– ለቃል ክርክር ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
ከተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ በነፃ መሰናበታቸውን በመቃወም፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ አቅርቦት የነበረው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት አገኘ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አመራሮች የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የዓረና ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ተጠርጥረው ከተከሰሱበት የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ መከራከር ሳያስፈልጋቸው እንዲለቀቁ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኘው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ፣ በማግሥቱ ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ያቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ አቤቱታውን መቀበሉንና ሁለቱ ወገኖች የቃል ክርክር እንዲያደርጉ ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የይግባኝ አቤቱታው ሲቀርብለት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይፈጸም በማገድ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን መርምሮ ‹‹ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም?›› በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የሰጠው ቀጠሮ እንደሚያስቀርብ ያስታወቀው ሦስት ተከሳሾች ሳይቀርቡ ነው፡፡
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰለሞን (ከእነ ሀብታሙ ጋር የታሰረና የፓርቲ አባል ያልሆነ ተከሳሽ) የቀረቡ ሲሆን፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የታሰሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሸዋስ አሰፋ አልቀረቡም፡፡