Friday, September 22, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ካቢኔያቸውን መሠረቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

– ብአዴን ኦሕዴድና ደኢሕዴን በእኩል ተወክለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. የአገሪቱ ጠቅላይ ሆነው በድጋሚ በተመረጡ በማግሥቱ፣ 30 አባላትን የያዘ ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ አፀድቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካፀደቁት 30 አባላትን የያዘ ካቢኔ ውስጥ 12ቱ ብቻ በቀድሞው ካቢኔ ውስጥ ያልነበሩ ሲሆኑ፣ የቀሩት 15ቱ በነበሩበት ሥልጣን የቀጠሉ የቀድሞ ካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ በሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተዘዋወሩ የቀድሞ ካቢኔ አባላት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው የካቢኔ አባላት ውስጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እያንዳንዳቸው በአዲሱ ካቢኔ ስምንት ተወካዮቻቸው ተመርጠዋል፡፡

ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) አራት አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ሲካተቱ፣ የአፋርና ሶማሌ ክልል አብዴፓና ሶሕዴፓ የተባሉት የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች አንድ አንድ አባሎቻቸውን በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ካቢኔ ውስጥ ተካተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት አቶ ደመቀ መኰንንን በድጋሚ አቅርበው አሹመዋል፡፡ አቶ ደመቀ የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው እንደሚሠሩም ታውቋል፡፡

የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የመገናኛ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አድርገው አሹመዋል፡፡

በተመሳሳይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ሆነው እንዲሠሩ፣ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን ወ/ሮ አስቴር ማሞን አሹመዋል፡፡

አቶ ደመቀ በፖለቲካ ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ዶ/ር ደብረ ጽዮን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ደግሞ በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪና በተቋማዊ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ (ደኢሕዴን)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴድሮስ አድሃኖም (ሕወሓት)፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ (ብአዴን) በድጋሚ የያዙትን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡ አቶ ሲራጅ በሰላምና ፀጥታ የማተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ዶ/ር ቴድሮስ በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ፣ አቶ ጌታቸው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪና በተቋማዊ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡

አቶ አህመድ አብተው (ብአዴን)፣ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ (ኦሕዴድ)፣ አቶ ሽፈራው ሸጉጤ (ደኢሕዴን) እንደ ቅደም ተከተላቸው ሲመሯቸው የነበሩ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርትና የትምህርት ሚኒስቴሮችን በሚኒስትርነት እንዲመሩ በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡

አቶ አህመድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸው በኢኮኖሚክስ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸው በተቋማዊ አስተዳደር አግኝተዋል፡፡ አቶ ሽፈራው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋማዊ አስተዳደር ያገኙ ሲሆን፣ አቶ ወርቅነህ ደግሞ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡

አቶ ቶሎሳ ሻጊ (ኦሕዴድ)፣ ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ (ደኢሕዴን)፣ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ (ሶሕዴፓ)፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ (ብአዴን) በተመሳሳይ በነበሩባቸው የሚኒስቴር ኃላፊነቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስትር፣ እንዲሁም የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስትር ሆነው እንደ ቅደም ተከተላቸው ተሹመዋል፡፡

አቶ ቶሎሳ በሚኒስትርነት ይመሩት የነበረው የማዕድን ሚኒስቴር ላይ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ጉዳዮችን የተመለከቱ መዋቅሮች እንዲካተቱባቸው የተደረገ ሲሆን፣ ወ/ሮ ዘነቡ ይመሩት በነበረው የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ላይ የወጣቶች ጉዳይ ተቀንሶ እንዲዋቀሩ ተደርገዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሚኒስትሮች አቶ ቶሎሳ ሻጊ በጂኦሎጂ መስክ የተማሩ ሲሆን፣ ዶ/ር ከሰተ ብርሃን በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ ደግሞ በማኔጅመንትና ቢዝነስ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ በተቋማዊ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡

መጠነኛ የመዋቅር ማስተካከያ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር አንዱ ሲሆን፣ ለሁለት እንዲከፈል ተደርጐ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተብሎ በአንድ መልክ የተዋቀረ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ሚኒስቴር ሆኖ ተደራጅቷል፡፡

የቀድሞ የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው (ብአዴን) የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ ተፈራ በአፈርና ውኃ ጥበቃ የማስትሬት ዲግሪ፣ እንዲሁም በእርሻ ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ በቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር የአቶ ተፈራ ምክትል ሆነው በሚኒስትር ዴኤታነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታሁን (ኦሕዴድ) የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ ስለሺ በእርሻ ምሕንድስና የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡

መዋቅራዊ ማስተካከያ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ይገኙበታል፡፡ በመዋቅራዊ ለውጡ መሠረትም እንደ ቅደም ተከተላቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሆነው ተደራጅተዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ አብዱላዚዝ አህመድ (ኦሕዴድ) የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርን እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡ አቶ አብዱላዚዝ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በሥራ አመራር አግኝተዋል፡፡ የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን (ብአዴን) ወደ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በመምጣት ለፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ አቶ ካሳ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋማዊ አስተዳደር አግኝተዋል፡፡

ሌላው መዋቅራዊ ማስተካከያ የተደረገበት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሲሆን፣ ለሁለት እንዲከፈል ተደርጐ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴርና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሆነው ተደራጅተዋል፡፡ የቀድሞው ሚኒስትር አቶ ኃይሌ መኩሪያ (ደኢሕዴን) አዲስ ለተደራጀው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ ኃይሌ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ንግድ የያዙ ሲሆን፣ በተጨማሪም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተመርቀዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሆኖ የተደራጀውን አዲስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በአማራ ክልል በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና ሌሎች ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኰንን (ብአዴን) ተሹመውበታል፡፡

ዶ/ር አምባቸው በኢኮኖሚክስ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ተምረዋል፡፡ እርሳቸው እንዲመሩት የተመሠረተው አዲሱ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትን በማደራጀት የግንባታው ዘርፍ ጥረትን እንዲያረጋግጥ፤ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር በዘርፉ እንዲመጣ ይሠራል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ሌላው በድጋሚ እንዲዋቀር የተደረገው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆን፣ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ የሚል አዲስ መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ከነዳጅ ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶቹ ወደ ማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ተሸጋግሯል፡፡ ይህንን ሚኒስቴር ይመሩ በነበሩት አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ምትክ አቶ ሞቱማ መቃሳ (ኦሕዴድ) ተሹመዋል፡፡

አቶ ሞቱማ በስታትስቲክስ ሙያ የተመረቁ ሲሆን፣ በውኃ ሀብት ዙሪያ የተለያዩ ኮርሶችን እንደወሰዱ በሹመታቸው ወቅት ተገልጿል፡፡ አቶ ሞቱማ ቀደም ሲል በኦሮሚያ የውኃ ሀብት ቢሮ የተለያዩ ኃላፊነቶች ይሠሩ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይም የቡራዩ ከተማ ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ሹመታቸውን እስኪያገኙ ድረስ በድጋሚ የኦሮሚያ ውኃ ሀብት፣ እንዲሁም የማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ለረጅም ዓመታት በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የቡና ዘርፍን ሲከታተሉ የነበሩትና በንግድ ሚኒስቴር የቡና ዘርፍ ገበያን ሲከታተሉ የነበሩት አቶ ያዕቆብ ያላ (ደኢሕዴን) የንግድ ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት የሠሩበት የቡና ዘርፍ ግን ወደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተጠሪ በሚሆነው የቡናና ሻይ ልማት ኤጀንሲ እንዲዘዋወር ተደርጓል፡፡ አቶ ያዕቆብ ያላ በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡         

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆነው የተመረጡት አቶ አብይ አህመድ (ኦሕዴድ) ናቸው፡፡ አቶ አብይ በመከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ አገልግሎት ውስጥ እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፣ በኋላ ላይ በመረጃ መረብ ደኅንነት በዳይሬክተርነት፣ ቀጥሎም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡

አቶ አብይ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በተቋማዊ አመራር የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩን አቶ አሚን አብደልቃድርን የተኳቸው ደግሞ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ሙሳ (አብዴፓ) ናቸው፡፡ ኢንጂነር አይሻ በአፋር ክልል የተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በትምህርታቸው በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ በተቋማዊ አመራር የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ደግሞ ወደ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ የተሾሙበት ተቋም በአዲስ መልክ በሚኒስቴርነት የተደራጀው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ነው፡፡

ይህ ተቋም የመንግሥት ልማት ድርጅቶችንና ግዙፉን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ፣ የኮርፖሬት አስተዳደርና ፋይናንስ ጤናማነትን እንደ ኦዲተር መሥሪያ ቤት መከታተልና ዕርምጃ መውሰድን ይጠይቃል፡፡ ወ/ሮ ደሚቱ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡

የቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም (ደኢሕዴን) በበኩላቸው የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሆኖ በድጋሚ በተዋቀረው ተቋም በሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ ዶ/ር ሽፈራው በሕክምና ዶክትሬት ያላቸው ሲሆን፣ ለረዥም ዓመታት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዴኤታነት ያገለገሉ ናቸው፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን (ደኢሕዴን) የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሆኖ በአዲስ ወደተቋቋመው ተቋም በሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡

አቶ ሬድዋን በሥነ ሕይወት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በተቋማዊ አስተዳደር የማስትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የካቢኔ አባል እንዲሆኑ የተሾሙት ደግሞ አቶ በከር ሻሌ (ኦሕዴድ) የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ጌታቸው ረዳ (ሕወሓት) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ዶ/ር ይናገር ደሴ (ብአዴን) የፕላኒንግ ኮሚሽን ኃላፊ፣ እንዲሁም አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ (ሕወሓት) በፓርላማ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -