Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነት 40 ዓመት ሞላው

  የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነት 40 ዓመት ሞላው

  ቀን:

  የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ጽሕፈት ቤት ባለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድና በኢነርጂ ልማት፣ በጤና፣ በዘላቂ የእርሻ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና በምግብ ዋስትና፣ እንዲሁም በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያበረታት ሥራ ማከናወኑን፣ የልዑኩ መሪ አምባሳደር ሻንታል ሔበርት ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

  አምባሳደሯ ይህን ያስታወቁት ኅብረቱና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩበትን 40ኛ ዓመት ለማክበር፣ የኅብረቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከጋዜጠኞች ጋር በልዑኩ ዋና ጽሕፈት ቤት ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

  በውይይቱ ወቅት በተለይ ኅብረቱ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚሠራቸው እንቅስቃሴዎች ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ኅብረቱ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ በተለይ በመንገድ እንዲሁም ሲቪል ማኅበረሰብን በማጠናከር ላይ የሠራቸውን ሥራዎችና ውጤቶችን የተመለከቱ ማብራሪያዎችም ተሰጥቷል፡፡

  ኅብረቱ በኢትዮጵያ በነበረው የ40 ዓመታት ቆይታ ማሳካት የቻለው ዋነኛ ግብ ምን ነበር በሚል ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹በዋነኛነት ከመንግሥት ጋር ጠንካራና ገንቢ አጋርነት መመሥረት መቻል የሚለው ነው፤›› ሲሉ አምባሳደሯ አስረድተዋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የመንገድ ልማት ዘርፍ፣ የትምህርትና የጤና መስኮች ኅብረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተባቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡

  ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች ጋር በተገናኘም ኅብረቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንደተጫወተ አምባሳደሩ ገልጸው፣ ‹‹በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማትን ማለትም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን፣ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴርን ማጠናከር ኅብረቱ አስተዋጽኦ ያበረከተባቸው ሌላኛው የስኬታችን መስክ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የኅብረቱ ቀዳሚ የትብብር መስኮች የመንገድና ኢነርጂ ልማት፣ ጤና፣ ዘላቂ የእርሻ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ፣ የምግብ ዋስትና፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችና እገዛ የሚያስፈልጋቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት እንደሆኑ ተገልጾ፣ እነዚህንም ተፈጻሚ ለማድረግ በ11ኛው የልማት ፈንድ አማካይነት እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ ጥቅም ላይ የሚውል 745 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡም ተጠቁሟል፡፡

  ኅብረቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ 200 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ በማድረግ የሰብዓዊ ዕርዳታና የፕሮጀክት እገዛ ማድረጉም እንዲሁ ተገልጿል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ ግንኙነት በ1975 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረ ሲሆን በዚያው ዓመት ኅብረቱ የሁለትዮሽ ልዑኩን ጽሕፈት ቤት በግዮን ሆቴል ቅጥር ጊቢ ውስጥ በመክፈት አሁን ወዳለበት ደረጃ ደርሷል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...