መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አፈ ጉባዔ በመምረጥ አምስተኛ ዘመን ሥራውን የጀመረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለተኛ ቀን ውሎው፣ በፌዴራልና የክልል መንግሥታት መካከል ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነት የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣት ወሰነ፡፡
ምክር ቤቱ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በመጀመርያ ጉባዔው አቶ ያለው አባተን በአፈ ጉባዔነት የመረጠ ሲሆን፣ አቶ መሐመድ ረሻድን በምክትል አፈ ጉባዔነት እንዲቀጥሉ መርጧቸዋል፡፡ በማግሥቱ መስከረም 25 ቀን ባካሄደው ጉባዔው የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2008 ዕቅድ አዳምጧል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴዎቹ መካከል የዴሞክራሲ አንድነት፣ የሕገ መንግሥት አስተምህሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዕቅድ ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡
በአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሥልጣንና ኃላፊነቶች ያሏቸው ቢሆንም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ደግሞ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚገባ ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግግ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ለመፍጠር ክልሎችና የፌደራል መንግሥታት የሚደጋገፉበትና የሚቀራረቡበት ሁኔታን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል፡፡
ይኼ ግንኙነት ግን በተደራጀ መልኩ መመራት ያለበት በመሆኑ፣ ግንኙነቱ የሚመራበት የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ የግድ ስለሆነ ማዕቀፉ በ2008 ዓ.ም. በማዘጋጀት ሕጉ እንዲወጣ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡