Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየብሔራዊ ቡድኑ ‹‹ሽፍንፍንነት›› እስከምን ድረስ?

  የብሔራዊ ቡድኑ ‹‹ሽፍንፍንነት›› እስከምን ድረስ?

  ቀን:

  ብዙ ጊዜ ጎልተው የሚደመጡት የብሔራዊ ቡድኑ ችግሮች ከአሠለጣጠንና የጨዋታ ዘይቤ ጋር ተያይዞ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ቢሆኑም፣ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ እነማን ከየትና እንዴት ተካተቱ የሚሉት ጥያቄዎችም በተመሳሳይ መልኩ ይደመጣሉ፡፡ እርግጥ ነው በአንድ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስለሚካተቱ ተጫዋቾች ምርጫና አሠላለፍ ሙሉ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚኖረው ዋና አሠልጣኙ ሲሆን፣ የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ የቴክኒክ ቡድን አባላትም የራሳቸው የሆነ ሚና እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን ፌዴሬሽኑም ሆነ አሠልጣኙ ስለተመረጡ ተጫዋቾችም ሆነ ስለሚሠለፉበት የጨዋታ ቦታ በሚዲያው በኩል ለሕዝቡ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡

  ይኼ ደግሞ የትኛውም ወገን በተወሰነ ነገር ላይ ቅሬታና ድብቅብቅ ብሎ የሚታይ ጥርጣሬ እንዳይኖረው ያግዛል ሲሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡
  ከሰሞኑ ሦስት የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ጋር ብሔራዊ ቡድኑ በሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ አለመካተታቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝም ሆኑ ፌዴሬሽኑ ምንም አለማለታቸው በእግር ኳሱ ቤተሰብ ዘንድ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ነገሮችን አጥርቶ ከመሄድ አንፃርም ሆነ ከመረጃ ነፃነት አንፃር ቢታይ የብሔራዊ ቡድኑ አመራር የሚከተለው መንገድ ትክክል አለመሆኑን የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ በብሔራዊ ቡድኑ የሚከሰቱ ማንኛውንም ዓይነት ለውጦች ከውሳኔ በኋላ ሕዝቡ የማወቅ መብት እንዳለውም ይሞግታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ከነገ በስቲያ ዓርብ ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ጋር በስታዲየም ኒኮላ ይጫወታል፡፡ ቡድኑ ማክሰኞ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በማለዳው ወደ ሥፍራው አምርቷል፡፡ 18 ተጫዋቾች መጓዛቸውም ተነግሯል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሽመልስ በቀለና ዋሊድ ኦታ በስተቀር ሦስቱ በደቡብ አፍሪካ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ፣ በአልጄሪያ የሚጫወተው ሳላዲ ሰይድና በግብፅ የሚጫወተው ኡመድ ኡክሪ ከቡድኑ እንዴትና በምን አግባብ ሊቀነሱ እንደቻሉ በአሠልጣኙም ሆነ በፌዴሬሽኑ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩት ይሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ቀርቷል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ቀድሞ የነበረው አሠራር የቀረበት ምክንያት እንኳ ማወቅ አልተቻለም፡፡

  አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ቡድኑን ስፖንሰር ካደረገው ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት ትልልቅ ውድድሮች ሲኖር በተናጠል ሳይሆን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት እንደሚችሉ ከፌዴሬሽኑ መመርያ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ደግሞ ይኼ የአሠልጣኙ መብት ስለሆነ እንዲህ ማድረግ አለብህ ብሎ ጣልቃ መግባት እንደማይፈልግ ይናገራል፡፡ አሠልጣኙም ሆኑ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በጉዳዩ መድረኮችን ፈጥረው በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ ግን አይስተዋልም፡፡ በዚህ ምክንያት አሠልጣኙ ለሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ጨዋታ ይዘዋቸው የተጓዙ ተጫዋቾችን አስመልክቶ ቅርበት ካላቸው ምንጮች በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ግብ ጠባቂዎች ታሪክ ጌትነት፣ ለዓለም ብርሃኑና አቤም ማሞ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሥዩም ተስፋዬ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ሙጅብ ቃሲም፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ አስቻለው ግርማ፣ ቢኒያም በላይ፣ ኤፍሬም አሻሞ፣ በረከት ይሳቅ፣ ራምኬሎ ሎክ፣ ዳዊት ፈቃዱና ሽመልስ በቀለ ናቸው፡፡ ለቱርክ በመጫወት ላይ የሚገኘው ዋሊድ አታ ደግሞ በዚያው ወደ ሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ያቀናል ተብሎ እንደሚጠበቅም እየተነገረ ይገኛል፡፡  
   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img