Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየይቻላል አሸናፊዎች

  የይቻላል አሸናፊዎች

  ቀን:

  በርካታ የአገራችን ሴቶች በልዩ ልዩ ሙያ ሰልጥነው ለዘመናት በወንዶች ብቻ ተይዞ የነበረውን ሥራ ሲያቀላጥፉ ይታያል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በአውቶቡስ ሾፈርነት ወይም በባስ ካፒቴንነት አሰልጥኖ ያስመረቃቸው 34 ሴት ሾፌሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

  በድርጅቱ ልዩ ልዩ ቢሮዎች ውስጥ በጽሕፈት ሥራ ተመድበው ያገለግሉ የነበሩት እነዚሁ ሴቶች የሾፌርነት ሥልጠና ሊያገኙ የቻሉት በራሳቸው ፈቃድና ድርጅቱ ለዚሁ ሲል ያወጣውን መስፈርት በማሟላታቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በንድፈ ሐሳብ፣ በቴክኒክና በማሽከርከር ዙሪያ ለሦስት ወራት ያህል የተሰጣቸውን ሥልጠና በብቃት ጨርሰዋል፡፡ የተዘጋጀላቸውንም ፈተና አልፈው ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የይቻላል ምስክሮች ለመሆንና ለመመረቅ በቅተዋል፡፡

  አቶ ያብባል አዲሱ፣ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ለተመራቂዎቹ ምስክር ወረቀትና በትምህርታቸው ብልጫ ላገኙት ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ኃላፊው “የአውቶቡስ ሾፌርነት ሥራ መኪናውን ማሽከርከር ብቻ አይደለም፡፡ የበርካታ ተሳፋሪዎችን ምቾትና ደህንነት በጠበቀ ሁኔታ፣ በወቅቱና በፕሮግራሙ መሠረት ተፈላጊው ቦታ የማድረስ ኃላፊነት ያለበት ነው፤” ብለዋል፡፡

  ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ የወጣቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ተመራቂዎቹ በሥልጠና የቀሰሙትን ሙያ ተፈጥሮ በቸራቸው ፀጋዎች ተጠቅመው በየጊዜው የሚታየውና የሚሰማውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

  አቶ በድሉ አሰፋ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ “ሥልጠናው ለሰልጣኞቹ ቴክኒካዊ ብቃትን ብቻ የሰጠ ሳይሆን በእነሱም ሆነ በሌሎቹ የድርጅቱ ሠራተኞች ዘንድ የይቻላል አስተሳሰብን ለውጥ ያስገኘ ነው” ብለዋል፡፡

  ከተመራቂዎቹም መካከል በስልጠናው አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ሽልማት ያገኘችው ወይዘሮ ወይንሸት ደገፋው ናት፡፡ ተሸላሚዋ ባለትዳርና የአንዲት ልጅ እናት ስትሆን በድርጅቱ ውስጥ የአገልግሎት ክፍያ ተቀባይ ወይም ገንዘብ ተቀባይ ሆና ስታገለግል እንደነበር ትናገራለች፡፡ ድርጅቱ ለሴቶች ልዩ ዕድል በሚል የባስ ካፒቴን ለመሆን በወጣው ማስታወቂያ መሠረት መስፈርቱን አሟልታና ተመዝግባ ሥልጠናውን ወስዳለች፡፡

  ከባለቤቷ በሥልጠናው ላይ ቢያበረታትም እና በተቃራኒው ደግሞ ወንድሞቿ ይቅርብሽ ሾፌርነት ይከብድሻል እንዳሏት ትናገራለች፡፡

  “እንኳን እኔ ጀማሪዋ ቀርቶ ነባር ሾፌርም ሥራው ሊከብደው ይችላል፡፡ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ዋናው በጥንቃቄ መሥራት ብቻ ነው የሚል እምነት ስለነበረኝና ፍላጎትም ስላደረብኝ ሥልጠናውን በንቃት መከታተሉን ተያያዝኩት” ብላለች፡፡

  በፆታ ምክንያት ለወንዶችና ለሴቶች ተብሎ የተለየ ሥራ የለም፡፡ ሴቶች ይችላሉ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ብልህነትን፣ ጠንቃቃነትንና አስተዋይነትን የመሳሰሉ ፀጋዎችን ከተፈጥሮ ተችረዋል፡፡ ይህ ችሮታ ደግሞ በቴክኒክና በክህሎት ሥልጠና ሲደገፍ የበለጠ ውጤታማ ወይም ምርታማ እንደሚያደርጋቸው አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img