Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ በለሁሉ በኩል እንዲሰበሰብ ተደረገ

የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ በለሁሉ በኩል እንዲሰበሰብ ተደረገ

ቀን:

‹‹ክፍያው በድብቅ እንዲሰበሰብ መደረጉ ደንበኛን ማታለል ነው›› የኮርፖሬሽኑ ደንበኞች

‹‹ክፍያው በድብቅ ሳይሆን በፈቃደኝነት በግልጽ የሚፈጸም ነው›› የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከደንበኞቹ ላይ የሚሰበሰበውን ዓመታዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ፣ በ‹‹ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› (ለሁሉ) በኩል እየሰበሰበ ነው፡፡ ክፍያው በለሁሉ በኩል እንዲሰበሰብ መደረጉና ኮርፖሬሽኑም ለደንበኞቹ አለማሳወቁ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ‹‹ደንበኞችን ማታለል ነው›› ሲሉ፣ ክፍያው እየተሰበሰበ መሆኑን ያወቁ ደንበኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ክፍያው የሚፈጸመው በድብቅ ሳይሆን ደንበኞቹ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የስልክ ወርኃዊ ክፍያ ሊፈጽሙ ሲሄዱ፣ በአስከፋዩ ማኅበር ሠራተኞች  ተነግሯቸው በፈቃደኝነት የሚከፈል መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የኮር ቢዝነስና ፋይናንስ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ደመረ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ወይዘሮ አስቴር ዮሐንስ የተባሉ የኮርፖሬሽኑ ደንበኛ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞች አሉት፡፡ ዘወትር በሚያደርገው ውትወታ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ክፍያ እየፈጸሙ መሆኑን በመጠቆም፣ እንደፈለገው ክፍያው ካልተሰበሰበለት በእጁ በሆነው ቴሌቪዥን የክፍያ ሲስተሙን በመቀየር በለሁሉ በኩል ማድረጉን ማሳወቅ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡ በከተማ ውስጥ የሚኖር ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በተለይ የውኃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ወርኃዊ ክፍያ የማይፈጽም እንደሌለ የገለጹት ወይዘሮ አስቴር፣ በርካታ ቤተሰቦች ክፍያ የሚፈጽሙት ‹‹ይህንን ያህል ቆጥሯል›› በሚለው እንጂ፣ አስከፋዮቹ እያንዳንዱ አገልግሎት ምን ያህል እንደቆጠረባቸው አስረድተዋቸው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹ በምን ሁኔታና እንዴት እንደሚከፈል ማብራሪያ ሳይሰጥ ዝም ብሎ ክፍያው እንዲፈጸም ማድረግ ደንበኛን ማታለል ወይም መናቅ ሆኖ እንደሚሰማቸው አስረድተዋል፡፡ እሳቸውም ሥራዬ ብለው አስበውበት ሳይሆን፣ የአንድ ወር ክፍያ ከፍተኛ ሆኖ ስለመጣባቸው ቢሉን በትኩረት ሲመለከቱ ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን›› የሚል ጽሑፍና ‹‹EBC›› የሚል ሎጐ በማየታቸውና በመጠየቃቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከፈልና ከ50 እስከ 80 ብር ሊደርስ የሚችል ክፍያ መሆኑን የሚገምቱ ቢሆንም፣ በየወሩ በለሁሉ በኩል ስንት እየከፈሉ እንደሆነ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቆ የክፍያውን መጠንና ቴሌቪዥን የሌላቸው እንዴት ተለይተው ክፍያ እንደሚፈጸም ማስረዳት እንደሚኖርበት ወይዘሮ አስቴር አሳስበዋል፡፡ ሌሎች ደንበኞችም የወይዘሮ አስቴር ዓይነት አስተያየትና ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለምን ለደንበኞቹ ሳያሳውቅ የክፍያ ሲስተሙን በለሁሉ በኩል ሊያደርግ እንደቻለ ተጠይቆ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የኮር ቢዝነስና ፋይናንስ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ደመረ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ክፍያው በለሁሉ በኩል እንዲሰበሰብ ከተደረገ ስድስት ወራት አካባቢ ሆኖታል፡፡ ክፍያው በግዴታ የሚፈጸም ሳይሆን በፈቃደኝነት ነው፡፡ በሌላ በኩል እንዲደረግ የተፈለገው፣ ለሁሉም ተደራሽነቱ ከፍተኛ ስለሆነና የቴሌቪዥን አገልግሎት የማያገኝ አለ ተብሎ ስለማይታሰብ የክፍያ ሲስተሙ በዚያ በኩል እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

ክፍያ የሚያስፈጽሙት የማኅበሩ ሠራተኞች ለደንበኞቹ ስለሚገልጹ፣ የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱበትን ጊዜ ለመቆጠብና ከሌላ ክፍያ ጋር በቀላሉ እንዲከፍሉ ለማድረግ እንጂ ደንበኞችን ለማታለል ወይም በመናቅ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቴሌቪዥን የሌለውና በአንድ ቤት ከአንድ በላይ ቴሌቪዥን ያለው ደንበኛ እንዴት ሊስተናገድ እንደሚችል የተጠየቁት አቶ ደመረ፣ ደንበኛው ራሱ ያለውን ተናግሮ ይከፍላል በሚል ዕምነትና የሌለውም እንደሌለው አሳውቆ ክፍያ እንደማይፈጽም ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ደንበኞቹን በማስተማር እንጂ ኮርፖሬሽኑ በማስገደድ ክፍያ እንደማይሰበስብም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...