ለሰባት ዓመታት የዘለቀው የዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከሀብታሞቹ አገሮች በተጨማሪ ወደ ድሆቹ እየተጋባ ‹ሀብታሞቹ ጉንፋን በያዛቸው ቁጥር ድሆቹን እያስነጠሰ ከአንዱ ምዕራፍ ወደ ሌላው በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ አገሮች ለተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ ዕድገት ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፣ ፍላጎትን እንዲያነሳሱ ተጠይቀዋል፡፡
በመላው ዓለም ያለውን የንግድና የልማት እንቅስቃሴ በማስመልከት፣ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ (አንክታድ) አማካይነት ይፋ የተደረገው ሪፖርት፣ ሀብታም አገሮች እጅጉን ለተቀዛቀዘው የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የመንግሥት ወጪዎችን በማስፋፋት፣ ደመወዝ በመጨመር በምርትና አገልግሎቶች ላይ እየታየ ያለውን የፍላጎት መቀዛቀዝ እንዲያነሳሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያ ይፋ የተደረገውን ሪፖርት ያቀረቡትና ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ የአፍሪካ ክፍል፣ በመልማት ላይ ያሉ አገሮችና የልዩ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ፣ የሀብታም አገሮች ኢኮኖሚያዊ ሕመም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሆች አገሮችን ሳይቀር እየነካካ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ዘንድሮ በ2.5 ከመቶ ማደጉን የገለጹት ዶ/ር ተስፋቸው፣ በሀብታም አገሮች ውስጥ የሚታየው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያሉት አገሮች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያና አንጎላ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ የሚያስመዘግቡት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እየቀነሰ መምጣቱን አሳይተዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ በከፍተኛ መጠን እያደጉ ካሉ አገሮች ተርታ እንደሚሰለፉ እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ያረጋግጣሉ፡፡
ሪፖርቱን በማስመልከት ከጄኔቭ የወጡ መግለጫዎች እንደሚጠቁሙት የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ አገሮችን ማጥ ውስጥ መክተት ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ እስካሁን ባሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ ያደጉ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ባለበት ሲረግጥ ወይም በቆመበት ሲቀር፣ አሳታፊና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት በዓለም ሊታይ አለመቻሉን፣ በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ሙኪሳ ኪቱዪ ተናግረዋል፡፡
ሀብታም አገሮች ኢኮኖሚያቸው ባለበት እንዲረግጥ ቢገደዱም በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች ግን ውጤታማነትን እያተረፉ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትንም እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ የሀብታም አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ ባስከተላቸው የፍላጎትና የፍጆታ መቀዛቀዞች ሳቢያ፣ በሸቀጥ ንግድ ላይ የተመሠረተ የወጪ ንግድ ያላቸው አገሮች እየተጎዱ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ተስፋቸው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የዓለም የሸቀጦች ንግድ ከሁለት እስከ 2.5 ከመቶ ባለው መጠን ብቻ ማደጉም ተፅዕኖውን እንዳጎላው ይተነትናሉ፡፡
የቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚታየው መዋዠቅና የመገበያያ ገንዘብ የምንዛሪ ለውጥ አፍሪካን ብቻም ሳይሆን በርካታ በሸቀጥ ንግድ ላይ የተመሠረተ የወጪ ንግድ ያላቸውን አገሮች እንደሚነካካ ምሁሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አሳይተዋል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ ከዚህ ቀደም ያድግበት የነበረውን ስምንት ከመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በመግባት፣ ምርቶቻቸውን ከዚህ ቀደም ኤክስፖርት ያደርጉበት ከነበረው መጠን በመቀነስ ሳቢያ ቻይኖች የፈጠሩት ኢኮኖሚያዊ ጫና ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ይህ በተለይ ከአሜሪካው የዶላር የመግዛት አቅም ማንሰራራት ጋር በተያያዘም ቻይኖች የወሰዱት ዕርምጃ ተደርጎ ታይቷል፡፡ ቻይና ከውጭ ትገዛቸው የነበሩ ምርቶች መጠን በመቀነሳቸው ሳቢያም እየታየ ያለው የዓለም ኢኮኖሚ መዋዠቅ እንዲስተካከል፣ ያደጉ አገሮች ፍጆታቸውን በመጨመር እንዲያተካክሉ በአንክታድ ተጠይቀዋል፡፡
ቻይና በዚህ ዓመት በወሰደቻቸው መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎች ሳቢያ በርካታ አገሮች ለመዋዠቅ ተገደዋል፡፡ የምንዛሪ ለውጥ በማድረጓ ብቻ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚከሰት ምሁራን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሪፖርተር የቻይና የምንዛሪ ለውጥ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በማስመልከት ትንታኔ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ይፋ ያደረገው ሪፖርትና ከዚህ ትንታኔ ጋር ተጓዳኝ በመሆኑ የቻይና ዕርምጃና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመረዳት ጥቂት ወደኋላ መለስ ብለን እንቃኝ፡፡
ቻይና የመገበያያ ገንዘቧ የሆነውን ዩዋን የመግዛት አቅም በአራት ከመቶ እንዲቀንስ ማድረጓን ተከትሎ፣ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ዕርምጃውን ጥሩም መጥፎም ዕድል ሆኖላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ ቻይና ያልተጠበቀ የተባለውን የምንዛሪ ለውጥ ካደረገች ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች፡፡ የአፍሪካ ተንታኞች የነገርየውን አሳሳቢነት እንዲያስረዱ ይጠበቃሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ተንታኞች ግን የቻይና ዕርምጃ ያንቀጥቅጥ ደረጃ ላይ ባይደርስም ንዝረቱ ለአፍሪካ መሰማቱ ግን አልቀረም እያሉ ነው፡፡
የምንዛሪ ለውጥ ማለት ምን እንደሆነ ለማየት በአጭሩ ከዚህ ቀደም አንድ ዶላር ለመግዛት ያስፈልግ የነበረው የቻይና ገንዘብ 6.39 ዩዋን ነበር፡፡ አሁን በተደረገው ለውጥ ምክንያት አንድ ዶላር በ6.90 ዩዋን ይገዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዶላር መግዛት የፈለገ የቻይና ነጋዴ ወይም ቱሪስት ይህንኑ ያህል ዩዋን መክፈል አለበት ማለት ነው፡፡
የቻይና አድራጎት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የአምራች ኢንዱስትሪዋን የወጪ ንግድ ለማሻሻል ብቻም ሳይሆን ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግ ማለት ከሚገባው በላይ በፍጥነት በመቀነሱ ልጓም ለማበጀት የወሰደችው ዕርምጃም ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የዶላር እየበረታ መምጣት የመግዛት አቅሙ እያሻቀበ መጓዝ፣ የቻይናውን ዩዋን እንዲጠነክር አስገድዷል የሚሉ ተንታኞች እንደሚያምኑት፣ ቀስ በቀስ የቻይና ምርቶች እየተወደደ ከመጣው የሰው ኃይላቸው ጭምር ገበያ ላይ እንደበፊቱ ርካሽ ሆነው እንደ ልብ አገሮችን ከማጥለቅለቅ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡
የቻይና መንግሥት የኢኮኖሚውን መቀዛቀዝ በመመልከት የወሰደው የምንዛሪ ለውጥ በአፍሪካ ጉዳቱ አመዝኖ ታይቷል፡፡ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው የቻይና መገበያያ ገንዘብ ከሌሎች መገበያያ ገንዘቦች አኳያ የመግዛት አቅሙ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ የቻይና ምርቶች ይበልጥ በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካ ምርቶች ለቻይና ገበያ ውድ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ለቻይና የምትሸጠው ሰሊጥ ከወትሮው ዋጋው ውድ ስለሚሆን ቻይና እንደ ቀድሞዋ ላትገዛ ትችላለች ማለት ነው፡፡ በአንፃሩ የቻይና ሸቀጦች ለኢትዮጵያ ገበያ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ርካሽ ይሆናሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገበያ ሰሌዳ የሚያሳየው ከ30 እስከ 70 ብር በኩንታል ጭማሪ መኖሩን ነው፡፡ እስካሁን የምንዛሪ ለውጡ ትኩሳት ገና አልተሰማም ማለት ነው፡፡ ይህ ቢባልም ግን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሰሊጥ ነጋዴዎች፣ ዋጋው በሃምሳ ከመቶ እየወረደ እንደሚገኝ፣ የቻይና የምንዛሪ ለውጥም የመግዛት ፍላጎትን ይበልጥ እንዲቀንስ በማድረግ የገበያው ዋጋ ላይ ይበልጥ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡
ይህንን ትንታኔ ከሚስማሙት መካከል ፕሮፌሰር ዶቦራ ብራውቲጋም ይጠቀሳሉ፡፡ ፕሮፌሰሯ በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በአድቫንስድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ ትምህርት ቤት፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፕሮፌሰር ከመሆናቸው ባሻገር በትምህርት ቤቱ የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ኃላፊም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቻይና አፍሪካ ምርምር ተቋምንም ይመራሉ፡፡ ፕሮፌሰሯ በቅርቡ ለሲኤንኤን በሰጡት ትንታኔ መሠረት፣ በቻይና ገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው መካከል ተመድባለች፡፡ የቻይና ኩባንያዎችም ሆኑ ቻይናውያን ሸማቾች ከአፍሪካ በዶላር የሚገዟቸው ሸቀጦች ውድ እየሆኑ ስለሚመጡ የመግዛት ፍላጎታቸው ይቀንሳል፡፡ ሆኖም ግን የቻይና የምንዛሪ ለውጥ የኢኮኖሚዋን ዕድገት እንዲያንሰራራ የሚያደርገው ከሆነ ከአፍሪካ ሸቀጦችን የመግዛት ፍላጎት እንዲጨምር የማድረግ ዕድል እንደሚፈጠር ይታሰባል፡፡ ዋጋቸውም ይሻሻል፡፡ አፍሪካውያንም በርካሽ ዋጋ የቻይና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ ስማርት ስልኮችንና አልባሳትን በገፍ ይገዛሉ፡፡ በርካሽ ዋጋ ከቻይና ብረት መግዛት ይቻላል፡፡
ይህ መሆኑ ለአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪ አደጋ ይሆናል ሲሉ ፕሮፌሰር ዲቦራ ይመክራሉ፡፡ ለአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብቻም ሳይሆን ቻይናውያን ቱሪስቶችም ወደ አፍሪካ መምጣቱ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ውድ ስለሚሆንባቸው እዚያው አገራቸው መዝናናቱን ሊመርጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ከቻይና ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢንቨስተሮች ዶላር ለማግኘት የሚያወጡት የቻይና ገንዘብ በመጨመሩ ሳቢያ የመምጣታቸው ነገር ብዙም አያወላዳም፡፡
ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ርካሽ የሰው ጉልበት እንዳላት ስትሰብክ፣ ዓለምም ይህንን ሲቀበልና የውጭ ኢንቨስተሮች ቢመጡ እንደሚያዋጣቸው ሲገነዘብ እንደነበር ቢታወቅም የአሁኑ የቻይና ዕርምጃ ግን ይህንንም ወደ ጎን የሚያደርግ ሆኖ ሊገኝ ይችላል እየተባለ ነው፡፡ በቻይና የሰው ጉልበት ውድ እየሆነ በመምጣቱ ፋብሪካዎች እየነቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሲወተወቱ፣ የቻይና ምሁራንም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል፡፡ የምንዛሪው ለውጥ ግን የቻይና ግብዓቶችን ከወትሮው ዋጋቸው ቅናሽ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ ነቅሎ መምጣቱን እንዳይመርጡ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡ እርግጥ እስካሁንም ይጠበቅ እንደነበረው ያለ የቻይና ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ኢንቨስት ካደረገችው ይልቅ ብድር በማቅረብ በምትገነባቸው መሠረተ ልማቶች የገዘፈ ስም አላት፡፡ በኢንቨስትመንት ረገድ ቱርክ ብቻዋን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረገችው ቻይና በአፍሪካ በጠቅላላው ካካሄደችው ኢንቨስትመንት የበለጠ ሆኖ ይገኛል፡፡
በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ነቅለው ይመጣሉ የሚል እምነት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ መሠረተ ልማቶችን ሲገነባ ከርሟል፡፡ ቻይና የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደምትደግፍ፣ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ድጋፍ እንደምትሰጥ ደጋግማ ከመግለጽ በቀር የቻይና ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጣበት መጠን ከቻይና ወገን ሲነገር ብዙም አይደመጥም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ ስብሰባዎች ቻይናውያኑ ሲናገሩ የሚደመጠው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ ዋናው ምክንያታቸው የመንግሥት ቢሮክራሲና አሠራር ጎታታነት ነው፡፡ የጉምሩክ ጣጣዎችን ያነሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ ሌሎች አገሮች ኢንቨስት ያደረጉትን ያህል ቻይናውያን ኢንቨስት አላደረጉም፡፡ በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የቻይና አፍሪካ ፎረም ላይ መንግሥት ከቻይና የሚመጣው ኢንቨስትመንት እየጨመረ እንዲመጣ ለማድረግ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
የምንዛሪ ለውጡ ሰበቦች
ቻይና የገንዘብ ምጣኔ ለውጥ ለማድረግ የተገደደችባቸው ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ የኢኮኖሚዋ መቀዛቀዝ አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ ወዲህ እያስገመገመ የመጣው የቻይና ኢኮኖሚ፣ ለመጋጋሙ ምክንያት የሆነው ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ፣ ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው ርካሽ የኤክስፖርት ዘርፍ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ቻይና መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ናት፡፡ የዓለም ባንክ ባስቀመጠው መለኪያ መሠረት በዚህ ረድፍ የሚመደቡ አገሮች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከአራት ሺሕ እስከ 12 ሺሕ ዶላር ነው (ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ለመሰለፍ ማቀዷን ልብ ይሏል፤ ይህም የነፍስ ወከፍ ገቢዋ በዝቅተኛው ረድፍ ከአንድ ሺሕ እስከ አራት ሺሕ ዶላር ባለው ክልል ውስጥ ይሆናል)፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ካለበት ደረጃ ለመድረሱ በብዛት እየተስፋፋ የመጣው አገር ውስጥ ፈጠራ፣ የአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲሁም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ምርቶችን በገፍ ኤክስፖርት ለማድረግ መቻላቸው ሁሉ ተደማምሮ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻላቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች ከቻይና ውጭ ኢንቨስት የማድረግ አቅምን ፈጠረላቸው፡፡
የቻይና መፈርጠምና የውጭ ኢንቨስትመንት ማብዛት አፍሪካን ጠቅሟል የሚሉት ፕሮፌሰር ዲቦራ፣ የቻይና ኢኮኖሚ ተስፋፊነትና ዕድገት የውጭ መጠባበቂያ ክምችቷን አበራክቶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ በምዕራቡ ዓለም ባንኮች የተከማቹ ተቀማጭ ሒሳቦችን ወደ ብድርነት እንዲቀየሩ በማድረግ በአፍሪካ በርካታ የመሠረተ ልማቶችን ፋይናንስ ለማድረግ አስችሏታል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት ለአፍሪካ ሸቀጦች ዋጋ መሻሻልም ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ምንም እንኳ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ለቻይና ያደላም ቢሆን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ዓምና የነበረው የንግድ ግንኙነት 220 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ይህ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ከሚካሄደው የንግድ ግንኙነት ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የአፍሪካ አምራቾችን ከጉዳት አልታደገም፡፡ የቻይናን ርካሽ ምርቶች መፎካከር የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው፣ አገሮች በቻይና ምርቶች መጥለቅለቃቸውን ሊገቱ አልቻሉም፡፡
የአፍሪካ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ቻይኖቹ የምንዛሪ ለውጡን ለማድረግ የተገደዱት የዶላር እየበረታ መምጣት የዩዋንን የመግዛት አቅም በግድ እንዲጨምር ስላስገደደው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት በተለይ ዩዋን በ14 ከመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ የተገደደው የዶላር አቅም መጎልበት በፈጠረው ጫና ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ በታየው ለውጥ ሳቢያ በሐምሌ ወር ብቻ የወጪ ንግዳቸው በ8.3 ከመቶ እንዲቀንስ አስገድዷል፡፡ ይህም የአሜሪካ የተወዳዳሪነት አቅም ያመጣው ጫና ነበር፡፡ በዚህ ሳያበቃም በርካታ የቻይና ፋብሪካዎች ምርት ከማቆም አልፈው ሠራተኞችን እስከማሰናበት እንዲደርሱ አስገድዷቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቀናት በፊት የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ የቻይናን የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ አስችሎታል፡፡ በአንፃሩ የወርቅ፣ የድፍድፍ ነዳጅ፣ የመዳብ፣ የፕላቲኒየም እንዲሁም የጠገራ ብረት ገበያና ዋጋ እንዲቀንሱ አስገድዷል፡፡ በተንታኟ መሠረት የደቡብ አፍሪካ ማዕድን ዘርፍ ከአሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ለማሰናበት አስገድዶታል፡፡ ሌሎችም ከአፍሪካ የሚላኩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንሱ ሰበብ ሆኗል፡፡ ሆኖም ተስፋ አለ፡፡ እንደ ፕሮፌሰሯ ግምት በመካከኛ ጊዜ የቻይና ኢኮኖሚ ካንሰራራ ለአፍሪካ ሸቀጦች የሚኖረው ፍላጎት ስለሚጨምር ዋጋው እንደሚያንሠራራ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚ በፍጆታ (በተለይ በአገልግሎት መስክ በሚታዩ ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች) እና በመንግሥት የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አማካይነት የሚካሄዱ ግንባታዎች የየኢኮኖሚዎቹን 60 ከመቶ ድርሻ እንደያዙ ያብራሩት ዶ/ር ተስፋቸው፣ ከመነሻው መንግሥታት የሚያደርጋቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ወሳኝ መሆናቸውንና እነ አሜሪካም ሆኑ የአውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ሲጀምሩ በመንግሥት አማካይነት በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የተመድ የዚህ ዓመት የንግድና የልማት ሪፖርት፣ በዕዳ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አሠራር፣ በዓለም ፋይናንስ ገበያ ላይ በሚታዩ ችግሮችና እያስከተሉ በሚገኙት ጫና ላይ ትንተና በማቅረብ ይበጃል ያላቸውን መፍትሔዎች አስቀምጧል፡፡ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ያልተገራ አሠራር ግሪክን አዘቅት ውስጥ በመክተት ሕዝቧን ለዕዳ ሸክም ከዳረገ ሰንበትበት ማለቱን የጠቀሱት ዶ/ር ተስፋቸው፣ አቴንስ ላስተናገደችው የዓለም ኦሎምፒክ ውድድሮች ዝግጅት የተበደረችውን በርካታ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የምትመልስበትን ዘዴ ባለመወጠኗና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሻሻጭ ድርጅቶች ጫና ሳቢያ አሁን ለምትገኝበት ቀውስ መዳረጓን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡