Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሶሪያ ተስፋ የጣለችበት የሩሲያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት

ሶሪያ ተስፋ የጣለችበት የሩሲያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት

ቀን:

ላለፉት አራት ዓመታት ሶሪያውያን ጥቃትንና የጦርነት ወንጀልን ሲጋፈጡ ኖረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ለመጣል የተቀጣጠለው አብዮትም አገሪቷን ለእርስ በርስ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በሶሪያ አሸባሪውን የኢስላሚክ ስቴትን (አይኤስ) ጨምሮ ከ40 ያላነሱ የሸማቂ ቡድኖች ተፈልፍለዋል፡፡

አሜሪካ ከግብረ አበሮቿ ጋር በመሆን የአል አሳድ መንግሥትን ለመጣል በሶሪያ የሚገኙ ሸማቂ ቡድኖችን ስትረዳ፣ ሩሲያና ኢራን ደግሞ አል አሳድን ሲደግፉ ከርመዋል፡፡ በሶሪያ ግዛት እንደተስፋፋ የሚነገርለትን ኢስላሚክ ስቴት እንደምትዋጋ የምትገልጸው አሜሪካና ተከታዮቿ ቡድኑን ማጥፋትም ሆነ ሶሪያን ማረጋጋት ተስኗቸዋል፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን በሶሪያ ሁኔታዎች ገጽታቸውን እየቀየሩ ነው፡፡ ከሶሪያ ጋር እርስ በርስ ላለመጠቃቃትና ወታደራዊ ትብብርም ለመፈጸም ከ50 ዓመታት በፊት የተፈራረመችው ሩሲያ፣ የበሽር አል አሳድን መንግሥት ለመታደግ በሶሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አድርጋለች፡፡

አሜሪካና ግብረ አበሮቿ ከዓመት ላላነሰ ጊዜ ኢስላሚክ ስቴትን ለመዋጋት የፈጠሩት ጥምረት ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ሆኖም ሩሲያ በጥቂት ቀናት ውስጥ እመርታ ማስመዝገቧ የሶሪያን ሸማቂ ቡድኖችን አስደንግጧል፡፡ ጥምረት እንዲፈጥሩም ምክንያት ሆኗል፡፡

አልጄዚራ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ከኢራን ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሩሲያ በሶሪያ አማፅያን ላይ እየወሰደች ያለችው ወታደራዊ ዕርምጃ ሶሪያን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ መካከለኛው ምሥራቅን ለመታደግ የሚያስችል ነው፡፡

አል አሳድ እንደሚሉት፣ ኢስላሚክ ስቴትን ለመዋጋት የተሰየመው የአሜሪካ ጥምር ጦር ቡድኑን ለመዋጋት ተስኖታል፡፡ ሞስኮ ግን ቡድኑን እየደበደበች ነው፡፡ ለውጥም ታይቷል፡፡ የሩሲያና የኢራን ጥምረት መቀጠል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሶሪያ ብቻ ሳትሆን አጠቃላይ መካከለኛው ምሥራቅ ይወድማል፡፡  

የአገሮቹ መጣመር በሶሪያ ያለውን ጦርነት ለማርገብም ሆነ መካከለኛው ምሥራቅ የገጠመውን ፈተና ለመወጣት የሚኖረው አስተዋጽኦ የሚናቅና ትንሽ የሚባል እንዳልሆነም አል አሳድ ተናግረዋል፡፡

በሶሪያ አማፅያን ላይ የአየር ጥቃት የጀመረችው ሩሲያ፣ ድብደባ በጀመረችባቸው በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት ውስጥ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን ላይ ጥቃት መፈጸሟን አሳውቃለች፡፡

የሩሲያው መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የታቀደላቸውን ዒላማ ብቻ የሚመቱ ሚሳይሎችን የታጠቁ የጦር ጄቶች በኢስላሚክ እስቴት ይዞታዎች ላይ ድብደባ አካሂደዋል፡፡ በኢስላሚክ ስቴት ቁጥጥር ሥር የወደቀውንና በራቋ ከተማ የሚገኘውን የወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕም ደብድበዋል፡፡

ሩሲያ በሶሪያ የሚገኙትን ሸማቂ ቡድኖች በጀት እየደበደበችና እመርታ እያሳየች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ፣ ምዕራባውያኑ ሩሲያ ድብደባዋን ታቁም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ሩሲያ በበሽር አል አሳድ በሥልጣን የመቆየት ውሳኔ ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ሩሲያ በኢስላሚክ ስቴት የተያዙ የሶሪያ ግዛቶችን ሳይሆን የበሽር አል አሳድ ሕጋዊ ተቃዋሚዎችን በአየር ደብድባለች፤›› ሲሉም ተችተዋል፡፡ የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንገላ መርከል ደግሞ፣ በሶሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ቢያስፈልግም ብቻውን ደም መፋሰሱን አያቆምም፡፡ ፖለቲካዊ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው፣ ሩሲያ በሶሪያ አማፅያን ላይ የከፈተችው የአየር ድብደባ በማንኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሩሲያ በሶሪያ አማፅያን ላይ እየፈጸመች ያለችው የአየር ጥቃት ለበሽር አል አሳድ ጥንካሬን እየሰጠ ነው፡፡ ይህ ግን ለአሜሪካ፣ ለእንግሊዝ፣ ለቱርክና አሜሪካን ለሚደግፉ የባህረ ሰላጤው አገሮች ምቾት አልፈጠረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሶሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከማድረግ አስቀድሞ በሽር አል አሳድ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡

በሽር አል አሳድ እንደሚሉት፣ የእሳቸውን በሥልጣን የመቆየትና ያለመቆየት የሚወስነው ሕዝባቸው እንጂ የውጭ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ከኢራን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የገለጹትም ይህንኑ ነው፡፡ ‹‹የእኔ ከሥልጣን መውረድ ለሶሪያ ቀውስ መፍትሔ ከሆነ አላመነታም፡፡ ሆኖም ይህንን የሚወስነው ሕዝቡ ነው፤›› ሲሉም ለመጀመሪያ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡

በሽር አል አሳድ ከሥልጣን ቢወርዱ እንኳን ሶሪያን ማን ይመራታል? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ከሶሪያ የተወሰኑ ግዛቶች ለእኔ ይገቡኛል ሲል ኢስላሚክ ስቴት እየተዋጋ ነው፡፡ ከቡድኑ በተጨማሪ ከ40 ያላነሱ የአሳድ ተቃዋሚ ቡድኖች ሶሪያ ውስጥ እየተዋጉ ነው፡፡ ሩሲያ ደግሞ፣ ‹‹አል አሳድን በሥልጣን አቆይቶ ሸማቂዎችን በመደምሰስ በሶሪያ ሰላም ማምጣት ይቻላል፤›› የሚል አቋም ይዛ በሶሪያ አማፅያን ላይ የአየር ጥቃቷን ጀምራለች፡፡ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮችም ሩሲያ የአየር ጥቃት በጀመረች ማግሥት አል አሳድን ያካተተ ድርድር ከሶሪያ አማፅያን ጋር ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ጀምረዋል፡፡ የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎች፣ አሜሪካና የባህረ ሰላጤው አጋሮቿ ግን ይህንን ተቃውመዋል፡፡

ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ ላይ ከምዕራባውያን ጋር ከዚህ ቀደም የነበራትን አለመግባባት ወደ ጐን ብላ ከኢራን ጋር በመሆን ከአሳድ ጎን ቆማለች፡፡ የአየር ድብደባዋንም በአማፅያኑ ላይ ቀጥላለች፡፡ ይህ አሜሪካንና አጋሮቿን ብቻ ሳይሆን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ጭምር አስግቷል፡፡ የሩሲያ የጦር ጄት የቱርክን የአየር ክልል በስህተት ማቋረጡን ተከትሎም ‹‹አደገኛ ነው፡፡ ሞስኮ በሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችና በንፁኃን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ጥቃት መቆም አለበት፤›› ሲል ኔቶ አስታውቋል፡፡

ኔቶ ከ28 አባል አገሮች አምባሳደሮች ጋር ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባም፣ ሩሲያ የቱርክን የአየር ክልል መጠቀሟን ተቀባይነት የሌለው ሲል ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ከአስቸኳይ ስብሰባው በኋላ በሰጠው መግለጫም፣ የኔቶ አባል አገር የሆነችውን ቱርክ እንዲሁም ኔቶ የሚቀጠምበትን የአየር ክልል ሩሲያ መድፈሯ፣ ኃላፊነት የጐደለው አካሄድ ነው ሲልም ወቅሷል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ቱርክ ጄቱን ተኩሳ ጥላው ቢሆንስ? ከዚህ በኋላ ይህ ሊሆን ይችላል ሲሉ ማስፈራሪያ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ሩሲያ ወደ ቱርክ አየር ክልል በስህተት መግባቷን ስታምን፣ ቱርክ ደግሞ ስህተቱ ቢደገም የቱርክ መከላከያ ኃይል ጄቶችን አስገድዶ እንዲያርፉ እንደሚያደርግ አሳውቃለች፡፡

‹‹የሶሪያ ጉዳይ የቱርክና የሩሲያ አይደለም፡፡ የቱርክ ወዳጆችና ጠላቶች የቱርክን የአየር ክልል እንዲጥሱና እንዲደፍሩ አንፈቅድም፤›› ስትልም ቱርክ አሳውቃለች፡፡ ቱርክና ሩሲያ ከሶሪያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚቃረን ቢሆንም፣ የቱርክና የሩሲያ ግንኙነት ባለበት ይቀጥላል ስትልም ቱርክ ገልጻለች፡፡

ከዚሁ ጐን ለጐን በሩሲያ የአየር ድብደባ እያፈገፈጉ የሚገኙት የሶሪያ አማፅያን ሩሲያን ለመዋጋት ጥምረት ለመፍጠር ባደረጉት ጥሪ መሠረት፣ 41 የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች በሽር አል አሳድን የሚደግፉትን የሩሲያና የኢራን ጦርን በጥምረት ለመዋጋት ተፈራርመዋል፡፡ የአልቃይዳ የሶሪያ ክንፍ ግን በስምምነቱ አልተካተተም፡፡

ሩሲያ በሶሪያ አማፅያን ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰድ ከመጀመሯ በፊት፣ የአል አሳድ መንግሥት እየተሽመደመደ ነበር፡፡ ሆኖም የሩሲያ ለአል አሳድ ድጋፍ መስጠት መልሶ እንዲያንሰራሩ ይረዳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአል አሳድን መንግሥት የማይደግፉ ጂሃዲስቶች ከየአገሩ እንዲሰባሰቡና በሶሪያ የበለጠ አለመረጋጋት እንዲፈጥሩ ዕድል ይከፍታል፡፡ ይህ ደግሞ ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገሮች ጭምር ፈተና ይሆናል፡፡ ሩሲያ ይህን ሁሉ አስታርቃ በሶሪያ ሰላም ታሰፍን ይሆን? የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ሩሲያ በሶሪያ አማፅያን ላይ በከፈተችው የአየር ድብደባ ላይ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ የሶሪያ አማፅያን መደምሰስ ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለመካከለኛው ምሥራቅ ጭምር መፍትሔ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...