Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅበቀስተ ደመና የተከበበችው ፀሐይ

በቀስተ ደመና የተከበበችው ፀሐይ

ቀን:

መስከረም 26 የዓመቱ 26ኛ ቀን ብቻ አይደለችም፤ የሳምንቱ 4ኛ፣ 3ኛ፣ 2ኛ፣ 1ኛ፣ 6ኛ ቀን ብቻም አይደለችም፡፡ የአዲስ ወቅት መጀመርያ ጭምር እንጂ፤ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ክረምትን ሸኝተን በማግስቱ መስከረም 26 ቀን የተቀበልነው መፀው -የአበባና የነፋስ ወቅት (በውጩ ቋንቋ ስፕሪንግ) እስከ ታኅሣሥ 25 ድረስ ያዘልቀናል፡፡ የወቅቱን ሽግግር ፀሐይና ቀስተ ደመና በሰማያት ላይ ሆነው  በዕለቱ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ በፈጠሩት ኅብር ርክክቡን አስፈጽመዋል፡፡ ደስ ሲል፡፡ ቀስተ ደመና እምብዛም በማይዘወተር መልኩ ፀሐይን ከብባ በዕለቱ ከረፋድ አምስት ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ደምቃ ትታይ ነበር፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት የኮፕት ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ ለጉብኝት አዲስ አበባ ጎራ ባሉበት የካቲት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ተመሳሳይ ክስተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ‹‹ፀሐየ ጽድቅ›› (የዕውነት ፀሐይ) እንዲል፡፡ (ሔኖክ መደብር)

 * * *

ማንባት ነው ያሰኘኝ

ማንባት ነው ያሰኘኝ
ማልቀስ ነው ያማረኝ

ከቁጭቴ ጋራ፤ ወትሮ ከመታገል
የንባ ማድጋዬን፤ ሰብሮ መገላገል
ማልቀስ ነው ያማረኝ፡፡

ያደራ ሳንዱቄ፤ ሲሰበር ክዳኑ
የባልንጀርነት፤ ሲጣስ ቃልኪዳኑ
መጋኛ ሲመታው
ዝምድና ሲከፋ
ፍቅር መሬት ከድታው
ባፍጢሙ ሲደፋ
የዳመነ ፊቴን፤ መዳፌ ውስጥ ልቅበር
የንባ ጋኔን ልስበር፡፡

እኔ
እንደበሬ ያረስሁ
እህል የጎመጀሁ፤ ዝማምን የጎረስሁ
አዝመራ ያደረስሁ
ፍሬውን ያልቀመስሁ፤
እኔ
መከራን በበርሚል
መጽናናትን በእፍኝ
ከዘመን ያተረፍሁ
እንቧይና ሙጃ፤ የወረሰው ሳሎን
ሳልፈልግ የታቀፍሁ

ቀስተደመናየ፤ ምድጃ ሥር ወድቆ
እፍኝ አመድ ዝቆ፤
እፍኝ ትቢያ ቅሞ
ጥላሸቱን ጠግቦ
ትቢያ ተሸክሞ
ኖህ ከነ ታሪኩ
ከነ ታይታኒኩ
እባህር ውስጥ ሰጥሞ
ለማየት የበቃሁ
ፊቴን እየፈጀሁ፤ ደረት እየደቃሁ
ማልቀስ ነው ያማረኝ፡፡

(በዕውቀቱ ሥዩም)

* * *

በደቂቃ እስከ 20 ጊዜ የምታስነጥስ ታዳጊ

12 ዓመቷ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት የጀመራት ማስነጠስ ሊቆምላት አልቻለም፡፡ ሁኔታውም ቤተሰቦቿንና የሕክምና ባለሙያዎችን ግራ አጋብቷል፡፡

ዩፒአይ እንደዘገበው፣ ታዳጊዋ ካትሊን ቶርንሊ ካለፈው ወር ጀምሮ በየደቂቃው 20 ጊዜ ታስነጥሳለች፡፡ በቀን ደግሞ 12 ሺሕ ጊዜ፡፡ ይህም የሆድ ህመም፣ የሰውነት መዛልና አቅም ማጣት አስከትሎባታል፡፡

ቤተሰቦቿ በቴክሳስ ለሚገኙ ስድስት የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ቢያሳዩዋትም የማስነጠሱ ምክንያት አለርጂና ቫይረስ መሆኑን ከመለየት ውጭ ማስነጠሱን ማስቆም ተስኗቸዋል፡፡ ‹‹አንዳንዴ ሰውነቴን ጥዬ ተኝቼ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም በህልም ውስጥ ሆኜ እንኳን ያስነጥሰኛል፤›› ስትል ቶርሊን ገልጻለች፡፡

* * *

አዲሱ የቻይና የመስተዋት ድልድይ ተሰንጥቆ ቱሪስቶችን አስደነገጠ

በቻይና ሰሞኑን ለመንገደኞችና ቱሪስቶች አገልግሎት መስጠት የጀመረውና በቻይና ደቡባዊ ክፍል የሚገኘውን ሸዋንዚ ብሔራዊ ፓርክ አቋርጦ የሚያልፈው የመስተዋት ድልድይ ተሰንጥቆ በሥፍራው የነበሩ ቱሪስቶችን አስደነገጠ፡፡

ዩፒአይ እንደዘገበው፣ ቱሪስቶች በመስተዋት ድልድዩ ላይ እየተረማመዱ፣ አንዱ ቱሪስት በእጁ የያዘው የብረት ኩባያ ይወድቅበታል፡፡ የወደቀበት ሥፍራ ላይም የመስተዋቱ የላይኛው ክፍል ይሰነጠቃል፡፡ ይህንን ያዩ ቱሪስቶች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ተሯሩጠው ድልድዩን ያቋርጣሉ፡፡ ሆኖም የድልድዩ የተወሰነ ክፍል ከመሰንጠቁ ውጭ የከፋ ጉዳት አልደረሰም፡፡ የቻይና ባለሥልጣናትም የድልድዩ የላይኛው የመስተዋት ክፍል ቢሰነጠቅም ከሥር ያሉት ሁለት የመስተዋት ርብራቦች የሚሰነጠቁ አይደሉም፡፡ ክብደት ያለው ነገር ቢሆንም ተሸክመው የመያዝ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡ የተሰነጠቀውን የመስተዋት ክፍል ለመቀየርም ድልድዩ ለጥቂት ሰዓታት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡

* * *

ፑቲን 63ኛ ዓመታቸውን በፈረስ የገና ጨዋታ አሳለፉ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን 63ኛ ዓመታቸውን በመስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ያከበሩት በክርምሊን ቤተመንግሥት ለልደት በተዘጋጀ በዓል አልነበረም፡፡ የሩሲያ ባለሥልጣናትም በተጋነነ የልደት ድግስ አልተንበሸበሹም፡፡ ምክንያቱም ፑቲን ልደታቸውን ያከበሩት ከክርምሊን ቤተመንግሥት የተውጣጣውን ቡድናቸውን ይዘው ከኤንኤልኤች ስታርስ ጋር የፈረስ ላይ የገና ጨዋታ በመግጠማቸው ወደ ሶቺ በማቅናታቸው ነው፡፡

ሚረር እንደዘገበው፣ ፑቲን በጨዋታው ኮከብ ሆነው ያሳለፉ ሲሆን፣ ሰባት ጐሎችንም አስቆጥረዋል፡፡ ቡድናቸው ተቀናቃኙን ቡድን 15 ለ 10 ማሸነፍም ችሏል፡፡ ፑቲን በዕለቱ ባስቆጠሩት ግብ ብዛት ዋንጫ የተሸለሙ ሲሆን፣ የሩሲያ ኮከብ የፖፕ አቀንቃኝ ቲማቲ ‹‹ማይ ቤስት ፍሬንድ›› የኔ ምርጥ ጓደኛ የሚል ሙዚቃ ለቆላቸዋል፡፡   

 * * *

አባ ሙሴ ዘርአይ የኖቤል ሰላም ሽልማት ዕጩ

ለዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ስዊዘርላንድ ነዋሪ የሆኑት ኤርትራዊው አባ ሙሴ ዘርዓይ መታጨታቸውን የአሜሪካ ድምፅ ዘግቧል፡፡

አውሮፓ ለስደተኞች ችግር እየተሟገቱ የሚገኙ ካቶሊካዊው ካህን አባ ሙሴ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በሜዲቴራኒያን ባህር ላይ እየታዩ ላሉ የስደትና የስደተኞች ችግሮች ለበርካታ ዓመታት ሲሟገቱ ቆይተዋል፡፡

አባ ሙሴ ሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ለአደጋ ከተጋለጡ ፍልሰተኞች የሚደርሷቸውን የ‹‹ድረሱልን›› ጥሪዎች ለጣልያንና ለማልታ የባሕር ኃይሎች እያቀበሉ በባሕር ላይ የነፍስ አድን ሥራዎች እንዲጀመሩ ላለፉት 12 ዓመታት ሲጥሩ የኖሩ ሰው መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ አባ ሙሴ ለኖቤል ሽልማት በመታጨታቸው የተሰማቸውን ስሜት ለአሜሪካ ድምፅ እንዲህ ብለውታል፡፡

‹‹ኮሚሽኑ ይህንን የሰላም ኖቤል ሽልማት መስጠት ካሰበ ባለፉት 20 ዓመታት የታገልኩለትንና የለፋሁበት የስደተኞች መብቶች ትኩረት አገኘ ማለት ነው፤ ያለፍትሕ፣ ያለ ነፃነት ያለ ዴሞክራሲ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች ሳይከበሩ ሰላም አይኖረንም፡፡ የትም ቦታ ደግሞ ሰላም እንዲሆን ከፈለግን መሠረቱ ፍትሕ፣ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነት ናቸው፡፡ ስለዚህ እኔን ለዚህ ሽልማት ያቀረበ ሰው በተለይም በሜዲትራኒያን ባህርና በየበረሃው በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ስደተኞች ትኩረት እንዲያገኙ ያለመ ነው፡፡››

አባ ሙሴ አያይዘውም በዓለም ላይ ለተንሰራፋው ችግር መፍትሔውን እንዲህ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የዚህ ችግር መፍትሔው የአፍሪካ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ማጓጓዝ አይደለም፤ መፍትሔው ለቀው የሚሰደዱባቸው አገሮች ውስጥ ላሉት ችግሮች መፍትሔ የመፈለግ ነው፡፡ እነዚህ ስደተኞች ለምንድን ነው የትውልድ አገራቸውን ለቀው የሚሰደዱት ችግሩ ምንድነው አፍሪካውያንን ሁሉ አውሮፓ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም ካናዳ ወስደን ማስፈር አንችልም፣ ሕዝብ በገዛ አገሩ ተከብሮ ነፃነቶቹና መብቶቹ ተከብሮ እንዲኖር ማስቻል አለብን፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የችግሩን ምንጭ ነው ማድረቅ ያለበት፡፡

ለዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ከአባ ሙሴ ጋር ከታጩት መካከል የሮማው ፓፓ አቡነ ፍራንሲስ እና የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል ይገኙበታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...