Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት ሰሞነኛ ትኩሳት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለመታደም የበረራ ቲኬት ቆርጠዋል፡፡

የዓለም ባንክ የዘንድሮው ዓመታዊ ጉባዔውን በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ ያካሂዳል፡፡ የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በመጣ ቁጥር የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ፕሬዚዳንቶች ለተሳትፎ ይጓዛሉ፡፡ የባንክና የኢንሹራንስ ኃላፊዎች ብቻም ሳይሆኑ፣ የፋይናንስ ተቋማቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችም ስብሰባዎችን ይታደማሉ፡፡ በዘንድሮው የዓለም ባንክ ስብሰባ ዋዜማ ሰሞን ከኢትዮጵያ የግል ኢንሹራንሶችና ባንኮች መንደር ውስጥ የገባ አዲስ ክስተት ታይቷል፡፡

የዓለም ባንክ ስብሰባ ሊካሄድ አንድ ሳምንት ሲቀረው ከብሔራዊ ባንክ ተከታትለው የወጡት መመርያዎች የበርካቶቹን ተቋማት ስሜት ሰቅሏል፡፡ በተለይ በመልካም አስተዳደር ላይ የወጣው ጠንካራ መመርያ እንዴት ይፈጸማል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሆኗል፡፡ ባንኮች ይተዳደሩበታል የተባለው መመርያ በተመሳሳይ በኢንሹራንሶችም ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ መመርያ አውጥቷል፡፡

17ቱ የግል ኩባንያዎች የሚገዙበት ይህ መመርያም ሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መከወን አለባቸው የተባሉትን አሠራሮች በግዴታ እንዲተገብሩ የሚያስገድደው ይህ መመርያ፣ የፋይናንስ ተቋማት በመልካም አስተዳደር ሥርዓት እንዲመሩ ለማስቻል የወጣ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ በግልጽ ቢያስቀምጥም፣ በመመርያው ይፈጸሙ የተባሉት ዝርዝር ጉዳዮችን ለመተግበር ግን ከባድ እንደሆነ  የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ከግል የመድን ዋስትና ሰጪዎችና ተያያዥነት ካላቸው ሕጐች ጋር ተገናዝቦ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚገኙ የመድን ዋስትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ ከመስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በጥብቅ ተግባራዊ እንዲደረግ የተቀረፀው መመርያ ይፋ ተደርጓል፡፡

የመድን ሥራ ዋስትና ሰጪ ድርጅቶች የመልካም አስተዳደር መዋቅራዊ ግዴታዎችን ብሔራዊ ባንክ ካወጣው መመርያ ጋር ትይዩ አድርጎ ከመቅረፅ በተጨማሪ የሥነ ምግባር ደንቦችንም በማውጣት ተገዢ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመድን ዋስትና ኢንዱስትሪያዊ ደኅንነት፣ የባለአክሲዮኖች፣ የደንበኞችና የባለድርሻ አካላትን ፍላጐት ያማከለ አገልግሎት በማስፈን ረገድ መመርያው ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

በባንኮች መመርያ ላይ ከወጣው ሕግ አንፃር በመድን ሰጪዎች መመርያ ላይ የሕግ ጥሰት የፈጸመ ዳይሬክተር ወይም ባለአክሲዮን ብድርንና የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በተመለከተ ከተገለጸው በስተቀር የተቀሩት አንቀጾች በሙሉ ተፈጻሚ ይሆኑበታል፡፡

በኢንሹራንስ መመርያው ላይ ከማንኛውም ባለድርሻ አካል የሚቀርቡ የጉዳት ካሳ ክፍያ ጥያቄዎችና የመድን ሰጪውን ቋሚ ንብረቶች፣ ቁሳዊና ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑትን ጨምሮ ግብይቱ ከተፈጸመ ጀምሮ ባሉ 15 ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ በዳይሬክተሮች ቦርድ ዕውቅና ያለው የግብይቱ ስም፣ ዓይነቱ፣ የገንዘብ መጠኑ በዝርዝር ተገልጾ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ከመድን ተቋማት ይጠበቃል፡፡ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የግብይቶች መረጃ በቦርዱ ታውቀው በሕጋዊ መስፈርቶችና በመድን ሰጪው ደንብና አፈጻጸም መርሃ ግብር መሠረት ስለፈጸማቸው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም ይደነግጋል፡፡

የመድን ዋስትና ሰጪዎች የአፈጻጸም ምዘና መሥፈርቶች ቢያንስ የመድን ሰጪው ከሕጎች፣ ከደንቦችና ከፀደቁ ፖሊሲዎች አኳያ ያስመዘገበው አፈጻጸም ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡  በውስጥና በውጭ የኦዲት ምርመራዎች እንዲሁም በሥጋት አስተዳደር የተለዩ ውጤቶች፣ የማሻሻያ ሐሳቦችና አፈጻጸማቸው፣ የመድን ዋስትና ሰጪው የሥጋት አስተዳደር ገጽታ ከሥጋት መቋቋም አቅም መጠኑ አንፃር የብሔራዊ ባንክ ደንቦችንና የቁጥጥር መርሆዎችን በተመለከተ ያከናወናቸው ወቅታዊ አፈጻጸሞችም ለገዢው ባንክ ሪፖርት መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አስተዳደራዊ የማሻሻያ ሐሳቦች በጊዜ ሰሌዳቸው፣ በጥረትና በስኬት ደረጃቸው መሠረት ተቀምረው ሪፖርት ከመደረጋቸው አንፃር፣ መሠረታዊ (ቁልፍ) የቢዝነስ ሥራና ምጣኔ ሀብታዊ የአፈጻጸም መለኪያዎች ከታቀዱ አፈጻጸሞችና፣ የሒደት ውጤቶች፣ ከተመሳሳይ ቡድኖች ጋር ያለው ንጽጽር በመቶኛ ተሰልቶ ሊቀርብ እንደሚገባ በመመርያው ተቀምጧል፡፡

በኢንሹራንስም ሆነ በባንኮች ላይ የወጡት መመርያዎችን ተከትለው በቅርቡ ይፋ የተደረጉት መመርያዎች ለዓለም ባንክ ስብሰባ የሐሳብ ስንቅ ይዘው እንዲጓዙ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችን አስገድደዋል፡፡

‹‹የኮርፖሬት ገቨርናንስ›› ወይም መልካም አስተዳደርን የሚመለከተው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ያካተታቸውና ሊፈጸሙ ይገባል ያላቸው ክዋኔዎች በእርግጥም አስፈላጊ ስለመሆናቸው ብዙዎች ቢያምኑም፣ በተቋማቱ ኃላፊዎች ዘንድ ግን መመርያው ብዙ የሥራ ጫና የሚፈጥርና ፋታ የሚያሳጣ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡

በየተቋማቱ እንዲቋቋሙ የሚፈለጉት ኮሚቴዎች ቁጥር መብዛት ሊያስከትል ከሚችለው ወጪ በላይ አንዱ ከሌላው የሚያቆላልፍ ነው ተብሏል፡፡ አነስተኛ አክሲዮን ያላቸውና በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ይታይ የነበረው ክፍተት ወደፊት በዚህ መመርያ ይስተካከላል ከሚል መነሻ ጠቀሜታው እንደሚጎላ እምነት አላቸው፡፡

መመርያዎቹ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የቦርድ አባላትን እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሥራ የሚያበዙ ናቸው ተብለው ይተቻሉ፡፡ መልካም የኩባንያ አመራርን ማምጣት አስፈላጊ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የብሔራዊ ባንክ አንቀጾች ጫና የሚፈጥሩና ለመተግበርም አስቸጋሪ ናቸው የሚሉ የባንክና የኢንሹራንስ አመራሮች ጥቂት አይደሉም፡፡

በተለይ የግዴታ መቋቋም አለባቸው ከተባሉ ሦስቱ ኮሚቴዎች ውስጥ እንዲካተቱ የሚፈለጉ የፋይናንስ ተቋማት አባላት ቁጥር በድምር ሲታይ ከቦርድ አባላቱ ብዛት ከሦስት እጅ በላይ ሲሆን፣ ለእነዚህ የኮሚቴ አባላት የሚከፍለው ለቦርድ አባላት በመከፈል ላይ ከሚገኘው ዓመታዊ ክፍያ ያላነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ በመሆኑም ባንኮቹም ሆኑ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለኮሚቴ አባላት ብቻ ከፍተኛ ወጪ ሊያወጡ እንደሚገደዱ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲሱ መመርያ መሠረት ከቦርድ አባላት የበለጠ ለተለያዩ የኮሚቴ አባላትና ለምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈል መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ለቦርድ አባልነት የሚመረጡ አባላትን ለመሰየም ከአንድ ዓመት ቀድሞ እንዲቋቋም ይጠበቃል፡፡

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በመመርያዎቹ የቦርድ አባላት በተለያዩ የትራንዚት ዘርፍ የተሰባጠሩ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በመመርያው አባላቱ ከአምስት በላይ የተለያዩ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን የጾታ ስብጥርም ያካተተ እንዲሆን መደረጉ አሳሳቢ ነው ይላሉ፡፡ በመመርያው የተጠቀሱትን የትምህርት መስኮች የሚያሟላ የኮሚቴ አባል ካልተገኘ እንዴት ሊኮን ነው? ሥራውን በአግባቡ ሊያሠራ ይችላል የተባለለት የትምህርት ዓይነት ካልተገኘና የቦርድ አባላት ምርጫ በትምህርት ኮታ ድልድል እንዲሆን ማስገደድ፣ ሊሠሩ የሚችሉና አቅሙ ያላቸውን ሰዎች ሊያስቀር ይችላል የሚል ሥጋታቸውን የሚገልጹም አልጠፉም፡፡

አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች በመመርያው አስፈላጊነት ላይ ያምናሉ፡፡ መመርያው እንዲተገበር የተፈለገበት መንገድ መወሳሰቡ ግን ያሳስባቸዋል፡፡ አነስተኛ አክሲዮን ያላቸው ግን መመርያው ዘግይቷል ይላሉ፡፡

የባንክ አሠራሮችን በቅርብ የሚከታተሉ በመካከለኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ኃላፊዎች በመመርያው አስፈላጊነት ላይ በብርቱ ያምናሉ፡፡ በተለይ በብድር አሰጣጥ ላይ ያለው ክፍተት እንዲህ ባለው መመርያ ካልተገደበ አደጋው ይበዛል ይላሉ፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ብድርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በትውውቅና ቅርርብ የሚሰጥበት ነበር፡፡ ትልልቅ ባለአክሲዮኖች በባንኩ ብድር አሰጣጥ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ በግልጽ ይታይ ስለነበር አምስት ሚሊዮን ብር አዋጥተው በቢሊዮኖች በሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ላይ እንዳሻቸው እንዳያዙ መመርያው መፍትሔ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ሌሎችም ብሔራዊ ባንክ የጠነከረ መመርያ ማውጣቱ የእስከዛሬው የባንኮች አሠራሮችና የቦርድ አባላት የፈጠሩት ክፍተት ስለመሆኑ ይስማማሉ፡፡ የቦርድ አባል ሆኖ ለመመረጥ ይደረግ የነበረው የቡድን ፉክቻ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባላት ዓመታዊ ክፍያን በ50 ሺሕ ብር እንዲገደብ ለመደንገግ አስገድዶታል፡፡

የገንዘብ መጠኑ ላይ የተደረገው ወሰን ሽኩቻውንና ወደ ላይ ለመውጣት የሚደረገውን ፍላጎት ባይገድብም፣ ችግሩ በተወሰነ ደረጃ እንዲረግብ አድርጓል፡፡ ወደቦርድ አባልነት መምጣት ሊያስገኝ የሚችለው ሌላ ጥቅም እንዳለ ጠቋሚ ሆኗል፡፡

ለቦርድ ምርጫ ድምፅ በገንዘብ የመግዛት እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ በአዲሱ መመርያ ገደብ ቢደረግባቸው ትክክለኛ ዕርምጃ ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ሊመረጥ የሚፈልገውን ቡድን በውክልና ድምፅ ይዘው የሚፈልጉትን ሰው ለማስመረጥ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ በሁሉም ባንኮች ይታይ ስለነበር፣ መመርያው በንፅህና የሚያገለግሉትን ወደላይ ለማምጣት ይረዳል ብለዋል፡፡ የባንኮቻቸውን እንቅስቃሴ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ለመስማት ይገደዱ የነበሩ ባለአክሲዮኖችም በአዲሱ መመርያ የተነሳ በተፈለገው ጊዜ መረጃ የማግኘት ዕድል በማግኘታቸው የመመርያው መልካም ጎኖች እንደሆኑም ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች