ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየው አምስተኛው የአገሪቱ ፓርላማ መቀመጫዎች ምንም እንኳ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በአጋሮቹ ሙሉ በሙሉ የተያዙ ቢሆንም፣ አሁን ካለው ተጨባጭ የዓለም ሁኔታና ከአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት እንዲያሰፍን ይጠበቃል፡፡ ይህ ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን በሁሉም መስኮች ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችንና አስተዳደራዊ መዋቅሮችን የሚፈልግ በመሆኑ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንም ሆነ ልማትን ለማካሄድ፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ሆነ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት ተጠያቂነት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የፓርላማው ኃላፊነት ነው፡፡
ተጠያቂነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ በዓለማችን ላይ ትልቅ ትኩረት ያገኘበት ምክንያት፣ በምርጫ የሕዝብ ድምፅ አግኝተው ሥልጣን የሚይዙ ወገኖች የሚያገለግሉት ሕዝብ ለሚያቀርብላቸው ማንኛውም ጥያቄ መልስ የመስጠት ግዴታ ስላለባቸው ነው፡፡ በመሆኑም ተጠያቂነት የሥነ ምግባር፣ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲና የመርህ መገለጫ በመሆኑ ትልቅ ግምት አለው፡፡ ተጠያቂነትን የማስፈን ጉዳይ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ለይስሙላ ብቻ የሚነገር ሳይሆን፣ በተግባር የተረጋገጠ ውሳኔ የሚሻ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ውሳኔ የሚያረጋግጠው ደግሞ የሕዝብ ኃላፊነት የተሰጠው ትልቁ የሥልጣን አካል የሆነው ሕግ አውጪ ፓርላማ ብቻ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ከሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መካከል በዋናነት የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሙስና በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ በግልጽነትና በተጠያቂነት ያለመኖር ምክንየት ሕዝብ ላይ የሚፈነጩ ችግሮች የአገር ሥጋት እየሆኑ ነው፡፡ ቁርጠኝነት ካለ በቁጥጥር ሥር መዋል የሚችሉት እነዚህ አደገኛ ተግዳሮቶች በጠንካራ የሥነ ምግባር መርህና በሕግ የበላይነት ሊገቱ ይችላሉ፡፡ ለተግባራዊነታቸውም ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን በመተማመን ላይ ያልተመሠረተ ግንኙነት ለማጠናከር የፓርላማው ሚና የጎላ ነው፡፡ ፓርላማው ራሱ ተጠያቂነትን መርህ ካደረገ ደግሞ ይሳካል፡፡
በመጀመሪያ የገዥው ፓርቲና የአጋሮቹ አባላት የሆኑ የፓርላማ ተመራጮች ወገንተኝነታቸው እንዳለ ሆኖ ታማኝነታቸውን ለሕገ መንግሥት፣ ለህሊናቸውና ለመረጣቸው ሕዝብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን በተግባር ማረጋገጥ ከቻሉ ሦስቱን የመንግሥት አካላት ማለትም የሕግ አውጪውን፣ የተርጓሚውንና የአስፈጻሚውን መናበብ በሚገባ ይቆጣጠራሉ፡፡ ሕግ አውጪው (ፓርላማው) የሕዝብ ውክልና ያለው የሥልጣን አካልነቱ እንዳይሸረሸር፣ ሕግ ተርጓሚው ፍትሕ እንዳያዛባ፣ አስፈጻሚው የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ እንዲሠራ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ በዚህ ሁኔታ ሲከናወን ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ይፈጠራል፡፡
ተጠያቂነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ባለመከበሩ ምክንያት ሕዝብ በአስተዳደር በደል እየተማረረ ነው፡፡ ኃላፊነታቸውን መወጣት በማይችሉ ደካማ አመራሮችና ግድ የለሾች ምክንያት መልካም አስተዳደር ማስፈን አልተቻለም፡፡ ፍትሕ ማስፈን ባመቻሉ ምክንያት ሕዝብ እየተበደለ ነው፡፡ ጉልበተኛ በነገሠበት በዚህ ወቅት ሕዝብ ፍትሕን በገንዘብ እንዲገዛ እየተገደደ ነው፡፡ ያልቻለ ደግሞ እንባውን እያዘራ ነው፡፡ ያፈራውን ሀብት እየተነጠቀ ነው፡፡ ያለጥፋቱ በእስራት እየማቀቀ ነው፡፡ በሙሰኞች ኔትወርክ ምክንያት አገር እየታመሰ ነው፡፡ በአብዛኞቹ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ሙስና ነግሷል፡፡ ጉቦ የማይከፍል አገልግሎት አያገኝም፡፡ ሕገወጡ ደረቱን ነፍቶ የፈለገውን ሲያደርግ በሕጉ መሠረት የሚለው ሜዳ ላይ ቀርቷል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ተሁኖ ነው የተጠያቂነት ያለህ እየተባለ ያለው፡፡
የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ተጠያቂነት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት እየተናበቡ፣ በተለይ ደግሞ ፓርላማው አስፈጻሚውንና ሕግ ተርጓሚውን በሚገባ እየተቆጣጠረ የሕዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይኖርበታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት የሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች በሚገባ መከበራቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ እነዚህን መብቶች የሚጥሱ ሕገወጦች አደብ እንዲገዙ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ፍትሕን እየደፈጠጡ ሕዝቡን ነፃነቱን የሚቀሙት ወገኖች አንድ መባል አለባቸው፡፡ ተጠያቂነት ያልሰፈነበት ሥርዓት እንኳን ዴሞክራሲ ሊገነባ ራሱም አደጋ ውስጥ እንዳለ ሊገነዘብ ይገባል፡፡
ፓርላማው በተለይ በቋሚ ኮሚቴዎቹና በጊዜያዊ ኮሚቴዎቹ አማካይነት የአስፈጻሚውን አካል የዕለት ተዕለት ሥራዎች መቆጣጠር አለበት፡፡ በዘፈቀደ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን መጣል አለበት፡፡ የአገሪቱ በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በሚገባ መቆጣጠር አለበት፡፡ በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ የመንግሥት ተቋማትን አብጠርጥረው መፈተሽ አለባቸው፡፡ እጅግ በጣም በተዝረከረኩ አሠራሮች የአገር ሀብት እየወደመ ነው፡፡ ተቋማቱ ሕዝብ እያስመረሩ ናቸው፡፡ በሙስና ተጥለቅልቀዋል፡፡ ተጠያቂነት የሌለባቸው የሚመስሉት እነዚህ ተቋማት የአገር ገጽታ እያበላሹ ነው፡፡ እነዚህን ዝርክርክ ተቋማትና አመራሮቻቸውን ለመሸፈን ሲባል ግልጽነትና ተጠያቂነት በመጥፋቱ አገር እያለቀሰች ነው፡፡ ፓርላማው ለዚህም ትልቅ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርት ማንም መታለል የለበትም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፓርላማዎችን በሚመለከት ያለው ግንዛቤ የሚያስረዳው፣ ፓርላማ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትንና የፍትሕ ሥርዓቱን በተጠያቂነት ማዕቀፍ ውስጥ መቆጣጠር እንዳለበት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ፓርላማው በሕዝብ ዘንድ ያለው ተዓማኒነት ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ፓርላማው የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትን ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ዕንባ ጠባቂ ተቋምና መሰል ድርጅቶችን ክፍተቶችን ለመሙላት በሚገባ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ተጠናክረው የሚፈለግባቸውን ሲያከናውኑ ተጠያቂነት ይጎለብታል፡፡ ሕገወጥነት ይከስማል፡፡
ፓርላማው ሕዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ መሆኑን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ መከበራቸውን፣ በመልካም አስተዳደር እጦት አለመቸገሩን፣ በሙስና አለመዘረፉን፣ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ በተግባር መታየቱን፣ ወዘተ. በሚገባ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ የፓርላማ አባላት ታማኝነታቸው ለሕገ መንግሥት፣ ለህሊናቸውና ለወከላቸው ሕዝብ ነው ሲባልም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጎች ሲወጡ የወከሉትን ሕዝብ ፍላጎት ማረጋጥ እንዳለባቸው መሟገት አለባቸው፡፡ ፖሊሲዎች ሲቀረፁ የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ሊታገሉ ይገባል፡፡ በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ሕዝብ ላይ በደል ሲደርስ ከማንም በፊት ማጋለጥ አለባቸው፡፡ የአስፈጻሚው አካል ጡንቻ ደንድኖ ሲያስቸግር ማስታገስ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕግ ተርጓሚው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽም መገሰጽ ብሎም ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተጠያቂነት እንዲሰፍን መስዋዕትነት ይክፈሉ፡፡
አገር የምትበለጽገው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው፣ የመልካም አስተዳደር እሴቶች የሚያብቡት፣ ሙስና የሚጠፋው፣ ዜጎች በነፃነት ሠርተው የሚኖሩት፣ አዲሱ ትውልድ አገር ለመረከብ የሚያስችለውን ዕውቀትና ልምድ የሚቀስመው፣ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረውና ሰላም የሚረጋገጠው ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ሲገነባ ብቻ ነው፡፡ ይህም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ሕግ ይከበርበታል፡፡ ሕገወጥነት ቦታ አይኖረውም፡፡ ተጠያቂነት በሌለበት ሥርዓት ውስጥ ግን ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት ይገዝፋሉ፡፡ የአገር ሉዓላዊነት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ መንግሥትም አገርን መምራት ያቅተዋል፡፡ ተጠያቂነት በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ መንግሥትና ሕዝብ ግንኙነታቸው ሰላማዊ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የልማቱ ተጠቃሚና ባለቤት ሕዝብ ይሆናል፡፡ አጭበርባሪዎችና ሌቦች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ አምባገነንነት አይታሰብም፡፡ የዜጎች ነፃነት ይከበራል፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በቋንቋ፣ በፆታና በመሳሰሉት ልዩነቶች አይኖሩም፡፡ ሥልጣን በጉልበት ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይያዛል፡፡ አገር የነፃነት፣ የብልጽግናና የዴሞክራሲ ተምሳሌት ትሆናለች፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ፓርላማው ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ያስፍን የሚባለው!