Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኢሬቻ በቢሾፍቱ

ኢሬቻ በቢሾፍቱ

ቀን:

ስንታየሁ ጉርሜሳና ብርቄ ታደሰ የተወለዱት ቦረና ነው፡፡ ወጣቶቹን ያገኘናቸው የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በኢሬቻ በዓል ላይ ለመፈጸም ቢሾፍቱ ከተማ በተገኙበት ወቅት ነበር፡፡ በየዓመቱ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበትን ዕለት ብዙ ጥንዶች ለሠርጋቸውም ይመርጡታል፡፡ ዘንድሮ ባለተራ ከሆኑት 20 ጥንዶች መካከል የሆኑት ጥንዶቹ፣ በኢሬቻ በዓል ላይ ጋብቻቸውን መፈጸም ህልማቸው እንደነበረና በመሳካቱም እንደተደሰቱ ይናገራሉ፡፡

‹‹ኢሬቻ ላይ በአባ ገዳ ምርቃት ቃል መገባባታችንን ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን፤ ባህላችን በመሆኑም የጋብቻ ሥርዓቱን ለመፈጸም ቀኑን ጠብቀናል፤›› የሚለው ስንታየሁ፣ በዕለቱ ከአባ ገዳ የተሰጣቸው ምርቃት ትዳራቸውን የተባረከ እንደሚያደርገው ይገልጻል፡፡ ቦረና በቤተሰቦቻቸው በተዘጋጀ ሠርግ ላይ ውህደታቸውን ይፋ ከማድረጋቸው አስቀድሞ፣ በኢሬቻ መጣመራቸው ጋብቻቸውን ውበት እንዳላበሰውም ያክላል፡፡

መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሲዲ ሐይቅ አቅራቢያ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የመጡ ሰዎች የታደሙበት ነበር፡፡ ከተማዋ ሞቅ ደመቅ ማለት የጀመረችው ከበዓሉ ዋዜማ አንስቶ ነበር፡፡ በመላ ከተማዋ የሚታዩት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያዘሉ ፖስተሮች ቢሾፍቱን ልዩ ገፅታ አላብሰዋታል፡፡ እያንዳንዱ ነዋሪ ቤት ከሚገኝ ስፒከር በሚያስብል መልኩ እዚህም እዚያም የኦሮምኛ ባህላዊ ሙዚቃዎች ይደመጣሉ፡፡ ሰብሰብ ብለው የሚጨፍሩም ጥቂት አይደሉም፡፡

የበዓሉ ዕለት ንጋት ላይ ወደ ሐይቁ የሚተሙ አክባሪዎች በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አልባሳት ተውበው ይታያሉ፡፡ የቦረና፣ የወለጋ፣ የሸዋ፣ የሐረርጌ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ባህላዊ ቁሳቁሶች አንግበው በዜማ ታጅበው ይጓዛሉ፡፡ ለምለም ሳርና አደይ አበባ በእጃቸው ይዘው፣ ‹‹ኦ… ያ…ማሬዎ … ማሬዎ፤›› እያሉ ክረምት በሰላም ተገባዶ በበጋ ወዳጅ ዘመድ በበጎ ስለመገናኘቱ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ሲሆን፣ ክረምት በሰላም አልፎ መፀው (አበባ ወቅት) ሲገባ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት እንዲሁም በጋው ረዝሞ ድርቅና ችግር እንዳይከሰት የሚማፀንበት ሥርዓት ነው፡፡ የሥርዓቱ ሁለት ዓይነት የአከባበር ሁኔታዎች ኢሬቻ መልካና ኢሬቻ ቱሉ ይባላሉ፡፡

ኢሬቻ ቱሉ የሚከናወነው የበጋ ወቅት ተጠናቆ የክረምት ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡ ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ ካልጣለ ድርቅ ተከስቶ ሰውና እንስሳት ስለሚጎዱ፣ ሕዝቡ አስቀድሞ በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ከፍ ባለ ተራራ ላይ በመውጣት ጥላ ባለው አካባቢ ሆነው ክረምት በሰላም እንዲገባና ዝናብም እንዲዘንብ ፈጣሪን ይማፀናሉ፡፡

ኢሬቻ መልካ ደግሞ ክረምት ተጠናቆ መፀው ሲገባ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ይከናወናል፡፡ ይህ ሥርዓት በክረምት ወቅት የሞላው ዝናብ ቀንሶ በወንዙ ሙላት ሳቢያ ተራርቆ የነበረው ዘመድ በመገናኘቱ ለፈጣሪ ምሥጋና የሚቀርብበት ሕዝቡም ደስታውን የሚገልጽበት ነው፡፡

በኢሬቻ መልካ ወዳጅ ዘመድ ከያሉበት ተጠራርተው የባህል ልብስ ለብሰው፣ እርጥብ ሳርና አደይ አበባ ይዘው ‹‹ፈጣሪን እንለምናለን፤ በፈጠረውም ነገር ፈጣሪን እናደንቃለን፤›› እያሉ ወንዝ ወርደው፣ ሙላቱ ከቀነሰው ወንዝ በሳሩና በአደይ አበባው ውኃ እየነከሩ ፊታቸውን ሰውነታቸውንም ይረጫሉ፡፡

ኢሬቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ክብረ በዓል ነው፡፡ ቢሾፍቱ የሚገኘው ሆራ አርሰዲም ከጥንት ጀምሮ ሥርዓቱ በተለየ ሁኔታ ሲከናወንበት የቆየ ስፍራ ነው፡፡ በዓሉ አንድ አምላክ (ዋቃ) የሚመሰገንበት ሲሆን፣ ሃይማኖት ሳይለይ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ዋቄ ፈታ አማኞችና የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችም ይታደማሉ፡፡ በአባ ገዳዎች ምርቃት የሚባረከው ኢሬቻ፣ ይቅር የመባባልም በዓል ነው፡፡

‹‹እርቅ እንዲወርድልን ለምለም ነገር ይዘን እንለምናለን፤ ኢሬቻ የእርቅ ምልክት ነው›› ያሉንን አቶ ጫልቶ በቀለን ያገኘናቸው በዓሉን ሲያከብሩ ነበር፡፡ በለገጣፎ የጥቃቅንና አነስተኛ አስተዳደር ውስጥ ይሠራሉ፡፡

ከኦሮሞ ባህል መገለጫዎች አንዱ የሆነውን ኢሬቻ፣ ‹‹ክረምትን በደህና ያወጣን ፈጣሪ እንኳን ወደ ብርሃን አደረሰን በማለት የኢሬፈና ሥርዓት የሚከናወንበት ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ አገር ሰላም እንዲሆን የሕዝብ አንድነትም እንዲጠናከር ፈጣሪ የሚለመንበት በዓል ይሉታል፡፡ በየዓመቱም በቢሾፍቱ ይታደማሉ፡፡

በኢሬቻ የኦሮሞን ባህል የሚያንፀባርቁ አልባሳት ይለበሳሉ፤ ልዩ ባህላዊ ምግቦችም ይዘጋጃሉ፡፡ ቅንጨ፣ ገንፎ፣ ጨጨብሳ፣ አንጮቴ፣ ጨሮርሳና ጭኮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ምግቦች ናቸው፡፡ ሁሉም በየዕድሜ ክልሉ በልዩ ልዩ ዝማሬ ደስታውን ያሰማል፡፡

ወይዘሮ አፀዱ ቶላ የአዳማ ተወላጅ ናቸው፡፡ ጮጮ (ወተት የሚያዝበት) አንግበው፤ የአርሲ ባህላዊ ልብስ ለብሰው በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ጮጮ በትልልቅ በዓሎች ስለሚያዝና የኦሮሞን ባህል ስለሚያሳይ እንደያዙት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢሬቻን ወንዶችና ሴቶች በህብረት የሚያከብሩት ቢሆንም ለሴቶች ልዩ ወቅት ነው፤›› ይላሉ፡፡ የተራራቁ የሚገናኙበት በዓል በመሆኑ ልዩ ቦታ ይሰጡታል፡፡

የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አለሜ ፋቲም የወይዘሮ አፀዱን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ በግብርና የሚተዳደሩት አዛውንቷ ኢሬቻ የምስጋና፣ የደስታ በዓል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቤታቸው እንጀራ በጎመን፣ ጠላ ያዘጋጃሉ፣ ችቦ አብርተው እየተመራረቁ ያከብራሉ፡፡ ‹‹በኢሬቻ ብርሃን ይሆናል፣ አበባ ያብባል፣ ዘርም ይደርሳል›› የሚሉት ወይዘሮ አለሜ፣ በዓሉን ከልጆቻቸው ጋር በየዓመቱ በጉጉት እንደሚጠባበቁት ይገልጻሉ፡፡

‹‹አያንቱ›› የሆኑት አቶ ንጉሡ ሙሉጌታ ደግሞ ‹‹የኦሮሞ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ ትልቅ በዓል ነው፤›› ይላሉ፡፡ በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት መልካም እንደሆነ ያክላሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ሕዝቡ አባ ገዳዎችን አጅበው በአደባባይ ምርቃት ይፈጽማሉ፡፡ ሌሊቱን በጭፈራ ካሳለፉ በኋላ በዓሉን አክብረው ወደ እንግዶች ሽኝት ያመራሉ፡፡ ኢሬቻ ቢሾፈቱ ከተከበረ በኋላ በቀናት ልዩነት ቦረና፣ ጉጂ፣ ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ሐረርጌ ስለሚከበር ዝግጅት እንዲያርጉ መልዕክት አስተላልፈውም ይለያያሉ፡፡

ቢሾፍቱ በየአካባቢው ያሉ አባ ገዳዎች እንዲሁም የበዓሉ አክባሪዎች ተሰባስበው የሚያከብሩበት ቦታ ነው፡፡ ‹‹አገር ሰላም ይሁን፤ ሰብል ሰላም ይሁን፤ የተዘራው ይብቀል፤ ነጋዴው አትርፎ ይግባ፤ መመቀኛኘት ይቅር፤ ልጆች ይደጉ፤›› ከምርቃቶቻቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡

የዘንድሮውን ኢሬቻ ለየት የሚያደርገው የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ ለመመዝገብ ጫፍ ላይ ባለበት ወቅት መከበሩ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድርና በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አልፋ ራይት ተገኝተዋል፡፡

አቶ ሙክታር፣ ‹‹የሥልጣኔና አብሮ የመኖር ተምሳሌት እንዲሁም የዴሞክራሲ መሠረት የሆነው የገዳ ሥርዓት ከኢትዮጵያ በላይ የዓለም ቅርስ ነውና ልዩ ጥበቃ ያሻዋል፤›› በማለት ነበር ስለበዓሉ የገለጹት፡፡ አቶ አሚን በበኩላቸው፣ ኢሬቻ ቱሪስቶችን ለመሳብ ያለው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ባህሉን በመጠበቅ ረገድ የሕዝቡ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቦታ አለውም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...