ከአንደ ወር በፊት ባጋጠመ የካሜራ (CCTV Camera) ብልሽት ለ29 ቀናት በቃሊቲ የአሽከርካሪዎች የተግባር ፈተና ተቋርጦ እንደነበርና በመጨረሻ ፈተናው እንደቀድሞው በሰው መሰጠት መጀመሩን፣ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ኦፕሬሽን ዋና ሥራ ሒደት መሪ አቶ ወጋየሁ አሰፋ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት በካሜራ ይካሄድ የነበረው የአሽከርካሪዎች የተግባር ፈተና ለ29 ቀናት በመቋረጡ፣ በቀን የሚካሄደው እስከ 285 የሚሆኑ የአሽከርካሪዎች የተግባር ፈተና መካሄድ ባለመቻሉ፣ በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ 5,400 የሚሆኑ ሰዎችን መፈተን ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል፡፡
የመጠባበቂያ ካሜራዎችን መጠቀም ወይም የተበላሹትን ካሜራዎች በፍጥነት ማስጠገንን በሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹የተወሰኑት ካሜራዎች ሲበላሹ ቀሪዎቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻ ሁሉም ካሜራዎች የቴክኒክ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ለካሜራዎቹ መጠገን አስፈላጊ የሆነው መለወጫ ዕቃ በአገር ውስጥ ስለሌለ በውጭ አገር እየተፈለገ ነው፤›› ነው ብለዋል አቶ ወጋየሁ፡፡
ካሜራዎቹን የገጠማቸው የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA) እንደሆነና አሁንም መለወጫ ዕቃዎቹን እየፈለገ ያለው ይኼው ኤጀንሲ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አስፈላጊው ዕቃ በቀላሉ ሊገኝ ያልቻለው ቴክኖሎጂው እየተቀየረ በመሄዱና ለአሽከርካሪዎች የተግባር ፈተና ሲውል የነበረው ካሜራ ትንሽ የቆየ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡
የተፈጠረውን የተፈታኞች ቁጥር ክምችት ለመቀነስና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ወደ ቀድሞ አሠራር መመለስ ግድ እንደነበርና እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደመከሩበት ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በአሁኑ ወቅት የአሽከርካሪዎች የተግባር ፈተና በሰዎች የሚሰጥ ቢሆንም፣ የፈተና አሰጣጡ ከቀድሞ የተለየ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አቶ ወጋየሁ እንደሚገልጹት ፈተናው እንደ ቀድሞው ፈታኝና ተፈታኝ አንድ መኪና ውስጥ ሆነው የሚሰጥ ሳይሆን፣ አንድ ሰው በስድስት ወይም በሰባት ሰዎች የሚመዘንበት ነው፡፡ ፈታኝና ተፈታኝ ሳይገናኙ የፈተናውን አሰጣጥ መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል ሲስተም ተዘርግቷል ብለዋል፡፡
አስፈላጊዎቹ መለዋወጫዎች መቼ ተገኝተው በካሜራ ወደ መፈተን አሠራር መመለስ እንደሚቻል መገመት እንደማይችሉ የሥራ ሒደት መሪው ገልጸዋል፡፡