በአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የካቢኔያቸውን ተሿሚዎች ሹመት አፀድቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡ እሳቸው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የተለያዩ ሴክተሮችን በብቃት ይመራሉ ያሉዋቸውን ተሿሚዎች ይዘው አገሪቱን ለአምስት ዓመታት ይመራሉ፡፡ ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ሹመት በተጠያቂነት መንፈስ ሊሠሩበት ይገባል፡፡ ይህ ሹመት ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነትን ማዕከል ማድረግ አለበት፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ሹመቱ ይሠራበት፡፡
በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚያስነሱ ተጠቃሽ ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሙስና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎንም ደንታ ቢስነት፣ የብቃት ማነስና በፍጥነት እየተለወጠ ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር እኩል መራመድ አለመቻልም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን በማመን እነሱን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም፣ ብዙ ጊዜያት ወስደውበታል፡፡ ቀልጠፍና ቆፍጠን ያለ ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ብሶቶችና ምሬቶች ይሰማሉ፡፡
አሁን ጊዜው የሥራ ነው፡፡ ሹመት የተሰጣቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለውጤታማ ሥራ ሊተጉ ይገባል፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላትና ተሿሚዎች በሕዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉትን በደሎች ማስቆም አለባቸው፡፡ ቢሮክራሲው ካለበት አረንቋ ውስጥ ወጥቶ በአገልጋይነት መንፈስ እንዲሠራ አመራር የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለመደው መንገድ እየተጓዙ ለውጥ መጠበቅ ስለማይቻል መንግሥት ቢሮክራሲውን ካለበት አስፈሪ ድባብ ውስጥ የማውጣት ግዴታ አለበት፡፡ ሕዝብን ለአምስት ዓመት አገለግላለሁ ብሎ ቃል የገባ አስፈጻሚ ሥራውን መሥራት ካቃተው መወገድ አለበት፡፡ ከዘመኑ ጋር የማይመጥን ኋላቀር አመራርን ለመቀበል ማንም ትዕግሥት የለውም፡፡ በፍጥነት ወደ ሥራ ይገባ፡፡
በፍትሕ እጦትና መስተጓጎል እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ የማስቆም ኃላፊነት የአመራሩ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ካለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት እንዲሠራ እየተደረገ፣ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ ሕዝቡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡለትን መሠረታዊ መብቶች በጉልበተኞች እንዳይነጠቅና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከተፈለገ አመራሩ መስዋዕትነት መክፈል አለበት፡፡ ሕዝብ ፍትሕን በገንዘብ እንዲገዛ የማስገደድ ሕገወጥ ተግባር መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲሱ ካቢኔ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር ሕዝብን ለመበደልና መብቱን ለመጣስ ስለሚመች ተቀባይነት የለውም፡፡ ፍትሕ ለማንገስ በአስቸኳይ ወደ ሥራ ይገባ፡፡
አገሪቱንም ሆነ ሥርዓቱን መሳቂያና መዘባበቻ እያደረገ ያለው ሙስና በቁርጠኛ አመራር ካልተወገደ አደጋ ነው፡፡ በኔትወርክ በተሳሰሩ ኃይሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር በተከፈቱ የባንክ ሥውር ሒሳቦችና በተለያዩ ገጽታዎች የሚፈጸመው ሙስና፣ ሕዝብ እያማረረ ነው፡፡ አገር የሚያለሙ ኢንቨስተሮችን ጭንቅላት እያዞረ ነው፡፡ ከአነስተኛ የአገልግሎት መስጫ መንግሥታዊ ተቋም እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ድረስ የተዛመተው ሙስና ጠንካራና ቆፍጣና አመራር ይፈልጋል፡፡ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መጥፋት ምክንያት ሙስና እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሏል፡፡ ይህንን እሳት ማጥፋት ካልተቻለ አገሪቱም አገር አትሆን፣ ሥርዓቱም እንደ ሥርዓት አይቀጥልም፡፡ ሙሰኞችን ልክ ማግባት ካልተቻለ አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ የአዲሱ ካቢኔ አባላት ይጠንክሩ፡፡ በተባበረ መንፈስ ወደ ሥራ ይግቡ፡፡ የሙስና አበረታቾችን ያስወግዱ፡፡
አገሪቱ በመሠረተ ልማቶች፣ በኃይል ማመንጫዎች፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤቶችና በመሳሰሉት ከፍተኛ ሀብት እያፈሰሰች ናት፡፡ ይህ ሀብት የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካና ሕዝቡም በእኩልነት ተጠቃሚ እንዲሆን ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ ቁጥጥሩን መሠረት በማድረግ ችግሮች ሲከሰቱ በአጥፊዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ፣ ጥሩ የሚሠሩትን ደግሞ ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ በደመነፍስ የሚከናወኑ ሥራዎች ሳይሆኑ ውጤታማ የሚያደርጉ፣ በመጠን የሚለኩ፣ በሕዝብ የሚታዩና የሚገመገሙ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለባቸው፣ ወዘተ አሠራሮች መስፈን አለባቸው፡፡ እስካሁን የነበሩ ከአቅም በታች የሆኑ አሠራሮች በፍፁም ሊታዩ አይገባም፡፡ ይህም ወደ ሥራ በፍጥነት ለመግባት ያግዛል፡፡
አገሪቱ በቀንድ ሀብት በአፍሪካ አንደኛ መሆኗ ለዘመናት ሲነገር የነበረና አሁንም የቀጠለ ነው፡፡ ለሕዝቡ ግን የእንስሳት ሀብት ውጤቶች ብርቅ ናቸው፡፡ የአገሪቱ ኤክስፖርት ቄራዎች ደረጃ የዓለም አቀፉን ደረጃ አልመጥን እያሉ የሥጋ ሀብት ኤክስፖርት ማድረግ አልተቻለም፡፡ ከዚህ ቀደም ሥጋ የሚወስዱ አገሮች እያቆሙ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የቁም እንስሳት በኮንትሮባንድ በገፍ ወደ ጎረቤት አገሮች ይነዳሉ፡፡ የግብርና ውጤቶች ኤክስፖርት ገቢ በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ የሚታቀደውና የሚገኘው ለየቅል ነው፡፡ ለአገሪቱ ለዘመናት የኢኮኖሚ ዋልታ የነበረው ቡና ገቢ አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡ እያንሰራራ ነው ከሚባልለት ማኑፋክቸሪንግም የሚገኘው ገቢ የሚያወላዳ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መመጣጠን ባለመቻላቸው አገሪቱ እየተጎዳች ናት፡፡ ለነዳጅ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ እየናረ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በማሽቆልቆሉ ብዙዎች መሥራት ተቸግረዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ችግር ታቅፋ ያለች አገር ጠንካራ አመራር ካላገኘች፣ ከዓለም የኢኮኖሚ አዝማሚያ አንፃር ሲታይ ብርቱ ፈተና አለ፡፡ በከፍተኛ ብድር የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በቶሎ ተጠናቀው ገቢ ማመንጨት ካልጀመሩ፣ አገሪቱ ከማትወጣበት የዕዳ አረንቋ ውስጥ ትዘፈቃለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች በፍጥነት ወደ ሥራ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
ከገጽታ ግንባታ አንፃር ብዙ ነገሮች ሲባሉ ይደመጣል፡፡ የአገር ገጽታ ግንባታ የሚጀምረው መንግሥት ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ በሩን ዘግቶ መረጃ የማይሰጥና አገሪቱን ማስተዋወቅ የማይችል የሕዝብ ግንኙነት አያስፈልግም፡፡ መረጃ ለሁሉም ዜጋና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወቅታዊ ሆኖ ያለምንም አድልኦ መዳረስ አለበት፡፡ የአገሪቱ የቱሪዝም መስህቦች፣ ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ ዘርፎች፣ የመንግሥት የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራሮች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጦች፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚፈቱበት አሠራርና መሰል ተግባራት በግልጽ ሊታወቁ ይገባል፡፡ ለዚህም ጠንካራና ሁሌም ለመልስ ዝግጁ የሆነ የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ያስፈልጋል፡፡ መረጃ መንፈግ ኋላ ቀርነት ነው፡፡ በአስቸኳይ ወደ ሥራ ይገባ፡፡
በአጠቃላይ አዲሶቹ ተሿሚዎች የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው፣ ለሕግ የበላይነት ራሳቸውን ያስገዙ፣ ከሙስና የፀዱ፣ ለህሊናቸው ታማኝ የሆኑ፣ ከፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት የራቁ፣ የሰዎችን መብት የሚያከብሩ፣ ወዘተ መሆን አለባቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሰብዕና ላይ ደግሞ ብቃት ሲጨመርበት በእርግጥም አገሪቱን ለስኬት ያበቃሉ፡፡ ነገር ግን እንደተለመደው የብሔር ስብጥር ኮታን ለማሟላት ተሹመው ከሆነ ግን አደጋ አለው፡፡ ይህ ዘመን ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን ነው የሚፈልገው፡፡ ከዚህ ፈጣንና ተለዋዋጭ ዘመን ጋር እኩል መራመድ ያልቻለ አገሪቱን እንኳን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ሊያራምድ ገደል ነው የሚከታት፡፡ ለዚህም ነው ይሠራሉ፣ ብቃት አላቸው ተብለው የተሾሙት ተሿሚዎች ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት የሚጠብቃቸው፡፡ መንግሥት የተሿሚዎቹን አፈጻጸም እግር በእግር እየተከታተለ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ያስፍን፡፡ የሥልጣን ትልቁ አካል የሆነው ሕግ አውጪው ፓርላማ ተጠያቂነትን በማስፈን መንግሥትን ይቆጣጠር፡፡ ተሿሚዎችም በዚህ መንፈስ ወደ ሥራ ይግቡ፡፡ ሹመቱ ይሠራበት!