Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሁለተኛ ጊዜ የተሰናዳው የሆቴል ፎረም የውጭ ኢንቨስትመንት ሊያመጣ አልቻለም

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዙ ተብሎለታል፡፡ የዓለም የሆቴልና የመስተንግዶ አውራዎችን በማምጣት ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር አገናኝቷል፡፡ የውጭ ብራንዶችን ለአገር ውስጥ በማስተዋወቅም የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ባለድርሻ ሆኗል፡፡ የፎረሙ መምጣት ግን ብራንዶችን የማምጣቱን ያህል የውጭ ባለሀብቶችን ራሳቸው እንዲገነቡና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከማስቻል ግን ተሳንፏል፡፡

ስብሰባው ባለፈው ዓመት በሸራተን አዲስ ሲካሄድ ስድስት የውጭ ብራንድ ሆቴሎች እዚህ ለመምጣት ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ስምምነት በማድረጋቸው ትልቅ ውጤት ታይቶበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም የሆቴሎቹን የግንባታና የኢንቨስትመንት ወጪ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲሸፍኑ፣ የውጭ ብራንዶች ግን ሆቴሎቹን በማስተዳደር ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ ውጭ አንድም የውጭ ሆቴል በራሱ ኢንቨስት አድርጎ ወደ ሆቴልና ቱሪዝም ገበያው የገባ የለም፡፡ በዚህ ዓመትም ተመሳሳዩ ተከናውኗል፡፡ የውጭ ሆቴሎች በማኔጅመንት ስምምነት ለመሥራት ከመምጣት በቀር ኢንቨስት ለማድረግ የመጡ አልታዩም፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንት በሆቴል መስክ አልታየም ለሚለው የሚቀርቡት ምክንያቶች አንድም ከመንግሥት አሠራር ጋር አንድም በአገሪቱ ላይ ካላቸው አመኔታ ጋር ተያይዟል፡፡ ከመንግሥት ጋር በተያያዘ ከሚነሱት ውስጥ የቪዛ  ሥርዓቱ ቅልጥፍና አንዱ ሆኗል፡፡ መንግሥት በቪዛ አሰጣጥ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ወደዚህ ለሚመጡ ጎብኝዎች ወዲያውኑ ቪዛ የመስጠት ወይም ‹‹ቪዛ ኦን አራይቫል›› የሚባለውን አሠራር መተግበሩ በብዙ አስመስግኖታል፡፡ ሆኖም ይህም አሠራር ቢሆን ቀርፋፋና ሰዓታት የሚፈጅ ሆኖ እንዳገኙት የሚገልጹ የፎረሙ ታዳሚዎች፣ ይህንንም ሊመለከተው እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዴቪድ ሃርፐር ሆቴል ፓርትነርስ አፍሪካ ለተባለ አማካሪ ተቋም ለሆቴሎች የንብረት አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ ሃርፐር እንደሚያብራሩት ኢትዮጵያ በሆቴል መስክ ትልቅ ተስፋ ካላቸው አሥር አውራ አገሮች ውስጥ ትመደባለች፡፡ በአገሪቱ ያለው ዝቅተኛ የብራንድ ሆቴሎች ቁጥር (ሒልተን፣ ሸራተን፣ ራዲሰን፣ ጐልደን ቱሊፕና ማሪዮት ብቻ ናቸው) አኳያ አገሪቱ በርካታ ብራንድ ሆቴሎችን መገንባት ይጠበቅባታል፡፡ የብራንድ ሆቴሎች ካለው የቱሪዝም ፍሰት አንፃር ሲታይም ብዙ መስፋፋት የሚጠበቅበት እንደሆነ የሚገልጹት ሃርፐር፣ ይህም ሆኖ የውጭ ባለሀብቶች የራሳቸውን ገንዘብ በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ አለማፍሰሳቸው ከብዙ አቅጣጫ እንደሚታይ ይገልጻሉ፡፡  ከቪዛ አሰጣጥ ባሻገር የውጭ ባለሀብቶች ያገኙትን ገንዘብ ወደ አገራቸው መልሰው የሚወስዱበት አሠራር ግልጽነት የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመምጣት ሊገቱ ከሚችሉት መካከል ተመድቧል፡፡ የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ቃል አቀባይ ዴቪድ ታርሽ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ የውጭ ኢንቨስተሮች ከማይመጡባቸው ምክንያቶች መካከል የፖለቲካ መረጋጋት፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ አብሮ ሊሠራ የሚችል ትክክለኛ አጋር ማግኘት ከፈተናዎች መካከል እንደሚመደቡ ገልጸው ነበር፡፡

ይህም ቢባል ግን ኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ በመሆኗ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንዳሏት ሃርፐር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትልቅ አቅም አለ፡፡ የሆቴሎች አቅርቦት ዝቅተኛ ነው፡፡ ለሆቴሎች ተስማሚ የኢኮኖሚ መሠረት ልማት አለ፤›› ያሉት ሃርፐር፣ የውጭ ሆቴሎች በአስተዳደር መስክ ቀድመው መምጣታቸው መልካም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የእነሱ ውጤታማነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ያስከትላል ብለው ይገምታሉ፡፡

የአገር ውስጥ ኢንቨስትሮች በኢንቨስትመንቱ መስክ ነቃ ማለታቸውም ብራንድ ሆቴሎች የሚያመጡት እሴት እንዳለ በማመን ነው የሚሉት ሃርፐር፣ እያንዳንዷ ኢንቨስት የተረገች ዶላር ስምንት ተጨማሪ ዶላር ይዛ እንደምትመጣ ጥናቶችን ዋቢ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢባልም ግን አንድም የውጭ ኢንቨስተር እስካሁን በተደረጉት የሆቴል ስምምነቶች ውስጥ ገንዘብ ይዞ በመምጣት ለመሥራት የተዋዋለ የለም፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በኢትዮጵያ በአብዛኛው የኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ ያተኮረ የቱሪስት ፍሰት የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ለመዝናናት፣ አገር ለመጎብኘት፣ ለቢዝነስ ሥራዎች በሚመጡ ጎብኝዎች ዘርፉን በማስፋፋት የሆቴሎችን ገቢ ከማሳደግ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማስፋፋት በመሆኑ፣ በዚህ መስክ መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግ የሚመክሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በፎረሙ ታድመዋል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባቱ፣ ከቀውሱ ቀደም ብሎ የቻይና መንግሥት የመገበያያ ምንዛሪ ለውጥ ማድረጉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የግብርና ሸቀጥ ላይ የወጪ ንግዳቸውን ጥገኛ ባደረጉ አገሮች ላይ ተፅዕኖ ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡ በወጪ ንግድ ላይ ምንም ጥርጥር ሳይኖር በገቢም በመጠንም ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደሚኖር ተንብየዋል፡፡ የተወሰኑ የአፍሪካ አገሮችም የበጀት ቅናሽ ለማድረግ መገደዳቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ በመሆኑ በቱሪዝም መስክ ላይ ትኩረት ማድረግ አማራጭ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ እንደሚሆን ምክር ተለግሷል፡፡

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ ለአምስተኛ ጊዜ የተሰናዳው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን እንግሊዝ ባደረገው ቤንች ኤቨትንስ በተባለ ተቋም የተዘጋጀ ነው፡፡ ቤንች ኤቨንትስ ከአፍሪካ ባሻገር በአውሮፓ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ የቱሪዝም፣ የሆቴልና የሬስቶራንት ኢንቨስትመንቶች ላይ ያነጣጠሩ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች