Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥትና በነዳጅ አቅራቢዎች መካከል አዲስ አለመግባባት ተፈጠረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አራቱ ትልልቅ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ኖክ፣ የተባበሩት፣ ቶታልና ኦይል ሊቢያ የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ያቀረበላቸውን አዲስ ውል አንቀበልም ማለታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡ በመንግሥታዊ ነዳጅ ድርጅትና በግል ነዳጅ አቅራቢዎች መካከል አዲስ አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 18 ለሚጠጉ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች አዲስ ውል ያቀረበ ሲሆን፣ የውሉ ዋነኛ ነጥብ በብድር የወሰዱትን ነዳጅ ሸጠው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብድሩን የማይከፍሉ ከሆነ 20 በመቶ ቅጣት መጣሉ ነው፡፡

ይህ አዲስ ውል የተላከላቸው የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ውሉን አምነውበት ፈርመው ባይልኩ እንኳ፣ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከውጭ የሚያመጣቸውን የተለያዩ የነዳጅ ዓይነቶች፣ አገር ውስጥ ለሚገኙ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች በብድር ያስረክባል፡፡

የግል የነዳጅ ድርጅቶች ለነዳጅ ማደያዎች፣ ለመንግሥታዊና የግል ኩባንያዎች፣ ለፕሮጀክቶችና ለመሳሰሉት ያቀርባሉ፡፡ ከነዳጅ ማደያዎች የሚያስፈልገው ገንዘብ ብዙም ሳያስጠብቅ የሚሰበስብ ቢሆንም፣ ለፕሮጀክቶችና ለተቋማት የሚቀርበው ነዳጅ ግን በብድር መሆኑን ኩባንያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ለተቋማትና ለፕሮጀክቶች የሚቀርበው ነዳጅ ተቋማቱ ጨረታ አውጥተው አወዳድረው የሚገዙ ስለሆነ፣ በዚህ ሒደት የሁለት ወራት ብድር ስለሚጠይቁ ውሉን ለመፈረም መቸገራቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ኩባንያዎቹ የሰበሰቡትን ገንዘብ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ካላስገቡ፣ ቀደም ሲል በነበረው ውል መሠረት 9.5 ሲደመር አንድ በመቶ ይቀጣሉ፡፡ ይህም ከባንኮች የወለድ ምጣኔ ጋር ተቀራራቢ ስለነበር በስምምነት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በአዲሱ ውል ላይ የሠፈረው ደግሞ ኩባንያዎቹ ብድራቸውን በ30 ቀናት ውስጥ ካልከፈሉ 20 በመቶ ቅጣት እንደሚጣል፣ የውል ማቋረጫ ጊዜም አሥር ቀናት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በተለይ አራቱ ግዙፍ የግል ነዳጅ አቅራቢዎች ይህ ቅጣት ተብሎ የተቀመጠው 20 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ ዝቅ እንዲል፣ እንዲሁም ቅጣት ሳይሆን ወለድ እንዲባልላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀው ይህ እንደማይሆን ተገልጾላቸዋል፡፡

የነዳጅ ኢንዱስትሪ ተዋንያን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት ነዳጁን የሚያመጣው በብድር ነው፡፡ እነሱም ለፕሮጀክቶቹ የሚያቀርቡት በብድር ነው፡፡ ብድሩ በወቅቱ እየተሰበሰበ ባለመሆኑ አዲሱን ውል ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ቅጣት›› ከተባለ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በወጪ ስለማያወራርድ እነዚህ ጉዳዮች ከግንዛቤ እንዲገቡላቸው ይጠይቃሉ፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ በወቅቱ እየተሰበሰበ ስላልሆነ ኩባንያዎቹ ገንዘቡን በወቅቱ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የፋይናንስ ተቋም ባለመሆኑ ወለድ አያስከፍልም፡፡ ከተዋናዮች አንዱ ግዴታውን ካልተወጣ መቅጣት እንደሚችል በሕግ ተፈቅዶለታል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ መንግሥት ከዚህ አሠራር ወደኋላ እንደማይመለስ አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች በተደጋጋሚ የታሪፍ ጭማሪ ጠይቀው ተግባራዊ ባለመደረጉ፣ እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በፋይናንስ ችግር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ ይህ አሠራር ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከጨዋታ ውጪ እንደሚሆኑ እየተናገሩ ነው፡፡

አራቱ የነዳጅ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ካሉ 800 የሚጠጉ የነዳጅ ማደያዎች ከ500 በላይ የሚሆነውን ይይዛሉ፡፡ ኩባንያዎቹ ማኅበር አቋቁመው የኖክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ይመሩታል፡፡ አቶ ታደሰ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች