Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የቻይናው የመስታወት ድልድይ

ትኩስ ፅሁፎች

ቻይናዎቹ ሃኦሃን ኳኦ ብለውታል፡፡ ትርጉሙም የጀግና ወይም የደፋር ሰው ድልድይ ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን በቻይና አገግሎት መስጠት የጀመረውና 300 ሜትር የሚረዝመው የመስተዋት ድልድይ፣ በቻይና ደቡባዊ ክፍል የሚገኘውን ሽዋንዚ ብሔራዊ ፓርክ አቋርጦ የሚያልፍ ነው፡፡

የድልድዩን ስራ መጀመር ተከትሎ በስፍራው የተገኙ ቻይናውያንና የውጭ አገር ቱሪስቶች ድልድዩን ለማቋረጥ በፍርሃት ሲርዱ፣ በዳዴ ሲሄዱ፣ መሀል ላይ ቆመው ፍርሃታቸውን ሲገልጹ በሲኤንኤን ታይተዋል፡፡

ከመስተዋት የተሠራው ድልድይ ከበታቹ ያለውን ገደል፣ ዳገትና ቁልቁለት እንዲሁም ወንዝ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ በተጠቃሚዎቹ ላይ ፍርሃት የሚያነግስ ቢሆንም፣ ድልድዩን የሠሩት ባለሙያዎች ድልድዩ ጠንካራና አስተማማኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድልድዩን ለመሥራት ከመደበኛ የመስተዋት ዓይነቶች 25 እጥፍ ጥንካሬና 24 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው መስተዋት ጥቅም ላይ የዋለ በመሆኑ፣ በድልድዩ የሚጠቀሙ ማናቸውም ሰዎች ቢዘሉበት እንኳን እንደማይሰበር ኮንትራክተሮቹ ተናግረዋል፡፡ ቢሰበር እንኳን ተጠቃሚዎች ወደ መሬት እንደማይወድቁም አሳውቀዋል፡፡

የቀድሞው የሃኦሃን ድልድይ በእንጨት የተሠራ ነበር፡፡ በ2014 ላይ ጥቂት የድልድዩ ክፍል ለሙከራ ተብሎ በመስተዋት የተሠራ ሲሆን፣ ከ2015 መስከረም መገባደጃ ጀምሮ ደግሞ አብዛኛው ክፍሉ በመስተዋት ተተክቷል፡፡ ቀሪው ክፍል ሲጠናቀቅ ድልድዩ በዓለም ትልቁና ረዥሙ የመስተዋት ድልድይ ይሆናል፡፡ 430 ሜትር ርዝመትና 300 ሜትር ቁመትም ይኖረዋል፡፡

***********

መጠየቅ መጠየቅ

መጠየቅ ቢጠየቅ፣ ጥያቄው መልስ ነው

‘ጠ’ በመጥበቋ ነው፣ እንደዚህ የሆነው

መጠየቅ ቢጠየቅ፣ መልሱ ጥያቄ ነው

‘የ’ ስለከረረ፣ ነገሩን ለወጠው።

ትልቁ ጥያቄ፣ ሰዉ እንደሚያስበው

የመልስ እጦት ሳይሆን፣ ጥያቄ ጠፍቶ ነው።

ሰው ራሱ ጥያቄ፣ ጥያቄስ መች ጠፋ

ጠያቂ መጥፋቱ፣ ነው እንጂ የሚይስከፋ።

ሁሉ ጠያቂ ነው፣ ጠያቂ አላነሰ

ተጠያቂ ጠፍቶ፣ ጥያቄው ኮሰሰ።

መጠየቅ መጠየቅ ለምን ያምታታሉ

ማጥበቅ ማላላቱስ ምን ይለውጣሉ?

ከአጉል ድካም በቀር ምን ይፈይዳሉ?

ያላወቁ ሰዎች ይጠያይቃሉ

መልሱን ላይፈልጉ ጠየቅን ይላሉ።

ጥያቄ መልስ የለው መልስም ጥያቄ አይሻው

የሚል ፍልስፍና ከንቱ ኪኒን ውጠው

ጥያቄን ሲሸሹ ከመልሱ እርቀው

መጠየቅን ፈርተው ጠያቂውን ገድለው

በስተመጨረሻ ጥያቄዎች ሆነው

ከገቡበት ማጥ ውስጥ መውጣት አቅቷቸው

ስንቶች በዛው ጠፉ ካንገት በላይ ሞተው።

መላላት ያለበት ሲከርር ሲጠብቅ

መክረርም ያለበት ሲላላ ሲለቀቅ

እንዴት ለውጥ አይኑረው ትርጉም አያጠፋ

በዚህ አይደለም ወይ አገሩ የጠፋ።

በሰው ነጻ ፈቃድ በሐሳብ በምርጫው

በኑሮ አካሄዱ በሆነ ባልሆነው

አክራሪ አጥባቂነት ሲነግስ ሲበዛ

አገር ሲያሸረግድ ለማይረባ ዋዛ

የጥቂቶች ምኞት ብዙውን ሲገዛ

ሰውነት ይቀላል ሕይወት ያጣል ለዛ።

ደግሞ ድንቅ ሐሳቦች እንቁ ውድ እሴቶች

የሰው ክቡርነት፣ ሰው የመሆን ፈርጦች

ሲላሉ ሲረሱ፣ እንደተራ ነገር

ምን ጊዘው ቢረዝም፣ ምንም ውሎ ቢያድር

ፍዳና መከራው፣ መወለዱ አይቀር።

የመልሶች ሁሉ ቋት የጥያቄው ምሥጢር

ማላላት ማጥበቅ ነው የነገሩ ነገር።

የመልሱ ጥያቄ የጥያቄው መልሱ

እንደነገሩ አመል እንዳደራረሱ

ማላላት ማጥበቅን ማወቅ ላይ መድረሱ

የሄው ነው ሚስጥሩ የሃሳብ መንፈሱ።

መጠየቅ መጠየቅ መመለስ መመለስ

የጥበብ ምንጭ ነው የሚያለመልም ነፍስ።

በምሕረት ደበበ

****************

የኤር ፍራንስ ማናጀሮች በሠራተኞች ተባረሩ

 በርካታ የሥራ ዘርፎችን ስለማጠፍ በመምከር ላይ የነበሩት የኤር ፍራንስ ማናጀሮች በቁጣ በነዳዱ ሠራተኞች ስብሰባ ጥለው ነፍሴ አውጭኝ ብለው መሮጣቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በስብሰባ ላይ የነበሩት ማናጀሮቹ ከተቆጡት ሠራተኞች ለማምለጥ ሲሞክሩ ልብሳቸው ተቀዳድዷል እንግልትም ደርሶባቸዋል፡፡ ኤር ፍራንስ በማናጀሮቹ ላይ የደረሰው ጥቃት እንዲሁ የሚያልፈው ሳይሆን ወደ ፍትህ አካል የሚወስደው ጉዳይ እንደሆነ አሳውቋል፡፡ የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ እንደገለጹት ተቃውሞ መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን መልኩን ቀይሮ ወደ ጥቃት የተቀየረው በጥቂት ሰዎች ምክንያት ነው፡፡

ማናጀሮቹ ሊያደርጉ አስበውት የነበረው የሥራ ዘርፎች ቅነሳ 1,700 ግራውንድ ሀንድሊንግ፣ 900 የበረራ ሠራተኞችንና 300 ፓይለቶችን የሚጨምር እንደነበር ታምኗል፡፡

**********

የ11 ዓመቱ ሕፃን የስምንት ዓመቷን ሕፃን ገደለ

አሜሪካ አንድ ስቴት ውስጥ የ11 ዓመት ሕፃን ትንሽዬ ውሻዋን አላሳይም ያለችውን የጎረቤት ሕፃን በሽጉጥ መግደሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ የተጠረጠረው ሕፃን ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡

ሕፃኑ የተበሳጨባትን ሕፃን የገደላት በአባቱ ሽጉጥ ሲሆን፣ ሕፃናቱ ጎረቤታሞች አንድ ትምህርት ቤት የሚማሩ ናቸው፡፡ የሕፃኗ እናት ሕፃኑ ቀደም ሲልም ስሟን እየጠራ በልጇ ያሾፍባት እንደነበር፤ ነገር ግን ግድያውን ከመፈጸሙ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ግን ማሾፉን ማቆሙን ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል፡፡

ሕፃኑ በተያዘው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ላይ ዳግም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

***********

ጥቁሩ ቁራ

ቁራ በአንድ ወቅት ሼኪ ወይም ቄስ ስለነበረ ቀለሙም ነጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ አእዋፋት ሁሉ አቤቱታ አሰሙበት፡፡ እንደዚህም አሉ ‹‹አንድ ወገን ሥጋ ይበላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍራፍሬ ይበላል፡፡››

ከዚያም ሁሉም አእዋፋት ተሰባስበው ‹‹አንተ ሼኪ ወይም ቄስ ነህ! ነገር ግን የምትሠራው ነገር ስህተት ነው፡፡ ትንንሾቹ አእዋፋት ሥጋ መመገብ አለባቸው፡፡ ትልልቆቹ ደግሞ ፍራፍሬ ይብሉ፡፡ አንተ ግን ከሁለቱም ወገን ትበላለህ፤›› አሉት፡፡

በሱማሌ ብቻ ሳይሆን በኩሽ ባህል በአጠቃላይ ቁራ የፀሐይ አምላክ የሆነው የዋቅ ተወካይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ኦሮሞዎችም ጭምር በፀሐይ አምላክ ያምናሉ፡፡ ቁራ የፀሐይ አምላክ ዋቅ የተናገረውን ለሰዎች የሚተረጉምና የሰዎችንም መልዕክት ወደ ፀሐዩ አምላክ የሚያደርስ መሆኑን ያምናሉ፡፡

ቁራውም ሲናገር “ዋቅ! ዋቅ!” እያለ ነው፡፡

ሆኖም ቁራው እምነት በማጉደል ሁለቱንም ነገሮች ማለትም ፍራፍሬና ሥጋ ስለበላ ቅጣት ተጣለበት፡፡ ረግመውትም ጥቁር ሆኖ ቀረ፡፡

በፕሮፌሰር አህመድ መሃመድ ዓሊ የተተረከ የሶማሌ ተረት

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች