Saturday, September 30, 2023

የአንድ ፓርቲ ሥርዓት በኢሕአዴግ መቃብር ላይ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግልን በድል አጥናቆ የሽግግር መንግሥት የመሠረተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከትጥቅ ትግሉ መነሻ ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ በሕዝብ ምርጫ የሚመሠረት መንግሥት እንዲኖር ግቡ ነበር፡፡ ይህንኑ ግብ ዕውን ለማድረግ ከድል በኋላ ሁሉንም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ ውይይት በማድረግ የሽግግር መንግሥት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ይኼው ፓርቲ በመጀመሪያው የአገሪቱ ምርጫ ከማሸነፉ በፊትም የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ መንግሥት የአገሪቱን ልሂቃን በማሳተፍ ተቀርፆ በ1987 ዓ.ም. ፀድቋል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሚያጐናፅፋቸው መብቶች መካከል እንደ ሕገ መንግሥቱ ምሰሶዎች የሚቆጠረው የፖለቲካ መብት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በመቀጠልም ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት እንዳለው፣ ይህ ነፃነትም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነት በዚሁ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሥር ተፈቅዷል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡

ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በፍጥነት ወደታች ወደ ሕዝቡ በማውረድ በኢትዮጵያ የሠለጠነ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ገዥው ፓርቲ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተንቀሳቅሷል፡፡ ሥልጣንን በሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት በሚደረጉ የፖለቲካ ውድድሮች የሚሳተፉ ፓርቲዎች ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እየጨመሩ እንዲመጡና የፓርላማ መቀመጫን የማግኘት ወይም የመመረጥ ዕድላቸውም በዚያው ልክ መስፋቱን በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡

በመጀመሪያው አጠቃላይ ምርጫ ከገዥው ፓርቲ ውጪ የፓርላማ ውክልናን ያገኙ አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ስምንት የግል ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ በ1992 ዓ.ም. በተካሄደው ሁለተኛው አጠቃላይ ምርጫ ወደ ፓርላማ የገቡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሥር ሲሆኑ፣ ተጨማሪ 13 የግል ተወዳዳሪዎችም መቀመጫ አግኝተው ነበር፡፡

በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ከሌሎቹ ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ የፖለቲካ ምኅዳሩ በሰፊው የተለቀቀበት፣ ሰፊ ክርክር በነፃነት የተካሄደበትና የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የገዛ እንደነበር የብዙዎች ትዝታ ነው፡፡

በዚህ የምርጫ ወቅት 136 የፓርላማው መቀመጫዎች በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የመሞላትን ዕድል አገኙ፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በሁለት እግሩ ለማቆም ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው የተጭበረበረ ነበር በማለት በመቃወማቸው ተገኝቶ የነበረው ዕድል ውኃ ሆነ፡፡

በአንፃሩ ይህ የምርጫ ሒደትና ውጤቱ ለኢሕአዴግ የማንቂያ ደወልን አቃጨለ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች እንዲሁም ራሱ ኢሕአዴግም እንደሚለው፣ የሕዝብን የልማት ጥያቄ በእኩል ማስተናገድና ፈጣን ዕድገት ማምጣት አንዱ ከምርጫው ውጤት የቀሰመው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ይህንን እየከወኑ ለመጪው ምርጫ መዘጋጀት ሌላው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የምርጫ ሕግ፣ የፓርቲዎች የሥነ ምግባር ኮድ የመሳሰሉት በሕግ ደረጃ ሲወጡ ኢሕአዴግ በፓርቲ ደረጃ መዋቅሩን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋቱን ቀጠለ፡፡ የአባላትን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ የወጣቶችና የሴቶች ሊጐችን በማደራጀት ሥሮቹን በመላ ኅብረተሰቡ መስደድ ቀጠለ፡፡ ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲ በ2002 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያገኝ እርግጠኛ አልነበረም፡፡

ከምርጫው በፊት በነበሩ ዓመታት የፈጸማቸው የፖለቲካ ዝግጅቶችና የፖለቲካ መዋቅሩን የማስፋት እንቅስቃሴዎች የት እንደሚያደርሱትና ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስገኙለት እርግጠኛ እንዳልነበር፣ በመስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ከታተመው የፓርቲው ልሳን አዲስ ራዕይ መጽሔት መገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹በምርጫው አሸናፊ የሚለየው በፌዴራል ደረጃና በክልል ደረጃ በሚደራጁት ምክር ቤቶች አብላጫ ወንበር በማግኘት ነው፡፡ ኢሕአዴግ በፌዴራል ደረጃና በአራት ክልሎች ይወዳደራል፡፡ ኢሕአዴግ አሸናፊ የሚሆነው በፌዴራል ምክር ቤትና በአራቱም የክልል ምክር ቤቶች ካሉት ወንበሮች ውስጥ 51 በመቶ ሲያገኝ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ወንበር ቢገኝ የሚጠላ አይደለም ብቻ ሳይሆን፣ ማግኘት የቻልነውን ያህል ለማግኘት መሥራት እንዳለብን ግልጽ ነው፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ምርጫ ውጤት ኢሕአዴግ የፌዴራል ፓርላማውን ወንበሮች ከአጋሮቹ ጋር በመሆን 99.6 በመቶ አሸነፈ፡፡ ይህም ማለት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይና አንድ የግል ተወዳዳሪ ብቻ የፓርላማውን መቀመጫ አገኙ፡፡ ይህ ሁኔታ በርካቶችን ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግንም ያስደነገጠ ነበር፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በምርጫው ማግሥት ለመረጣቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ምሥጋና ባቀረቡበት ወቅት፣ ኢሕአዴግ በትልቁ የገመተው የፓርላማ መቀመጫውን 75 በመቶ ብቻ መያዝ ነበር ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከገደል አፋፍ ላይ እንደሆነ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችና የውጭ መንግሥታት ሥጋታቸውን ጠቆሙ፡፡ የገዥው ፓርቲ አመራሮች በተለይም የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ የተፈጠረውን የፖለቲካ ሁኔታ መገምገምና ምክንያታዊ ምላሽ ለመስጠት ይተጉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

አቶ መለስ በዋና አዘጋጅነት ይመሩት የነበረው የፓርቲው ልሳን አዲስ ራዕይ መጽሔት በመስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ስለምርጫ ካስነበበው የፓርቲው አቋም በተለየ መልኩ፣ በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. የምርጫውን ውጤት የሚተነትን በኢትዮጵያ ሊኖር ስለሚገባ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የራሱን ትርጓሚ የሚሰጥ አቋም ይፋ አደረገ፡፡

የአንድ ፓርቲ ሥርዓት በኢሕአዴግ መቃብር ላይ

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው የፓርቲው ልሳን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የገዥውን ፓርቲ አዲስ አቋም ይዞ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ብቅ ብሏል፡፡

‹‹ምርጫ 2002 በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ፀረ ሕገ መንግሥት ኃይሎችን ማርጅናላይዝ (ጥግ ማስወጣቱን) ማድረጉና ተመልሰው የሚያገግሙበት ዕድል በጣም ጠባብ መሆኑን ማረጋገጡ፣ አንድ አዲስ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ መጀመሩን ያሳያል፡፡ የምርጫ 2002 ድል ተራ የምርጫ ድል ሳይሆን በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት አንድ አዲስ የስትራቴጂ ምዕራፍ የከፈተና ወደ አዲስና የላቀ ደረጃ ያሸጋገረን ድል ነው፤›› በማለት የራሱን የፖለቲካ አመክንዮ አቅርቧል፡፡

በአጠቃላይ በኢሕአዴግ የተያዘው አቋም በዋና የፖለቲካ ተዋናይነት የሚፈረጁ ክፍሎች ማለትም ፓርቲዎችና ኅብረተሰቡ ሕገ መንግሥቱን በሙሉ ልብ አምነው ካልተቀበሉ፣ የፖለቲካ ውድድሩ ሕገ መንግሥቱን ተጠቅሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ወይም ለመከላከል የሚደረግ ፍልሚያ እንደሚሆንና በዚህ ውስጥ ደግሞ የተረጋጋ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖር እንደማይችል የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ይህንን ሥራ ሕዝቡ ቀድሞ በመከወን በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ተቃዋሚዎችን ዳር እንዳወጣ የሚያምነው ፓርቲው፣ በቀጣይ ይህንን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ተቃዋሚዎች ፈጽሞ እንዳያንሰራሩ ለማድረግ አቋም ይዞ እየሠራ መሆኑን በይፋ ይገልጻል፡፡ ይኼ የሚሆነውም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አምነውና ተቀብለው የሚሠሩ ፓርቲዎች እስኪፈጠሩ ድረስ መሆኑን ፓርቲው ይገልጻል፡፡   

ጠንካራ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የጋራ ጠንካራ እምነት ያላቸው ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት እንደሆነ፣ በኢትዮጵያም ይህ እስኪመጣ ድረስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳያንሰራሩ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡     

ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ፓርቲዎች በመሠረታዊ የፖሊሲ ጉዳዮችም ቢሆን እጅግ ተቀራራቢ የሆነ አመለካከት እንደሚኖራቸው፣ በመሆኑም በምርጫ አንዱ አንዱን ቢተካ የሚከሰት ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እንደማይኖር፣ ስለዚህም ምርጫዎች ተራ የፖለቲካ ሁነቶች ሆነው እንደሚፈጸሙ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያም ይህ እስኪመጣ ድረስ አሁን ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳያንሰራሩ ማድረግን በአቋም ደረጃ ይዟል፡፡

ይህ አካሄድ በራሱ ሕገ መንግሥታዊ አለመሆኑን የሚከራከሩ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ሰላማዊ በሆነ የፖለቲካ ውድድር እስካሸነፈ ድረስ በሕዝብ ፈቃድ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች የማሻሻል ወይም በሌላ የመተካት መብት ሊኖረው እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተንፀባረቁ የፖለቲካ ድንጋጌዎች ይዘትም ይኼንኑ የሚፈቅዱ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡  

ይህንን ፈቅዶ መንፈግ እንዲሁም ለኢሕአዴግ ብቻ የሚመች የመድበለ ፓርቲ ፅንሰ ሐሳብን በሌላው ላይ መጫን፣ የአምባገነንነት ብሎም ከቻይና የተወሰደ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ይተቻሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ የሚቀጠል ከሆነ ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ ላይ ብቻ የተጻፈ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያላት አገር ከመሆን እንደማትመለስ፣ ይህም የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎች ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ሌሎች አማራጮችን እንዲከተሉ የሚያስገድድ እንደሆነ በመግለጽ ኢሕአዴግ እየሄደበት ያለውን መንገድ ይተቻሉ፡፡ አንደኛውኑ አሁን ያሉትን ፓርቲዎች በሕግ እንዳይንቀሳቀሱ መገደብ አይሻልም ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ኢሕአዴግ በበኩሉ የሚሰጠው ምላሽ የመራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ምሰሶ ተብለው ከሚታወቁት መብቶች ውስጥ በቅድሚያ የሚጠቀሱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህ የተደነገገ በመሆኑ ዜጐች ሕግና ሥርዓቱን እስካከበሩ ድረስ ሕገ መንግሥቱን የመቀየር ዓላማንም ይዘው የመደራጀት መብት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ ይህ መብት ለአንድ ዜጋ ከተከለከለ የሌላውም አደጋ ላይ ይወድቃልና መብታቸውን እያከበሩ እንዳያንሰራሩ ማድረግ እንደሚገባ የሚገልጽ ስላቅ የሚመስል ምላሽ ይሰጣል፡፡

‹‹የእነርሱን መብት የማክበር ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን ራሱን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ነው፤›› በማለት ይከራከራል፡፡

የዳበረ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተዘርግቶ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የጋራ ጠንካራ እምነት ያላቸው ፓርቲዎች ለምርጫ እስኪሰለፉ ድረስ፣ ኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ እንደሚቀጥል ይገልጻል፡፡

ይህ ጊዜ ምን ያህል ዓመታትን እንደሚፈጅ በግልጽ ፓርቲው አያውቀውም፣ ወይም በይፋ አላስቀመጠውም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ፈጽሞ ሊመጣ እንደማይችል በድፍረት ይሰብካል፡፡ የፓርቲው ልሳን እንደሚገልጸው በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን የተሻለ የአስተዳደር ሥርዓት የመምረጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ሉዓላዊነት፣ የአገሪቱን ህልውናና ቀጣይነት የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ኢሕአዴግ ከጅምሩም በትጥቅ ትግል ያሳለፈውና መስዋዕትነት የከፈለው የአንድ ፓርቲ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመልሶ እንዲመጣ እንደማይፈቅድ ይናገራል፡፡

ፓርቲው በመሬት ፖሊሲው ላይ ያለውን አቋም ከዚህ ቀደም በገለጸበት መንገድ፣ ‹‹የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ተመልሶ እንዲመጣ ይፈቅዳል ማለት ድርጅቱ ራሱን በራሱ ያጠፋል የማለት ያህል ነው፡፡ በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ተመልሶ የሚመጣበት ሥርዓት ዝግ ነው፤›› ይላል፡፡

ይህ የፓርቲው አቋምና አዲሱ የመድበለ ፓርቲ ፅንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያን ወዴት ይዟት እየሄደ እንደሆነ ደፍሮ ለመናገር አዳጋች ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ይህንን አቋም በወሰደ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መንፀባረቂያ ዋነኛ መድረክ የሆነውን የፓርላማ መቀመጫ በ2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ከነአጋሮቹ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል፡፡ ይህ ፓርላማ በዚህ ሳምንት የኢሕአዴግን መንግሥት በመመሥረት የአንድ ፓርቲ ሐሳብ ብቻ በነፃነት የሚንፀባረቅበት ችሎት የመሆን ሥራውን ይጀምራል፡፡   

 

   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -