Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጤፍን ጨምሮ ነባር ዝርያዎች አደጋ እንደተጋረጠባቸው በጥናት ተረጋገጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ዝርያዎችን ለመታደግ አገር አቀፍ ፓኬጅ ተዘጋጅቷል

ጤፍን ጨምሮ በአርሶ አደሩ ዕጅ የሚገኙት የስንዴ፣ የገብስ፣ የዳጉሳና የሌሎች አዝርዕት ነባር ዝርያዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ፡፡ ከተሻሻሉ ዝርያዎች አኳያ ያላቸውን የተሻለ ምርታማነት ከግምት ባለማስገባት በተሻሻሉና በድብልቅ ዝርያዎች ለመተካት በሚደረገው ሙከራ ሳቢያ፣ የነባሮቹ ዝርያዎች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን በጥናት መረጋገጡን፣ የኢትዮጵያና የዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ተቋማት ገልጸዋል፡፡

በተለይ በጤፍና በስንዴ ላይ በተደረጉ ጥናቶች በተፈጥሮ ይዞታቸው የሚታወቁት ነባር የአርሶ አደሩ ዝርያዎች፣ በሳይንሳዊ መንገድ ተዳቅለው ‹‹የተሻሻለ ዝርያ›› ተብለው የሚሰራጩት በምርታማነታቸውና በተስማሚነታቸው ውጤታማ መሆናቸውን የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡

በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ገመዶ ዳቤ፣ ‹‹በተደጋጋሚ እንደሚነሳው የእኛ ያልሆኑ ዝርያዎች ምርታማ አይደሉም ሲባል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከዓለም አቀፉ የብዝኃ ሕይወት ተቋም ጋር በጋራና በተናጠል ባደረግናቸው ጥናቶች ለአገር በቀል ዝርያዎች የተሰጠው ግምት የተሳሳተ እንደሆነ ከመረጋገጡም ባሻገር፣ በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ ተሻሽለው ተዘጋጁ ከሚባሉት የተሻለ ምርታማነት እንዳላቸው ተረጋግጧል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ ‹‹በእጃችን ያለውን እምቅ ኃይል ሳንጠቀም ከውጭ በመጡ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ በመሞከራችን የራሳችንን አገር በቀል ዝርያዎች አደጋ ውስጥ እየጣልናቸው ነው፤›› በማለት ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ባሳዝነው በበኩላቸው፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ጤፍን ለዓለም ያበረከተችና ጤፍም ከ4,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ቢኖረውም፣ በአገሪቱ ከስንዴና ከገብስ በፊት ምርምር ማድረግ ቢጀመርም፣ በአሁኑ ወቅት በተሻሻሉ ዝርያዎችና በሌሎችም ምክንያት ጤፍ አደጋ ተደቅኖበታል በማለት፣ ወደፊት ሊጠፋ ይችላል የሚለውን ሥጋት አጠናክረዋል፡፡

‹‹ይህ ዝርያ (ነባሩ ጤፍ) ከባህር ወለል በታች ከ3,000 እስከ 1,500 ሜትር ከፍ ሲልም እስከ 1,700 ሜትር፣ በአገራችን መመረት ይችላል፡፡ እንዲሁም በአገራችን አርሶ አደሮች ዕጅ ያለው የጤፍ ዝርያ በምርታማነቱ የበላይነት ከፍ ያለ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን በተሻሻሉ ዝርያዎችና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ነባር ዝርያዎች ከፍተኛ አደጋ መጥቶባቸዋል፤›› በማለት ተባባሪ ተመራማሪው አስጠንቅቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከ5,900 በላይ የጤፍ ዝርያ ናሙናዎች ተሰብስበው በኢትዮጵያ ዘረመል ባንክ ውስጥ እየተጠበቁ ሲሆን፣ በዚህ ሰብል ዝርያ ላይ የሚደረገው ናሙና የማሰባሰብና የባህርይ ትንተና ሥራ በግብርና ሳይንስ ምርምር ከ1950ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ነበር የተጀመረው፡፡

እንደ ኃላፊዎቹ ከሆነ የባህርይ ትንተና አካል የሆነው ምርምር በ2006 እና በ2007 ዓ.ም. ተካሄዶ ነበር፡፡ ምርምሩም 12 የአርሶ አደር ዝርያዎችና ቁንጮ ተብሎ የሚታወቀውን ጤፍ ጨምሮ ሦስት አዳዲስ ዝርያዎችን (የተሻሻሉ ዝርያዎች) ያካተተ ሲሆን፣ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳና በሌሎች አራት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የአርሶ አደር ማዕከላት ውስጥ የምርምር ሥራዎች መከናወናቸው ተነግሯል፡፡

በምርምር ሥራው የተገኙትን ውጤቶች ይፋ ያደረጉት አቶ ፋንታሁን፣ ‹‹ለማወዳደሪያነት በተረመጡት የተሻሻሉ ዝርያዎችና በአርሶ አደር ዝርያዎች መካከል መመዘኛ በተደረጉት ከመድረሻ ቀን፣ ከእህል ምርት፣ ከቁመት፣ ከዛላ እርዝመት አንፃር ሲታይ በስታትስቲክሳዊ ሥሌት መሠረት ልዩነት እንደሌላቸው ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ የተለቀቁት የተሻሻሉ ዝርያዎች የተሻለ የምርት መጠን እንደሚኖራቸው በስፋት የሚታመን ቢሆንም፣ በተጠቀሱት የናሙና ውጤቶችና በስታትስቲክሳዊ ሥሌቶች መሠረት የአርሶ አደሩ ነባር ዝርያዎች የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት ያህል ቁንጮ በሚባለው የተሻሻለ የጤፍ ዝርያና በነባሩ ዝርያ ላይ በአራት አካባቢዎች በተካሄደ ጥናት መሠረት፣ ነባሩ ዝርያ በሔክታር 22 ኩንታል ምርት ሲሰጥ ቁንጮ ግን 21 ኩንታል ብቻ መስጠቱን በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ጤፍ ሁሉ በሌሎችም የአዝርዕት ዓይነቶች ላይ ተመሳሳይ ውጤት መታየቱን የሚገልጹት የተቋሙ ተመራማሪዎችና ኃላፊዎች፣ አገር በቀል ዝርያዎች ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸውና የተለየ የአመራረት ፓኬጅም ተግባራዊ መደረግ እንደለበት አሳስበዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የብዝኃ ሕይወት ተቋም በበኩሉ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ሥፍራዎች በስንዴና በዳጉሳ ላይ ባካሄዳቸው የናሙና ጥናቶች፣ ከውጭ ከሚገቡትም ሆነ ከተዳቀሉት የተሻሻሉ ዝርያዎች አኳያ በሚሰጡት የምርት መጠንና በጥራት አገር በቀሎቹ ነባር ዝርያዎች የተሻሉ መሆናቸውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ብዝኃ ሕይወት ተቋም ተጠሪ ካርሎ ፋዳ፣ ስኮላ ሳንታ አና ከተባለው የጣሊያን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምር በተካሄደ ጥናት፣ በአርሶ አደሩ ዕጅ የሚገኙትና ለማካሮኒና ለፓስታ ማምረቻ የሚያገለግሉ ስንዴዎች (ዱረም) በተፈጥሮ ካላቸው የዝርያ ተያያዥነትም ሆነ ዘረመል አወቃቀር አንፃር፣ ለገበሬው ከተሰራጩ የተሻሻሉ ዝርያዎች (Mediterranean Group)  ከሚባሉት በእጅጉ የተሻለ ምርታማነት እንደሚታይባቸው አስረድተዋል፡፡

አደጋ ተደቅኖባቸዋል የተባሉ ዝርያዎችንና ሌሎች በይፋ ያልተለዩ አገር በቀል ዝርያዎችን በተሻለ መንገድ ለመጠቀምና ‹‹ከመዋጥ ሥጋት›› ለማዳን፣ የተለየ ፓኬጅ  በመዘጋጀቱ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ረዘም ላሉ ዓመታት ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትኩረት መስጠቱን፣ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በተለይ ለምርትና ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ መሆኑን የሚገልጸው መንግሥት፣ በግብርና ምርምር አቅምና በቴክኖሎጂ መስክ ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱን ደጋግሞ ሲናገር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የምርምር ማዕከላትን በመላ አገሪቱ እየተስፋፉ በመምጣታቸው በተሻሻሉ ዝርያዎች የተሻለ ውጤትና ተስፋ እየታየ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአሁኑ የጥናት ውጤት ግን ጥያቄን አጭሯል፡፡ በተለይ ባለፉት ዓመታት መንግሥት የግብርና ምርምር ተቋማት እንዲስፋፉና የነባሮችንም አቅም በማሳደግ በግብርና ምርት ዕድገት መታየቱን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች፣ የእስከዛሬው ጥረት አሁን ይፋ ከወጣው የጥናት ውጤት አኳያ ሲታይ የቀድሞዎቹ ኢንቨስትመንቶችና ጥረቶች ተገቢነት ላይ ትልቅ ጥርጣሬ ያሳደረ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች