– ተቀጣሪ ላልሆኑ 191 ሰዎች ከ3.3 ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ተከፍሏል ተብሏል
በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የፋይናንስ ኦፊሰር መሆኑ የተጠቀሰው ግለሰብ፣ በድርጅቱ ውስጥ ባልተቀጠሩ ሰዎች ስም የሁለት ወራት ደመወዝ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተላልፏል ተብሎ ከሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊውና ከቤተሰቦቹ ጋር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ፣ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡
የድርጅቱ ሠራተኞች ሳይሆኑ ከ14,000 ብር እስከ 18,000 ብር የወር ደመወዝ ተከፋይ እንደሆኑ በማስመሰል፣ ለ191 ሰዎች የሐምሌ የነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ደመወዝ ከ3.3 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስገባቱን፣ ጉዳዩን በመመርመር ላይ የሚገኘው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
የድርጅቱ የፋይናንስ ኦፊሰር መሆኑ የተገለጸው አቶ ጌታቸው ደበበ የተባለው ተጠርጣሪ፣ 3.3 ሚሊዮን ብር በባለቤቱ የባንክ ሒሳብ ውስጥ ማስገባቱን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ባለቤቱ ደግሞ ገንዘቡን ከባንክ በማውጣት በሁለቱ ስም (በባልና ሚስት) የተከፈተ ሌላ አካውንት ውስጥ ማዘዋወሯን አክሏል፡፡
የገንዘቡን ዱካ ለማጥፋት የአቶ ጌታቸው ባለቤት ለወንድሟ ሚስት ስታስተላልፍ፣ የወንድሟ ሚስት ደግሞ ደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ መካነ ሰላም ለሚገኙት ለአቶ ጌታቸው ባለቤት እናት 2.2 ሚሊዮን ብር በአቢሲኒያ ባንክ አማካይነት ማስተላለፏን መርማሪ ቡድኑ ለተረኛ ችሎቱ አስረድቷል፡፡ 2.2 ሚሊዮን ብር የደረሳቸው የተጠርጣሪ ጌታቸው አማት፣ 1,079,000 ብር መሬት ቆፍረው እንደቀበሩት ቡድኑ አብራርቷል፡፡
የተረፈውን ብር ደግሞ ለአክስታቸው ባል አደራ የሰጡ ቢሆንም፣ የፌዴራል ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ተቆፍሮ የተቀበረውን ገንዘብና የተቀባበሉትን ገንዘብ በመሰብሰብ በማስረጃነት መያዙንም መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሰው ኃይል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ምትኩና የአቶ ጌታቸው ቤተሰቦችም ተጥርጥረው የታሰሩ ሲሆን፣ የዋስትና መብታቸው ታልፎ ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከኤርፖርቶች ድርጅት መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ በመዝረፍ የተጠረጠረ ሠራተኛ መያዙን፣ በመስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡