አሥራ አምስት ነጥብ አምስት ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው የሞዛይክ ሥዕል ሥራው ተጠናቅቆ እሑድ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉርድ ሾላ በሚገኘው በካቶሊክ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ተመረቀ፡፡ በኢትዮጵያዊቷ ሠዓሊት መዓዚት ኃይሌ የተዘጋጀው የመጨረሻው እራት (ዘ ላስት ሰፐር) የተሰኘው ሥዕሉ በዓመታዊው ዓለም አቀፍ የሞዛይክ አርት ዐውደ ርዕይ ለመሳተፍ ወደ ጣሊያን ሚላኖ እንደሚሄድም ታውቋል፡፡
ከስብርባሪ ሴራሚኮች የተዋቀረው ሥዕሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር የነበረውን የመጨረሻ እራት ያሳያል፡፡ ሥራውን ለማጠናቀቅም ዘጠኝ ወራት ያህል የፈጀ ሲሆን፣ ከ400 ሺሕ የሚበልጡ ስብርባሪ ሴራሚኮችን እንደፈጀ መዓዚት ትናገራለች፡፡
ምስሉ በሥዕል ሥራ ግንባር ቀደም ከሆኑት ተርታ የሚሠለፈው የሠዓሊ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ ሥራዎች አንዱ ‹‹ዘ ላስት ሰፐር›› (የመጨረሻው እራት) የተሰኘውን ሥራ ይወክላል፡፡ የመጀመሪያ ሥዕሉን ለማስመሰልም ኦርጅናል ሥዕሉ እንደተጠቀመች ትገልጻለች፡፡ ምንም እንኳን የኦሪጅናል ምስሉን መሠረት በማድረግ እንድትሠራ ብትገደድም የራሷን የቀለም ምርጫ ተከትላለች፡፡
‹‹በጣሊያን፣ በአሜሪካና ሌሎችም ፍላጐት ባሳዩ አገሮች ተዘዋውሮ ይታያል፡፡ ይህም አገሪቱን ለማስተዋወቅ ይረዳናል፤›› የምትለው መዓዚት ሥዕሉን አገራዊ ይዘት እንዲኖረው ብትፈልግም እንዳልተሳካላት ገልጻለች፡፡
ከዚህ ቀደም ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሥዕሎችን መሠራት ብታዘወትርም በሞዛይክ ይዘት ስትሠራ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሥዕሎች መሥራቷ ግን ከጣሊያናዊው የሞዛይክ ሠዓሊ ከሆነው ጆን ፍራንኮ ጋር እንድትገናኝና ምስሉን እንድታዘጋጅ ረድቷታል፡፡ እንደ መዓዚት ገለጻ፣ የሞዛይክ ጥበቡን ያስተማራት ጆን ነው፡፡ ጆን በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር የሞዛይክ ሥራ አዘጋጅቷል፡፡ የመጨረሻው እራት ከዚህ ቀደም ከቀረበበት በመጠንም ሆነ በአሠራር የተለየ ነው፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ዲፕሎማቶችና ጥበበ አፍቃሪዎች እንዲመለከቱት ክፍት ይደረጋል፡፡
ሞዛይኩ ከተለመደው አሠራር ውጪ በፓናሎች ላይ በመሆኑ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲታይ ያስችለዋል፡፡ ይህም አገሪቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ በሚላን ከሚዘጋጀው ዐውደ ርዕይ በኋላ ዓመቱን በሙሉ በሌሎች አገሮች በመዘዋወር ይታያል፡፡ በየዓመቱ መጨረሻ ላይም ኢትዮጵያ በመመለስ ጉርድ ሾላ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ይቀመጣል፡፡