋውንዴሽኑ ሥራ ይቀጥላል፡፡ በቅርቡም ተመሳሳይ ሥራ የምንሠራበት አራተኛው ትምህርት ቤት በአማራ ክልል ለመገንባት ተዘጋጅተናል፡፡ ፋውንዴሽኑ በአዲስ አበባም አረጋውያንን የሚረዳበት ማዕከል እየገነባ ነው፡፡ ግንባታው እስከ 40 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ የአረጋውያን ማዕከሉ ከ400 እስከ 500 አረጋውያንን እንዲረዳ ይደረጋል፡፡ ይህ ማዕከል ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ የፋውንዴሽናችን ዓመታዊ ወጪ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ይደርሳል፡፡ ሁለተኛውን የአረጋውያን መንደር የመገንባት ውጥን አለን፡፡ በበጐ አድራጐት ሥራ ላይ ሌሎች ዕቅዶችም አሉን፡፡ መንግሥት በርካታ መሠረተ ልማቶችን እየሠራ ይገኛል፡፡ እኛ እዚህ አገር ንብረት ያፈራን ሰዎች እንዲህ ያለ ፋውንዴሽን አቋቁመን የዜግነት ግዴታችንን የመወጣት ኃላፊነታችንንም እንቀጥልበታለን፡፡ ይህ ተግባር በእኛ ብቻ እንዳይገደብ 170 ሺሕ ብር በማውጣት አንድ ጥናት አስጠንተን፣ ሌሎችም ኩባንያዎች ሊሳተፉበት የሚያስችላቸው ፕሮጀክታችንን ለሠራተኛና ለማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ ፕሮጀክት ዓላማው ከእናንተ ፋውንዴሽን ጋር ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ቢሆንም፣ እንዴት ይሆናል?

አቶ ሳሙኤል፡- ትልልቅ ኩባንያዎች በፋውንዴሽን መሳተፍ እንዳለባቸው እየተነጋገርንበት ነው፡፡ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ፕሮጀክቱ ሥራ እንዲጀምር ፍላጐት አለን፡፡ እኛ በተግባር አሳይተናል፡፡ ሌሎች ባለሀብቶች ቢመጡ 50 እና 60 ትምህርት ቤቶች ገንብቶ መማር ያልቻሉ ዜጐችን ማስተማር ያስችላል፡፡ 20 እና 30 የአረጋውያን መንደር ቢኖሩ ብዙዎችን መጦር የሚቻል በመሆኑ፣ በዚህ ኃላፊነት ውስጥ ሁላችንም አሻራችንን ማሳረፍ አለብን፡፡ ሌሎች ሲገቡ በምን መልክ ይሁን የሚለውን ለመመለስ ጥናቱ ያስቀመጣቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ እኔ የሕብረት ባንክ ባለአክሲዮን ነኝ፡፡ አሥር ሚሊዮን ብር አክሲዮን ቢኖረኝ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ብር ትርፍ አገኛለሁ ብል፣ ከዚህ ዓመታዊ ትርፍ ሁለት በመቶውን ማዋጣት ብችል 60 ሺሕ ብር አበረከትኩ ማለት ነው፡፡ ሌሎችም እንዲህ ቢያደርጉ ከሕብረት ባንክ በተዋጣው ገንዘብ ሕብረት ባንክ አንድ ትምህርት ቤት ኖረው ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት እንዲህ እያደረጉ ቢቀጥሉ ብዙ ትምህርት ቤት መገንባት ይቻላል፡፡ ሌሎችም ትልልቅ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ቢያደርጉ በዓመት ውስጥ 30 እና 40 ትምህርት ቤቶች መክፈት ይቻላል፡፡ ዕቅዱ ተግባራዊ ከሆነ ብዙ ለውጥ ይመጣል፡፡ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ከብዙዎቹ የባንከ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረን ተግባብተናል፡፡ በሐሳቡ ደስተኞች ናቸው፡፡ እንዲሁም አንዳንዶቹ ባንኮች ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ለሚደረግ ግብዣ የሚወጣውን ወጪ ለዚህ ለማዋል ይቻላልም የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ እኛም ይህ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲሆን ጉዳዩን ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ እናቀርባለን፡፡    

ሪፖርተር፡- ሰንሻይን የሪል ስቴት ግንባታውን አቀዝቅዟል ይባላል፡፡

አቶ ሳሙኤል፡- አልቀዘቀዘም፡፡ ከዚህ ቀደም የምንገነባቸውን የሪል ስቴት ቤቶችን ስንሸጥ የነበረው በማስታወቂያ በማስነገር ነበር፡፡ ቤት ገዥዎች እንዲመጡ ብዙ እናስተዋውቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ዝም ብሎ የሚመጣውን ቤት ገዥ ራሱ አልቻልነውም፡፡ አሁን አንድ ቦታ ብቻ ከ200 በላይ ቪላ ቤቶች አስረክበናል፡፡ 67 ፎቆች ሠርተናል፡፡ በዚህ ቤት ተረካቢዎቹ ደስተኞች ናቸው፡፡ እኛ በሁለት ሚሊዮን ብር ቤት ሠርተን ያስረከብነው ደንበኞች ዛሬ አሥራ አምስት ሚሊዮን ብር እስከመሸጥ ድረስ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ያለው ፍላጐት ከፍ ያለ በመሆኑ ዛሬ ጠዋት የአሥር ፎቅ ሽያጭ ስናወጣ ስድስት ሰዓት ላይ ሽያጩ ያልቃል፡፡ ስለዚህ አሁን ወጥተን ማስተዋወቁ ውስጥ ከገባህ ብዙ መሥራት አለህ፡፡ ማስተዋወቁን በማቆማችን ግን የቀዘቀዘ ይመስላል እንጂ የቀዘቀዘ ነገር የለም እየሠራን ነው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የምንገነባቸው በርካታ ሪል ስቴቶች አሉ፡፡ ይህ እያለ ደግሞ ማስተዋወቁ ብዙም ትርጉም የለውም ከሚል እንጂ አሁንም እየገነባንና እያስረከብን ነው፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ ብዙ ቤቶችን ገንብተናል፡፡ በገነባናቸው ቤቶች እስካሁን 1,198 አባወራዎች ገብተዋል፡፡ አሁን በምንገነባቸው ሪል ስቴቶች ደግሞ 2,056 አባወራዎች ይገባሉ፡፡ ደንበኞቻችንም በሥራችን ደስተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ሥራ የተወሰነ መዘግየት አለ፡፡ ይህም የሆነው የማጠናቀቂያ ዕቃዎች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መዘግየት ሊፈጠርባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተወሰነ መዘግየትም ቢኖር ሁሉም ቤታቸውን አግኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንቨስትመንት ውስጥ ካላችሁ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ቤቶች እየገነባችሁ ነው?

አቶ ሳሙኤል፡- በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ብዙ የምንገባቸው ቤቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቦታ ብቻ 108 ፎቆች እንገነባለን፡፡ በሌላ ቦታ 43 ቪላዎችን እንገነባለን፡፡ ሌሎችም ቦታዎች በተመሳሳይ የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ እነዚህ ግንባታዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ብዙ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ይህ የሪል ስቴት ልማት ደግሞ ከመንገድ፣ ከሌሎች የሕንፃና የሆቴል ግንባታዎች በተጨማሪ የምንሠራው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም አነስተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ሰንሻይን ደግሞ ትላልቅ ናቸው ከሚባሉት አገር በቀል ኮንትራክተሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አቅሙን ለማጐልበት ምን ያህል ሠርቷል? በተለይ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር የመወዳደር አቅምና ብቃትስ አለው ወይ?

አቶ ሳሙኤል፡- ብቃት ሲባል በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡ አንዱ ኩባንያህን በባለሙያዎች ማደራጀት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሠርተን ጨርሰናል፡፡ ሁለተኛው የብቃት መለኪያው የፋይናንስ ጉዳይ ነው፡፡ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር የምንወዳደረው ደግሞ በመንገድ ሥራ ነው፡፡ ሁለት ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች በአንዴ እንይዛለን፡፡ አንዱን ስንጨርስ አንዱን እናስገባለን፡፡ ከያዝናቸው ሦስት አራት ከሚሆኑ ፕሮጀክቶች ውስጥ ባለፈው ዓመት ሁለቱን ትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች አስረክበናል፡፡ ከአራት ወራት በኋላ በመሀል ሜዳ አካባቢ የምንገነባውን የመንገድ ፕሮጀክት እናስረክባለን፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ እነዚህን የሚተካልን ሌላ የመንገድ ሥራ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በአቅምህ የምትችለውን ያህል መሥራት አለብህ፡፡ ሥራ ባበዛህ ቁጥር ‘ኦቨር ማኔጅመንት’ ይመጣና ራስህን ‘ማኔጅ’ ማድረግ ያቅትሃል፡፡ እንዲህ እንዳይሆን አቅምህን ማወቅ አለብህ፡፡ አቅምህን ካላወቅክ ደግሞ ሦስት ነገሮችን ትጐዳለህ፡፡ በተለይ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት በጀት ተመድቦላቸው የሚሠሩ በመሆኑ በአግባቡ እንዲሠሩ ይፈለጋል፡፡ የአካባቢው ሕዝብ መንገዱን ይፈልጋል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ለአንተም ቢሆን የሚጠቅመው በወቅቱ ገንብተህ አስጨርስ ነው፡፡

ከውጭ ኮንትራክተር ጋር ከመወዳደር ጋር በተያያዘ ደግሞ አንድ የተለየ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የዓለም ባንክ ፋይናንስ የሚያደርገው የመንገድ ፕሮጀክት ጨረታ ሲወጣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች እንዳይወዳደሩ የሚያግዳቸው ነገር አለ፡፡ በዓለም ባንክ ፋይናንስ የሚደረገውን መንገድ ለመገንባት ለመወዳደር ብትፈልግ አንዱ መሥፈርት የኮንትራክተሩ ዓመታዊ ‘ተርን ኦቨር’ (የሚያገላብጠው ካፒታል) 200 ሚሊዮን ዶላር መሆን አለበት ሊል ይችላል፡፡ ይህ መሥፈርት ካለ ለውድድር አትቀርብም፡፡ ምክንያቱም ይህን ያህል ዓመታዊ ‘ተርን ኦቨር’ ያለው አገር በቀል ኩባንያ ላይኖር ስለሚችል ከጅምሩ ከውድድሩ ትወጣለህ፡፡ አታሟላም ትባላለህ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ካልኖሩ በስተቀር በሌሎች የግንባታ ሥራዎችና የአገነባብ ሥልት ልንወዳደር እንችላለን፡፡ አሁንም እኮ ከቻይና ኮንትራክተሮች ጋር እየተወዳደርን ነው፡፡ አንዳንዶቹንም ሥራዎች ያገኘነው ከእነሱ ጋር ተወዳድረን በማሸነፍ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ከፋይናንሱ ውጪ ወይም ዓመታዊ ‘ተርን ኦቨርህ’ ይህንን ያህል መሆን አለበት ተብሎ የሚቀመጠው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ብቻ፣ ከዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች ጋር የመወዳደር ዕድልህን ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በመንገድ ብቻ አይደለም፡፡ በሕንፃ ግንባታ ዘርፍም ቢሆን የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሳትፎ በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ ባንኮች ከ30 ፎቅ በላይ ሕንፃ ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እስካሁን ለአራት ወይም ለአምስት ባንኮች ሕንፃዎች ግንባታ ጨረታ አሸንፈው ሥራውን የወሰዱት የውጭ ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡ መንገዱ የራሱ የሆነ ችግር አለው ቢባልም፣ እንዲህ ያሉትን ሕንፃዎች ለመሥራት ያልቻላችሁበት ምክንያት ምንድነው? ለብቻ ካልቻላችሁ በጋራ ለመሥራት ለምን አልተሞከረም? እንደ ሰንሻይን ኩባንያ በበጐ አድራጐት ዘርፍ ላይ ያሳየውን የማስተባበር ሥራ በዚህ ላይስ ለምን አልሞከራችሁም?

አቶ ሳሙኤል፡- ትክክል ነህ፡፡ አሁን ያልከው ነገር አለ፡፡ አይኖርም አልልም፡፡ እኛ ራሳችን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለሕንፃ ግንባታ አስይዘናል፡፡ ለራሳችን ትልልቅ ግንባታዎች በእጃችን አሉ፡፡ ለምሳሌ አሁን ካሉት ሥራዎች ተጨማሪ የሕብረት ባንክን 30 ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት ብንገባ ተጨማሪ ነገር ይፈልጋል፡፡ ያለን ሥራ በቂ ስለሆነ አጣጥመን መሥራት አለብን በሚል ነው እንጂ ለውድድር ተጋብዘናል፡፡ ብዙዎቹ ባንኮች ጋብዘውናል፡፡ ራሳችን በሌሎች ሥራዎች ስለተወጠርን ነው እንጂ የመሥራት አቅምና ብቃት አጥተን አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በጥምረት ከሌሎች ኮንትራክተሮች ጋር በመሆን የመሥራቱ ጉዳይስ አልተሞከረም?

አቶ ሳሙኤል፡- ይቻላል፡፡ ግን ኮንትራክተሮች በጥምረት ሆነው ለመሥራት ገና ብንሆንም በሒደት እየመጣ ነው፡፡ አሁን ግን አልደረስንበትም፡፡ በአክሲዮን ተደራጅቶ መሥራት እየተለመደ ስለሆነ በቀጣይ ‘በጆንይንት ቬንቸር’ ወይም በጥምረት የመሥራቱ ነገር መምጣቱ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሆቴል ኢንዱስትሪ ውጪ ሌላ ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት አይቻልም ነበር? የሆቴሉን ሥራ የበለጠ አተኩራችሁበታል፡፡ ከግንባታ ወደ ሆቴል እየተገባ ነው ማለት ነው?

አቶ ሳሙኤል፡- ሁለት ዓይነት ኢንዱስትሪ ነው ያለው፡፡ አንዱ ኢንዱስትሪ ጭስ እያጨሰ ገንዘብ የሚያመጣ ነው፡፡ ሌላው ጭስ ሳያጨስ የሚያመጣ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፎች መንግሥት የሚፈልጋቸው ሁለት ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ኢንዱስትሪ ብዙ የሰው ኃይል ይይዛል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ሁለተኛ ያመረትከውን ልከህ የውጭ ምንዛሪ ታመጣለህ፡፡ ሦስተኛ ከውጭ የምታመጣውን ነገር ትቀንሳለህ፡፡ ሦስቱም ነገሮች ኢንዱስትሪ ላይ ብዙ ጥቅም አላቸው፡፡ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ላይ ስትሄድ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያመጣል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ምሳሌ አሁን ሥራ የጀመረው ሆቴል አንድ ትልቅ ፋብሪካ ለመገንባት ሊያስወጣ ከሚችለው በላይ ኢንቨስትመንት ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እንደኛ ያለ ሆቴል በወር ከ600 ሺሕ ዶላር እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪን ግኝት ከጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ማግኘት ያስችላል ማለት ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ወጪውን ሲታይ ደግሞ አንድ ትልቅ ሆቴል መገንባት አንድ ፋብሪካ ግንባታ ወጪ ጋር ሊበልጥ  እንደሚችልም እገምታለሁ፡፡

ግንባታው በዓለም አቀፍ መሥፈርትና ደረጃ መሠረት በመሆኑ የግንባታ ወጪው ከፍተኛ ነው፡፡ ወደዚህ ዘርፍ የሚገቡት አቅማቸውን ያጠነከሩ ካልሆኑ በስተቀር ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ማሪዮት ሆቴል በአሜሪካ ለመገንባት አሥር ወይም ሃያ ባለአክሲዮኖች በጋራ ሆነው የሚሠሩት እንጂ በግልህ የምትሠራው አይደለም፡፡ የእኛ የግላችን አለ፡፡ ባንክ ደግሞ ከጐናችን አለ፡፡ ሥራው ቀላል ባይሆንም ገብተንበት እየሠራን ነው፡፡ ከገባንበት ካልቀረ ደግሞ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራው ይገባል፡፡ ይህንን ስንል ግን በኢንዱስትሪዎች ውስጥ አልገባንም ማለት አይደለም፡፡ ትናንሽ የሚባሉና ለኮንስትራክሽን ግንባታ የሚሆኑ ምርቶችን የማያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ግን አሉን፡፡ አልሠራንም አይደለም፡፡ እነሱን ከፍተን እየሠራን ነው፡፡ ሆቴል ደግሞ በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ዘርፉ ብዙ ያንቀሳቅሳል፡፡ ከመንግሥትም ገቢ አንፃር ከፍተኛ ታክስ የሚሰበሰብበት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅምን አይተን የገባንበት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት ይመስለኛል በድርጅቱ ረዥም ጊዜ ላገለገሉ ሠራተኞች ቤት ለመገንባት ቃል ገብታችሁ ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ ከሠራተኛው፣ ከኩባንያውና ከባንክ በሚገኝ ብድር ቤቶች ለመገንባት የቀረፃችሁት ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?

አቶ ሳሙኤል፡- ሰንሻይንን ከሌላው ለየት የሚያደርገው አንድ ነገር አለ፡፡ ኩባንያችን የሚያምንበት አንድ መርህ አለው፡፡ ባለቤቶቹ ወይም ድርጅቶቹ በአንድ እጅ አያጨበጭቡም፡፡ ሁለት እጅ ሲገናኝ ነው ድምፅ ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ስለዚህ በየአምስት ዓመቱ ዓመታዊ በዓላችንን ስናከብር ለሠራተኞች ቤት እንሸልማለን፡፡ 25ኛ ዓመታችንን ስናከብር ከ30 ላላነሱ ሠራተኞች ቤት ሸልመናል፡፡ ይህ ተግባራችን ይቀጥላል፡፡ 30ኛ ዓመታትን ስናከብር የሸለምናቸው አሉ፡፡ በተለየ መንገድ ሠራተኞቻችን የቤት ባለቤት ለማድረግ አንድ ፕሮጀክት ቀርፀናል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ላገለገሉ ሠራተኞች 30/40/40 በሚባል ፕሮግራም እንዲጠቀሙ ዕድል ሰጥተናል፡፡ ይህ ፕሮጀክታችን ከቤት ግንባታ ወጪ 30 በመቶ ከሠራተኛው፣ 40 በመቶ ከሰንሻይን፣ 40 በመቶ ከባንክ በሚገኝ ብድር አድርገን የምንሠራው ነው፡፡ ይህንንም የምናደርገው ሠራተኛው ድርጅቱን አፍቅሮ ደስተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ነው፡፡

ይህንን በማድረጋችንም የሠራተኛ ፍልሰት የለም የሚባልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የሠራተኛ ፍልሰት አንድ በመቶ አለ ማለትም ይከብደኛል፡፡ 30/40/40 ፕሮጀክታችን እየተገነባ ነው፡፡ በዚህ የታቀፉና የሚመለከታቸው ሠራተኞች ስምምነት ፈርመው ቤቱ እየተገነባላቸው ነው፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤቱ ተገንብቶ ያልቅላቸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ከጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ ክስ ከፍተኛ ማኔጅመንት ድረስ ላሉና ከ20 ዓመታት በላይ ላገለገሉ ሠራተኛ የፈጠርነው ዕድል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ፕሮግራም የታቀፉት ምን ያህል ሠራተኞች ናቸው?

አቶ ሳሙኤል፡- ወደ 360 አካባቢ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰንሻይን አሁን ያለበት ደረጃ እንደሚደርስ አስበው ያውቃሉ?

አቶ ሳሙኤል፡- እኛ ሰንሻይንን ስናቋቁም ትልልቅ ግንባታዎች አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ ያኔ እኔ የሚያፈስ ጣራ እየፈለግሁ ስለምጠግን ‘ሳሙኤል ጣራ’ ነበር የምባለው፡፡ ከዚያ ጅማሬ አንፃር አሁን የደረስንበት ደረጃ ይደረሳል ተብሎ ማሰብ ሊከብድ ይችላል፡፡ ሥርዓቱ የፈጠረው ዕድልና አሁን ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ እኛን ጠቅሞናል፡፡አሁን ለደረስንበት ደረጃ ያበቃን አንዱ ትልት ነገር የአገሪቷ ዕድገት ነው፡፡ የመንገድ ግንባታ ሲባል ግንባታውን አውራ ጐዳና ይሠራዋል እንጂ የግል ዘርፉ አይሠራውም ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት ገባበት፡፡ ቅድሚያ ክፍያ እከፍላለሁ፣ ማሽን ከቀረጥ ነፃ አስገባለሁ ሲል ይህንን ዓይተን ገባን፡፡ ይህ ጠቅሞናል፡፡ አሁን ለደረስንበት ደረጃ አብቅቶናል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ የዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር እንሠራለን፡፡ የመንግሥት ዕቅድ ጠቅሞናል፡፡ ይህ ዕቅድ ለእኛም ይደርሳል፡፡ አሁንም እየቀጠለ ነው፡፡ ሥርዓቱ የፈጠረው ነው፡፡ ለምሳሌ የትኛው አገር ላይ ነው ይህንን ያህል ኮንዶሚኒየም እየተሠራ ያለው? ብዙ ቦታ ተዟዙረን አይተናል፡፡ ቻይና ካልሆነ በቀር ሌላ አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ የሠለጠኑት አገሮች ገንብተው ጨርሰው ሊሆን ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ እንዲህ ዓይነት ግንባታ አይታይም፡፡ ይህ እንደኛ ላለው እጅግ ጠቅሞናል፡፡ ብዙ እንድንሠራና ብዙ እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ አሁን የደረስንበት ዕድገት መሠረት ሥርዓቱ ያመጣቸው ዕቅዶች ውጤት ነው፡፡ ነገም ከዚህ የበለጠ ለማደግ እንሠራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...