Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከማዕድን ዘርፍ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዷል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማብቂያ፣ ከማዕድን ወጪ ንግድ በየዓመቱ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ ከመስከረም 20 እስከ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ውይይቱን የሚመሩት የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደገጹት፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጠናቀቂያ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ ከማዕድናትና ከጋዝ ወጪ ንግድ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ የውጭ ምንዛሪውን በዋነኛነት ለማግኘት የታቀደው ከወርቅ፣ ከፖታሽ፣ ከታንታለምና ከተፈጥሮ ጋዝ ኤክስፖርት እንደሆነ አቶ ቶሎሳ አስረድተዋል፡፡

በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ኦጋዴን ክልል ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ በ2010 ዓ.ም. ወደ ምርት ይገባል ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በአፋር ክልል ውስጥ ዳሎል አካባቢ የሚገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው የፖታሽ ማዕድን ለማልማት ጥናት ሲያካሂዱ የቆዩት ያራና ሰርኪውም ሪሶርስ የተሰኙ ኩባንያዎች ወደ ምርት ይሸጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አላና ፖታሽ የተሰኘው የካናዳ ኩባንያ በፖታሽ ምርት ለመሰማራት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ሰፊ የፍለጋና የምርመራ ጥናት ካካሄደ በኋላ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የከፍተኛ የማዕድን ምርት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው እንደታሰበው ወደ ምርት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ ‹‹አላና ፖታሽ በዓለም ገበያ ከፖታሽ ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር ተያይዞ እንዳሰብነው አልሄደልንም፤›› ብለዋል አቶ ቶሎሳ፡፡ አላና የፖታሽ ይዞታውን አሳልፎ እስራኤል ኬሚካልስ ለተሰኘ ግዙፍ የእስራኤል ኩባንያ የሸጠ ቢሆንም፣ ማዕድን ሚኒስቴር የሽያጭ ውሉ በአግባቡ እንዳልተገለጸለት አስታውቋል፡፡ ‹‹እኛ የሰማነው ወሬውን ነው እንጂ ፎርማል በሆነ መንገድ አልተገለጸልንም፡፡ ስለዚህ እኛ የምናውቀው አሁንም አላና መኖሩን ነው፤›› ብለዋል አቶ ቶሎሳ፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የወርቅ ምርት በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡ አዳዲስ የወርቅ ማውጫ ያቋቁማሉ ተብለው የሚጠበቁት ከፊ ሚኒራልስ (ወለጋ ውስጥ) ሚድሮክ ጎልድ (መተከል)፣ አስኮም ማይኒንግ (ቤኒሻንጉል) እና ኢዛና ማይኒንግ (ትግራይ) ውስጥ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከማዕድን ኤክስፖርት 500 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች፡፡ ከዚህ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የወርቅ ኤክስፖርት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ በማሽቆልቆሉ በ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከማዕድን ኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ቀንሷል፡፡ ይህንን ለማካካስ የማዕድን ሚኒስቴር የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡ የከበሩ ድንጋዮችና ጌጣ ጌጥ ኤክስፖርት መጨመር፣ የታንታለም ምርት መጨመርና የፖታሽ ምርት መጀመር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በተካሄደው ውይይት የማዕድን ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለኢንዱስትሪ ማዕድናት ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዓለሙ የማዕድኑ ዘርፍ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኮንስትራክሽንና ለግብርና ዘርፎች ግብዓት በማምረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች