ማክሰኞ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲሱ ካቢኔያቸው በፓርላማ የፀደቀላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ለሰባት የመንግሥት ባለሥልጣናት የአማካሪ ሚኒስትርነትና የካቢኔ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመት ሰጡ፡፡
በሹመቱ መሠረት የቀድሞ የንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር፣ አቶ በዙ ዋቅቤካ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር፣ የቀድሞ በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተሹመዋል፡፡
የቀድሞ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፊስካል ፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር፣ የቀድሞ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መኮንን ማንያዘዋል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም አቀፍ ንግድ ግንኙነት ድርድር ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር፣ የቀድሞ የደንና የአካባቢ ሚኒስትር አቶ በለጠ ታፈረ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፋሰሶችና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
የቀድሞ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡