Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ቢዝነሱ ሽርሽር እንዳይሆን

  የትኛውም አገር ዕድገትን ይፈልጋል፡፡ ዜጐች መለወጥና መበልጸግ ይሻሉ፡፡ አገርንና ዜጐችን ከድህነት ለማውጣት ሁሉም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፈው ይታትራሉ፡፡ አቅምን ያገናዘበ ዕቅድ አውጥተው መንቀሳቀሳቸውም የዓለማችን አገሮች የተለመደ ተግባር ተደርጐ ይወሰዳል፡፡

  ዛሬ በምንኖርባት ዓለም ደግሞ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት መድከምና መወዳደር ግድ ይላል፡፡ በተለይ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪን ለማጐልበት ብሎም በርካታ ዜጐችን ሊቀጥሩ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ያለው ምኞት የጠነከረም ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማምጣትም አገሮች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ሲሠሩም ይታያል፡፡ የተሻለ ዕድል ለመስጠትም የእኔ ይሻል የእኔ በማለት ይሠራሉ፡፡

  አገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ሌላው መንገድ ደግሞ ኢንቨስትመንትን ወደ አገር በመሳብ፣ ከድንበር ዘለል ኩባንያዎች ጋርም በጥምረት መሥራት ነው፡፡ ወደ አገር የሚገባውን ካፒታል ለማሳደግ ደግሞ አገርን በሚገባ ማስተዋወቅ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

  በመሆኑም በንግድና በኢንቨስትመንት ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች በግልም ሆነ በጋራ ገበያ ማፈላለግ ግድ ይላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥትም የራሱን ሚና የመጫወት ግዴታ ስላለበት፣ የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ ገበያ የማፈላለጉ ሥራ ከአገር አገር መዞርን ይጠይቃል፡፡ በተመሳሳይ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ እነዚህ ኩባንያዎች የተሻለ ዋጋ እንደሚሰጡ በማሳመን የውጭ ምንዛሪን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በጥራት አምርቼ ማቅረብ እችላለሁ በሚል ማግባቢያ ገበያውን ለማግኘት መጣር አለባቸው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ገበያውን ለማግኘት ወደ ውጭ የሚደረጉ ጉዞዎች እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ጥያቄው እነዚህን ጉዞዎች በአግባቡ ተጠቅመናል ወይ? የሚለው ነው፡፡ በግል፣ በተቋማትና በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ቢዝነስ ነክ ጉዞዎች ይካሄዳሉ፡፡ እንዲህ ያሉ የቢዝነስ ጉዞዎች ደግሞ በምንም መልኩ ቢሆን አንድ ነገር የሚገኝባቸው ሊሆኑ ይገባል ተብሎ ይታመናል፡፡

  የበረታ ነጋዴ በራሱ መንገድ እየተጓዘ ገበያ ለማምጣት ይጥራል፡፡ ከዚህ ጉዞ ይህንን አመጣለሁ፤ ለአገሬም እንዲህ ሊጠቅም ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት ይኖረዋል፡፡ በተቋምም ደረጃ በሚደረግ ግብዣ የንግድ ግንኙነት የሚፈጠርበት አጋጣሚዎች ሊያስገኙ የሚችሉት ዕድል አለ፡፡

  እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ ተቋማት ደግሞ የንግድ ትስስሮችን ሊፈጥሩ የሚያስችሉና ወደተለያዩ አገሮች ሊያስጉዝ የሚችል በርካታ ዕድሎች አሉዋቸው፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች በሚፈጥራቸው ግንኙነቶችም የንግድ ልዑካንን ይዞ የመጓዝ ልምዳቸው ከሌላው የተሻለ ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የንግድ ልውውጥ ስምምነት ለመፈራረም ከሁሉም በላይ የተሻለ ዕድል ያለው ደግሞ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ወደ አንድ አገር ሲጓዙ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ጉዞ ከልዑካን ቡድኑ ጋር የሚጓዙት የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ቁጥራቸው ልቆ በሚታይበት አጋጣሚ ጥሩ የገበያ ዕድል ሊያስገኝ እንደሚችል አይጠረጠርም፡፡

  ምክንያቱም ነጋዴዎቻችን ጉዞ ካደረጉበት አገር ነጋዴዎች ጋር ልምድ ከመለዋወጣቸውም ባሻገር የቢዝነስ ሽርክና እንዲፈጥሩ ስለሚያስችል ነው፡፡ ሽርክና እንዲፈጠር ማድረግም እንዲህ ካሉ የውጭ የቢዝነስ ጉዞዎች ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከኢትዮጵያ የሚላኩ ምርቶች ገዥ እንዲያገኙ ለማሳመን የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

  ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ጉዞዎች አገር ጠቅመዋል ወይም ነጋዴዎቻችን ተጠቅመውበታል ለማለት አይቻልም፡፡ በዓመት ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ልዑካን የሚታደሙበት የንግድ ጉዞዎች ምን ያህል ውጤት አምጥተዋል? ተብሎ ቢፈተሽ፣ ውስጡን ለቄስ ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ልዑካን ሄደው ከጉዞዋቸው ይዘው የተመለሱት ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

  ይህ ከሆነ ደግሞ ነጋ ጠባ የሚደረጉ ጉዞዎች ምክንያት አልባ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ሊወስደን ይችላል፡፡ ተወደደም ተጠላ ለንግድና ኢንቨስትመንት በሚደረጉ ጉዞዎች ውስጥ አንድ ቡና ላኪ ከሄደ ቢያንስ ቡናውን ሊገዛው የሚችል አዲስ ደንበኛ ፈጥሮ ሊመጣ የሚችልበትን ጥረት ማድረግ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጉዞው ከሽርሽር የተለየ አይሆንም፡፡

  በሰሊጥ ወይም በቆዳ የተሠሩ የኢትዮጵያ ምርቶች እንዲሸጡና በተጓዘበት አገር ይህንን የሚገዛ አዲስ ደንበኛ ለመፍጠር ያልቻለ፣ ጉዞዎችን ደጋግሞ ማድረጉም ትርጉም የለውም፡፡ በሽርክና ሊሠራ የሚችልበት መንገድ ማመቻቸት ያልቻለ ኢንቨስተርም፣ ለምን በተደጋጋሚ ለውጭ ጉዞ እንደሚመረጥ ሊጠየቅ ይገባል፡፡

  ከከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ጋር ሄዶ በርካታ ገዥዎች ያሉበት ቦታ መሃል ተቀምጦ አንድም ቁም ነገር ሳይፈጥር ሽቶና ሸሚዝ ገዝቶ የሚመጣ ከሆነ ነገሩ ትርጉም የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውጤት አልባ ጉዞዎች እየተደጋገሙ ስለመሆኑ በሰፊው መነገር ከጀመረ የቆየ ሲሆን፣ አሁን አሁን እንዲያውም እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ባሉ ተቋማት ውስጥ የውጭ ጉዞ እንደ ጥቅም እየታየ አንዳንዶች እየተሻኮቱበት ነው መባሉም ለጆሮ አይጥምም፡፡ እንዲያውም የውጭ ጉዞዎች ላይ የተከፈለኝ አበል አነሰኝ ብለው የሚያጉመርሙ ‹‹ነጋዴዎች›› አሉ ከተባለ፣ ስለእውነት እነዚህ ሰዎች ነጋዴዎች እንዳልሆኑ መገመት አያቅትም፡፡ የውጭ ጉዞዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል እየተገኘባቸው ላለመሆኑ ደግሞ የራሱ ምክንያት እንዳለ ይሰማኛል፡፡ አንዱና ዋነኛው እንዲህ ባሉ ጉዞዎች የሚጓዙ የንግድ ሰዎች ምርጫ የራሱ የሆነ ሥርዓት የሌለው ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ወደ አንዱ አገር በሚደረግ ጉዞ ማን ከየትኛው ዘርፍ አዲስ ነገር ይፈጥራል የሚል እሳቤ አለመኖር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡

  የንግድ ልዑካንን የመመልመል ዕድል ያላቸው አንዳንድ ምክር ቤቶች፣ ወደ አንድ አገር በሚደረግ ጉዞ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ከማሰብ ይልቅ በወዳጅነት የሚያደርጉት ምርጫ ከውጭ ጉዞ ሊገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም ኮሳሳ አድርጐታል፡፡

  እንዲያውም በአንዳንድ ተቋማት የጉብኝትና የቢዝነስ ግብዣ ሲደረግ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተቋማትና ብርቱ የንግድ ሰዎች ገሸሽ በማድረግ፣ መራጮቹ የፈለጉትን በመምረጥ ነገሩን በውለታ ለማቆየት የሚጥሩም አሉ፡፡    

  ስለዚህ የጉዞ ፕሮግራሞች ጥቅም ያላቸው አገራዊ ኢንቨስትመንት ዕድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ሰዎችን ማሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ቢያንስ አገሪቱን በሚገባ ማስተዋወቅ የሚችሉ ኢንቨስተሮችን ማካተት አለበት፡፡ የሚመለከተው አካል ከጉዞ መልስም ጉዳዩን በደንብ እስካልተከታተለው ድረስ ውጤት የሌላቸው የቢዝነስ ጉዞዎች ከሽርሽር የማይለያዩ ይሆናሉ፡፡

  ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ ሌሎች ተቋማትም ከሌሎች አገሮች አቻ የንግድ ተቋማት ጋር ስምምነቶች ካደረጉ በኋላ፣ ስምምነቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተከታትሎ ማስፈጸም ካልተቻለ በቀር ፊርማ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቶች ነጋ ጠባ ከአቻ ማኅበራት ጋር የሚፈራረሙት ወረቀት ፋይል ማሳበጫ እንዳይሆን ያሻል፡፡ በአጭሩ የውጭ ጉዞዎች ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ አገርና ምርትን በማስተዋወቅና አዲስ ገበያ ለመፈጠር ያለውን ከፍተኛ ጥቅም በትክክል ለመተግበራቸው ግልጽ አሠራር ይኑር፡፡