Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው ጨረታ ታገደ

ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው ጨረታ ታገደ

ቀን:

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶችን ለመግዛት ያወጣውን ጨረታ አገደ፡፡ ኤጀንሲው ጨረታውን ያገደው መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ጨረታው የታገደው በጨረታው ተሳታፊ የሆነው አግታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡

አግታ መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ቅሬታውን በደብዳቤ አቅርቧል፡፡ አግታ ባቀረበው አቤቱታ ትምህርት ሚኒስቴር የመንግሥትን የግዥ አዋጅ በተፃረረ መልኩ ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበ ኩባንያ ሥራው መሰጠቱን ተቃውሟል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከሰባት ወራት በፊት አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶች ግዥ ለመፈጸም ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ በጨረታው አራት ኩባንያዎች ቢሳተፉም፣ አንዱ ኩባንያ በቴክኒክ ምክንያት ወዲያውኑ ከጨረታ ውጪ ተደርጓል፡፡ የተቀሩት አግታ፣ ሐግቤስና በላይ አብ ሞተር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

አንድ ሺሕ ሞተር ብስክሌቶች ለማቅረብ አግታ 37 ሚሊዮን ብር ሲያቀርብ፣ ሐግቤስ ኩባንያ ደግሞ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ አቅርቧል፡፡ የአግታ ኩባንያ ቅሬታ ከዚህ የመነጨ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ሞተር ብስክሌቶች ለማቅረብ 13 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መወዳደርያ ገንዘብ ያቀረበ ኩባንያ አሸናፊ መደረጉ አግባብ አይደለም፣ የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት ይፃረራል በማለት የአግታ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማይ  ወልደአረጋይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

“መንግሥትና ሕዝብን ሊከሳራና ለሕገወጥ ወጪ የሚዳርግና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር ያደርጋል፤” በማለት የትምህርት ሚኒስቴር የግዥ ሒደት ሕገወጥ መሆኑን አቶ ግርማይ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የአግታን አቤቱታ በመቀበል ለትምህርት ሚኒስቴር ጨረታውን እንዲያቆም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 75 ንዑስ አንቀጽ 1 የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ አቤቱታ ሲቀርብለት፣ ወዲያውኑ አግባብ ላለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ማስታወቂያ ይልካል፡፡ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስም ማናቸውም ቀጣይ እንቅስቃሴ ወዲያውኑ መቆም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

በዚህ መሠረት የጨረታ ሒደቱ የታገደ ሲሆን፣ በአዲሱ አጠራር በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ የሚመራው የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ የመጨረሻ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ጨረታው በእግድ ይቆያል፡፡

ኤጀንሲው ለትምህርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ዕገዳ ከማስተላለፍ በተጨማሪ፣ የጨረታ ሒደቱ ሙሉ መረጃና ቃለ ጉባዔ እንዲላክለት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ገብረ ሚካኤል በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ