Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሒልተንና ሸራተን በሆቴል ደረጃዎች አሰጣጥ አለመደሰታቸውን ገለጹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰናዳው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የታደሙት የሒልተንና የሸራተን ኃላፊዎች፣ መንግሥት በቅርቡ መተግበር በጀመረው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ አለመደሰታቸውን ገለጹ፡፡

በሒልተን ዓለም አቀፍ የአውሮፓና የአፍሪካ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ፊትዝጊቦን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ስለሚገኘው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ ተጠይቀዋል፡፡ ሒልተን አዲስ አበባ የአራት ኮከብ ደረጃ ማግኘቱን ተከትሎ ቅሬታቸውን ካቀረቡ 11 ባለኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ምንም እንኳ በደረጃ አሰጣጡ ሒደትና በሒልተን ውጤት ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢጠነቀቁም፣ ደረጃ መዳቢዎች ከሚያወጡት የኮከብ ደረጃ ይልቅ የሒልተንን ማምነት የሚገልጸው ደንበኞች ከሒልተን የሚጠብቁት አገልግሎት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሒልተን ብራንድ ከሚሰጠው የኮከብ ደረጃ ይልቅ በደንበኞቹ ይታወቃል ያሉት ፊትዝጊቦን፣ በተዘዋዋሪ ከመናገር ውጪ በቀጥታ ቅሬታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

በሌላ በኩል ሸራተን አዲስ ሆቴልን የሚያስተዳድረው ስታርውድ  ሆቴሎችና ሪዞርቶች ዓለም አቀፍ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአፍሪካና የህንድ ውቅያኖስ የቀጣናው የኦፕሬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ሐሳን አህዳብም ከሪፖርተር ስለደረጃ አሰጣጡ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንደ አህዳብ አባባል በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ አገሮች ያሉ ደረጃ አውጪዎች ሊገነዘቡት የሚገባው የሆቴል ደረጃ አሰጣጥ ‹‹ጊዜው ያለፈበት›› ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡ ሆቴሎች ባላቸው የብራንድና የቄንጠኝነት ደረጃ መመደብ አለባቸው የሚሉት አህዳብ፣ ከደረጃ አሰጣጥ ይልቅ በብራንድ ላይ መተኮር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በየጊዜው እየተቀየረ ባለው የሰዎች አኗኗር ሳቢያ የኮከብ ደረጃ ሆቴሎችን ገላጭ ሆኖ እንዳላገኙት በመጥቀስ፣ ሸራተን ባለአምስት ኮከብ ከመባል ይልቅ ‹‹ለግዠሪ ኮሌክሽን›› በሚለው ደረጃው በደንበኞቹ ዘንድ እንደሚታወቅ፣ ይኸው ብራንድም መገለጫው እንደሆነ በመግለጽ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥን አጣጥለውታል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ከሆኑት መካከል ከዓለም የቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ባስተዋወቀው የደረጃ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት፣ እስካሁን መግለጫ የተሰጠባቸው 95 ባለኮከብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ ተመዝነው ውጤት ቢነገራቸውም እነማን እንደሆኑ ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ግን ሚኒስቴሩ ተቆጥቦ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥን ካጠናቀቀ በኋላ ለቀረቡለት ቅሬታዎች ምላሽ በመስጠት የደረጃ አሰጣጡ ያካተታቸው ሆቴሎችና ያገኙትን ደረጃ ይፋ እንደሚያደርግ ቢያስታውቅም እስካሁን ዝምታን መርጧል፡፡ ይሁንና ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያገኙት ሸራተን፣ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል እንዲሁም ካፒታል ሆቴልና ስፓ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጪ የተቀሩት ሆቴሎች ከአራት እስከ አንድ ኮከብ ባለው ደረጃ የተመደቡ ናቸው፡፡

ሒልተን ኢንተርናሽናል ሁለተኛውን ሆቴል በሐዋሳ ለማስተዳደር ከሰንሻይ ቢዝነስ ጋር በተዋዋለበት ሳምንት፣ ሸራተንን የሚያስተዳድረው ስታርውድ በበኩሉ በአፍሪካ 20 የሆቴል ፕሮጀክቶች ላይ እየሠራ መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ምንም ይፋ የሚያደርገው የሆቴል ፕሮጀክት እንደሌለ የስታርውድ የአፍሪካና የህንድ ውቅያኖሶች ቀጣና ልማት ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ኔል ጆርጅ አስታውቀዋል፡፡

አህዳብ በበኩላቸው ሸራተን አዲስን ከጥንስሱ ጀምሮ ሲያተዳድሩ ቆይተው በቅርቡ ያረፉት ዣን ፔዬር ማኒጎፍ በምክትላቸው ተተክተው ሆቴሉን የማስተዳደር ኃላፊነት እንደተረከቡና ሆቴሉ ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶችም ሳይስተጓጎሉ መቀጠላቸውን ከሪፖርተር ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡ በሟቹ ማኒጎፍ አስተዳደር ጊዜ ከሠራተኞች ጋር የነበረውን ግጭት በሚመለከትም ተጠይቀዋል፡፡ ሟቹ በነበራቸው ሥራን በፍጥነት የመሥራት ፍላጎትና ችኮላ ይከሰቱ ከነበሩ ችግሮች ውጪ የጎላ ችግር እንዳልተፈጠረ ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ በተለያዩ ጊዜያት መብታቸውን በመጠየቃቸው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ ገበታቸው መሰናበታቸውን ሠራተኞች ሲገልጹና አስተዳደሩን ሲከሱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች