Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ምፅዓተ ኤርትራ የመጀመርያው መጨረሻ

  በአሸናፊ አ.

  የመስከረም አንዱን በአሜሪካ አሸባሪዎች ጥቃት ተከትሎ የዓለም ሕዝብ  ዓይንና ጆሮውን ወደ አገረ አሜሪካ አቅጣጫ አስተካክሎ ምን ይከተል ይሆን? በማለት በሥጋት የነገሮችን አካሄድ ይከታተላል፡፡ የዓለም ሚዲያዎችም የኃያሏን አገር እንደቆሰለ አውሬ መቆጣትን ሳይታክቱ እያስተላለፉ ነበር፡፡

  በዚሁ ሰሞን ከአሜሪካ ከስድስት ሺሕ ማይል በላይ ርቃ በምትገኘው አገረ ኤርትራ ፕሬዚዳንታዊ ቢሮ ውስጥ ከባድ ነገር እየተደገሰ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለዓመታት አድብተው ሲጠብቁት ለነበረው ሴራ ከዚህ የበለጠ አመቺ ጊዜ እንደማይመጣ አውቀውታል፡፡ ስን ዙ (Sun Tzu) የተባለው የቻይና ምሁር አንደዚህ ነበር ያለው (In The Midst of Chaos, There is an Opportunity) በደፈናው ብጥብጥ ሲፈጠር በውስጡ ዕድል አለ እንደ ማለት ነው፡፡

  ነገሩ ሲጀምር እንደዚህ ነበር፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ጦርነት በሽንፈት መጨረስ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከነባር ታጋዮችና የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጦርነቱ ላይ በነበራቸው ሚና ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር የደረሰባቸው፡፡ እነዚህ ነባር ታጋዮችና ከፍተኛ አመራሮች ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲጠሩ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲፀድቅ፣ የምርጫንና የፓርቲዎችን መቋቋም የሚደነገግገው አዋጅ እንዲወጣና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ለፕሬዚዳንቱ ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው እነዚህ 15 የሚሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊርማቸውን አስባስበው ጉዳዩን በኢንተርኔት በመበተንና ጋዜጣ ላይ በማውጣት ገሀድ አውጡት፡፡

  የለውጥ ዕርምጃ ለመውሰድ የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት እንደ ሰበብ ሲጠቀሙ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የጉዳዩ አደባባይ መውጣት በጓደኞቻቸው እንደተከዱ ነበር የቆጠሩት፡፡ ታዲያ ሰኔ እና ሰኞ ሲገጣጠሙ የመስከረም አንዱን የአሜሪካ ጥቃት ተከትሎ ማለትም መስከረም 1993 ዓ.ም. ከሰባት ቀን በኋላ ማለት ነው በአገር  መክዳት ከወነጀሉዋቸው 15 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ወስጥ 11ዱን በቁጥጥር ሥራ አዋሉዋቸው፡፡ ከ15ቱ ባለሥልጣናት ውስጥ ሦስቱ በወቅቱ ከአገር ውጭ በመሆናቸው ሲተርፉ፣ መሐመድ ብርሃን ብላታ የተባለው ነባር ታጋይ አመፁን በመጨረሻ ሰዓት በመክዳት ወደ ፕሬዚዳንቱ ቡድን በመቀላቀሉ ከእስር ሊተርፍ ችሏል፡፡ ይህ ሁሉ ትርምስ በዚያች የቀይ ባሕር ትንሽ አገር ውስጥ ሲከሰት  ታዲያ አንድም የዓለም ሚዲያ ነገሬ አላለውም ነበር፡፡ ላለፉት 11 ዓመታት ታዲያ እነዚህ ታሳሪዎች ይሙቱ፣ ይኑሩና የት ይታሰሩ የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡

  እነዚህ ባለሥልጣናት ይኼን ሁሉ ዓመታት ክስ ሳይቀርብባቸውና ራሳቸውን መካላከል ሳይችሉ የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ እጁን የሰጠው የኢሳያስ አፈወርቂ ታማኝ የእስር ቤት ጥበቃ ኃላፊ በሰጠው እማኝነት፣ ከ11ዱ እስረኞች ውስጥ ስድስቱ በዓመታት ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግሯል፡፡ እምባ ተከለና ኤራይሮ በተባለው ዘግናኝ እስር ቤት ውስጥ ሕይወታቸው ካለፈው ባለሥልጣናት በተጨማሪም አምስት ጋዜጠኞችም ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል፡፡

  ይህ መከራ በእነዚህ ቱባ ባለሥልጣናት ብቻ ሳያበቃ ቤተሰባቸውንም ጣጣ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ በተለይ በጴጥሮስ ሰለሞን ቤተሰብ ላይ የደረሰው መከራና ግፍ በቃላት  የሚገለጽ  አልነበረም፡፡ የትግሉ መሥራች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና በውኃ ውስጥ ሀብት ሚኒስተርነት ያገለገለው ይህ ግለሰብ ከኢስያስ ጋር በነበራቸው ግንኙነት በትግሉ ወቅት ‘E’ የሚለውን የኤርትራን ‘Eritrea’ የመጀመርያው እንግሊዝኛ ፊደል  በክንዳቸው ላይ በአንድ ምላጭ መነቀሳቸውን ይናገራል፡፡

  ጴጥሮስ ሰለሞን አስቴር ዮሐንስ ከተባለች ነባር ታጋይ የወለዱዋቸው አራት ልጆች ነበሯቸው፡፡ ባለቤቷ ሲታሰር ወ/ሮ አስቴር አሜሪካ ትምህርቷን እየተማረች ነበር፡፡ የተከሰተውን ነገር ስትሰማ ልጆቹዋን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ያደረገችው ጥረት በፕሬዚዳንቱ እንቢተኝነት አልተሳካም ነበር፡፡ ይልቁንም በአሜሪካ የኤርትራ አምባሳደር በነበሩት ግርማ አስመሮም በኩል የደረሳት መልስ ልጆቼን ልውሰድ ማለቱን ትተሸ አገርሽ ገብተሸ ብታሳድጊያቸው ይሻላል  ተብለሻል ነበር፡፡ ምንም እንደማይደርስባት መተማመኛ በመስጠት አግቧቧት፡፡

  ወ/ሮ አስቴር ወደ ኤርትራ ባደረገችው ጉዞ ገና አውሮፕላኑ የአስመራ ኤርፖርትን መሬት እንደነካ በደኅንነት ሰዎች ታፍና ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተወሰደች፡፡ የእናታቸውን መመለስ በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩት ልጆችና ለወ/ሮ አስቴር እናት ኤርፖርቱን ለቃችሁ ውጡ የሚለው ትዕዛዝ  ድንጋጤ ውስጥ ነበር የከተታቸው፡፡

  ከእናታቸው መታፈን በኋላ ቤተሰቡን ለማነጋገር መሞከርና አብሮ መታየት ሰው በመፍራቱ መገለል ደረሰባቸው፡፡ በአገራቸው ባይተዋር የሆኑት ልጆች ከሴት አያታቸው ጋር የውሸት መታወቂያ በማሠራትና ለደላላ በመክፈል እንደማንኛውም ኤርትራዊ  ነፍሳቸውን ሸጠው ነው ከአገር የውጡት፡፡ በዚህ የሽሽት ጉዞ ላይ ሀና የተባለችው የጴጥሮስ ሰለሞን ልጅ ተለይታ በሌላ መንገድ ስትጓዝ ተይዛ  በተለያዩ እስር ቤቶችና የጉልበት ብዝበዛ በሚካሄድባቸው የሻዕቢያ እርሻዎች መከራዋን ከባላች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ አምልጣ ኢትዮጵያ በመግባት፣ በሱዳን በኩል አሜሪካ ከገቡት ቤተሰቦችዋ ጋር ተቀላቀለች፡፡ የመጨረሻ ልጁ የነበረችውና እናቷን ከሁለት፣ አባቷን ደግሞ ከአራት ዓመቷ ጀምሮ ያላየቸው  መዓዛ  ሰለሞን  በአንድ ዝግጅት ላይ እንዲህ ነበር ያላቸው (The  Country my Parents Helped to Librate Made Me An Orphan) ቤተሰቦቼ ነፃ ያወጧት ኤርትራ ቤተሰብ አልባ አደረገችኝ፡፡

  ከወራት  በፊት ሃያ አራተኛ የነፃነት በዓልዋን (ነፃነት ካለ) ኤርትራ ስታከብር የታየው ትርዒትና ዝግጅት አጀብ ነበር የሚያስብለው፡፡ በተለይ በአስመራ ስታዲየም በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ኤርትራን ትልቅ ዘንዶ መሰል አውሬ ሊውጣት ሲያባርራት ይታያል፡፡ በሌላ ትዕይንት ደግሞ ጥቁርና ነጭ እንዲሁም የኒንጃ ልብስ የለበሱ ወራሪ መሰል ሰዎች የኤርትራን ድንበር ጥሰው ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ በኤርትራ ቅርፅ የተደረደሩ ወጣቶች ደግሞ ሲከላከሉ ይታያል፡፡ በዚህ የነፃነት በዓል ላይ ትርዒቱ በአጠቃላይ ጠላቶች ኤርትራን በምድር፣ በሰማይና በባህር ለመውረር የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ ልማት በፅናት (Development Through Resilience) በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ ግን የብዙዎቹ ተሳታፊዎች ፊት ላይ ተስፋ መቁረጥ ይነበብ ነበር፡፡                                                                        

  ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነው በነፃነት በዓሉ ላይ በተጋባዥነት ከተገኘው የደቡብ አፍሪካ የሙዚቃ ቡድን አባላት መካከል አንዷ የተናገረችው ንግግር ነው፡፡ ‹‹The Sound of a Diamond›› የተባለው ሙዚቃ ቡድን አባሏ ሲኒማ ሮማ (Cinema Roma) ለተገኘው ታዳሚ አንዴ የቢዮንሴን ሌላ ጊዜ የሻኪራን ጨምራ የብሪንዳ ፋሲን ዘፈኖች እየተውረገረገች ብታቀርብም፣ ከተመልካቹ ያገኘችው ምላሽ አልነበረም፡፡ ብዙው ተመልካች ወይ እጁን አጣምሯል ወይም እጁ አፉ ላይ ነው ያለው፡፡ በጣም የተናደደችው ይህች ዘፋኝ ታዲያ መዝፈኑዋን አቁማ ወደ ተመልካቹ እያፈጠጠች፣ ‹‹ምንድነው የሆናችሁት? ፈዛችኋል! ለቅሶ ለመድረስ የመጣችሁ መሰላችሁ እንዴ? 24 ዓመት በነፃነት መኖር ትንሽ ነው እንዴ?›› በማለት ቅሬታዋን ስትገልጽ ታዳሚው የምንት እፍረቱን ቆሞ አጨበጨበላት፡፡

        በኤርትራ እጅግ የበዛ ፍርኃት ሰፍኗል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በቅርቡ ባወጣው የምርመራ  ዘገባ ላይ ኤርትራን እንደ አገር የሚያኖራት ሕግ ሳይሆን ፍርኃት ነው ብሎ  የደመደመው፡፡ የሚገርመው ነገር ፍርኃቱ አገሪቱን ለቀው በወጡ ዜጎች ላይ ሳይቀር መታየቱ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በእስራኤል ሻዕቢያን ለመቃወም ሠልፍ የወጡ ኤርትራውያን በሙሉ ነጭ ማስክ አድርገው ነበር የወጡት፡፡ ይህ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡  ሠልፈኞቹ ማንነቴ ከታወቀ አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቼ ከሻዕቢያ የበቀል ዱላ አይተርፉም ብሎ ስለሚያስብ ነው፡፡ አንድ ማንነቱ እንዳይገለጽ የፈለገ ኤርትራዊ ስደተኛ ለአጣሪ ኮሚሽኑ እንደዚህ ነበር ያለው፣ ‘እጅግ ከመፍራቴ የተነሳ የሻዕቢያ ደኅንነቶች ምን እንደማስብ አውቀው አደጋ ይደርስብኛል ብዬ እሠጋ ነበር’ ብሏል፡፡ በኤርትራ  የስለላ መዋቅሩ እስከ ቤተሰብ ድረስ የተዘረጋ ነው፡፡ ጓደኛ ጎረቤት ብሎ ነገር የለም፡፡ ትንሽዬ ስህተት ትልቅ መስዕዋትነት ታስከፍላለች፡፡ በናይዝጊ ክፍሉ ላይ  የደረሰው መመልከት ሻዕቢያ ምን ያህል አፋኝ መሆኑን ያስረዳል፡፡ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር፣ ምክትል የአገር ውስጥ ሚኒስትር እንዲሁም በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር የነበረው ናይዝጊ ክፍሉ ከመታመሙና ከመሞቱ በፊት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ለንደን ለሕክምና ሄዳ እዚያው ሲሞት አስከሬኑ ኤርትራ መጥቶ እንዳይቀበር ፕሬዚዳንቱ በመከልከላቸው የለንደን ማዘጋጃ ቤት እንደ አንድ ተራ ሰው ቀብሮታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አንዴ ሰው ከጠሉ የሞተን ሰው ከመበቀልም ወደኋላ አይሉም፡፡

  ኤርትራዊ ዳያስፖራ

  ሻዕቢያ በትግሉ ወቅት ከምሥራቁ ይሁን ከምዕራቡ ጎራ ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አላገኘም፡፡ የምሥራቁ ጎራ ከደርግ ጋር በነበረው መተሳሰር ሻዕቢያን ምንም አልረዳውም፡፡ የምዕራቡ ዓለምም ቢሆን ሻዕቢያ ይከተል በነበረው ማኦኢስት አስተሳሰብ እጁን ለመዘርጋት አልደፈረም ነበር፡፡ ሻዕቢያ ይህን ክፍተት ይሞላ የነበረው ዘውዳዊውና ወታደራዊው ሥርዓት ይፈጽሙት የነበረውን ግፍ ሸሽተው በስደት ከሚኖሩ ዜጎች ኪስ ነበር፡፡ ዩኒሴፍ (UNICEF) በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በዚህ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ኤርትራውያን በላይ ተሰደው ነበር፡፡

  ሻዕቢያ እነዚህን ስደተኞች ወደ ራሱ መዋቅር ውስጥ በማስገባትና በተለያዩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች በማካተት በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ በተለይ ‹‹Eritreans for Notational Libration in AMERICA (EFNLA) and Eritreans for Notational Libration in Europe (EFLE)›› የተባሉት ማኅበራት ከታሪካዊ ዓረብ የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀጥለው የገንዘብ ምንጭ ነበሩ፡፡

  በዚያ የጦርነት ወቅት መላው ኤርትራዊ ስደተኛ በጣሊያን ቦሎኛ ከተማ የሚዘጋጀውን ዓመታዊ በዓል ለመካፈል ከአራቱም የዓለም ማዕዘን ይጎርፍ ነበር፡፡ በዚህ በዓል ላይ ለሻዕቢያ የገንዘብ ድጋፍ ከመደረጉም በላይ የፖሊሲ ጠመቃ ይካሄድ ነበር፡፡

  እነዚህ ቀደምት ስደተኞች በትግሉ ወቅት በነበራቸው ሚና ቀንደኛ የሻዕቢያ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን በወረረ ወቅት በየኤምባሲውና በየከተማው ሰላማዊ ሠልፍ በመውጣት ኢትዮጵያን ወራሪ ለማስኘት ትልቅ ሥራ ሲሠሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሻዕቢያ በውጭ የሚኖር ኤርትራዊ ከገቢው መክፈል አለበት የሚለውን የሁለት በመቶ ታክስ `በፈቃደኝነት በመክፈል ይታወቁ ነበር፡፡ እነዚህ አንጋፋ ስደተኛ ደጋፊዎች ሻዕቢያ በአገር ውስጥ የሚፈጽመውን በደል ለመቃወም ቀርቶ በግልጽ ለማውራትም ምንም ድፍረት አልነበራቸውም፡፡

  እነዚህ ቀደምት ስደተኞች ለሥርዓቱ ለነበራቸው ፍፁም ታማኝነት ማሳያ የሚሆነውም የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ባደረገው ስብሰባ ላይ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ማዕቀቡን ለመከላከል ተገኘተው ነበር፡፡ ሙከራቸው ከሽፎ በኤርትራ ላይ ማዕቀቡ ተጣለ፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱ ከስብሰባው አዳራሽ ወደ ውጭ ሲወጡ የተቀበሉዋቸው የፕሬዚዳንቱን ምሥል በቲሸርቶቻቸው ላይ ያተሙና የሚጨፍሩ ኤርትራዊ ዳያስፖራዎች ነበሩ፡፡ በዕለቱ ፕሬዚዳንቱ ከእነዚህ ኤርትራዊ ዳያስፖራዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ማዕቀቡ ምንም እንደማያስፈራቸውና አንዳችም ጉዳት እንደማያመጣ ሲናገሩ ጭብጨባው ታላቅ  ነበረ፡፡ በዕለቱ ስብሳባ ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ ነበሩ፡፡ አንድም ሰው እንኳን ስለምርጫ፣ ያለ ፍርድ ስለታሰሩ ባለሥልጣናት አልጠየቀም፡፡ ይባስ ብሎም አንድ ተሰብሳቢ፣ ‹‹የገጠሩንና የከተማውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል እንዲህ ሌት ተቀን እየለፋህ ለመሆኑ የመተኛ ጊዜ አለህን?›› የሚል የፌዝ ጥያቄ ነበር ፕሬዚዳንት ኢሳያስን የጠየቃቸው፡፡

  የላምፓዱሳ ትኩሳት

  በውጭ በሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል በግልጽ የሚታይ መከፋፈል የተጀመረው በጣሊያን የላምፓዱሳ ደሴት አካባቢ በሕገወጥ መንገድ በመርከብ ሲጓዙ የመስጠም አደጋ ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ፣ ከ350 በላይ ኤርትራዊ መሆናቸው ሲነገር ነው፡፡

  በዚህ አደጋ በኤርትራውያን መካከል በሹክሹክታ ሲነገር የነበረው የሥርዓቱ ተቃውሞ አደባባይ ወጣ፡፡ ወጣት ኤርትራውያን ከአዲስ አበባ እስከ ሮም፣ ከእንግሊዝ እስከ አሜሪካ፣ ከቴላቪቭ እስከ ጄኔቫ ሰላማዊ ሠልፍ ይወጡ ጀመር፡፡ በተለይ በጣሊያን በተካሄደው ተቃውሞ እንቅስቃሴ የኤርትራን ኤምባሲ እስከ መቆጣጠር ደርሰው ነበር፡፡  ‹‹ISAYAS  to ICC, Stop Slavery In ERITERIA, hay hay, ho ho, ISAYAS must go›› የሚሉ  የተቃውሞ ድምፆች  በእነዚህ ሠልፎች ላይ በብዛት ይሰሙ ነበር፡፡ ኤርትራውያን ባለሥልጣናት የውጭ አገር ጉብኝታቸው እንደ ቀድሞው በጭበጨባ በሚቀበሉዋቸው ኤርትራውያን ሳይሆን፣ እሳት ለብሰው እሳት በጎረሱ የሥርዓቱ ተቃዋሚዎች ይታጀብ ጀመር፡፡ በአሜሪካ ወጣት ኤርትራውያን የሥርዓቱን ቁልፍ ሰው  የማነ ገብረ አብን መንገድ ለመንገድ እየሰደቡ ወደ ሆቴላቸው እንዲገቡ አስገደዱዋቸው፡፡ በእስራኤል የኤርትራ አምባሳደር ከስብሰባ ሲወጡ በተቃዋሚዎች ጥቃት ሊደርስባቸው ሲል በፖሊስ እገዛ አመለጡ የሚሉ ዜናዎች መሰማት ጀመሩ፡፡

  አሁን ወጣት ኤርትራውያን አገዛዙን ለመጣል ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ሰላም ኪዳኔ አንዷ ናት፡፡ ለንደን ሆና በጀመረችው ‹‹Freedom Friday›› የሚል ዘመቻ ወደ ኤርትራ በዘፈቀደ በመደወል የምታገኘውን ሰው ‹‹አይዟችሁ፣ በርቱ፣ እኛም ከእናንተ ጋር ነን…›› በማለት አጋርነቷን ትገልጻለች፡፡ ይህ ዘመቻ አሁን አሁን አድጎ የተለያዩ ጽሑፎችንና ፖስተሮችን በድብቅ በማስገባት አገዛዙን እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ሜሮን እስጢፋኖስ ደግሞ የስዊድን ነዋሪ ስትሆን፣ ታዋቂ የሆነውና ኢሳያስን የሚቃወመው ‹‹ራዲዮ ኤሪና›› (Radio Erina) መሥራች ነች፡፡ ሜሮን ከስዊድን የምታስተላልፋቸው ሥርጭቶች አሁን ኤርትራዊ አድማጫቸው ብዙ ነው፡፡ ዳንኤል መኮንን የተባለውና በአውሮፓ የሚኖረው የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ በኤርትራ ላይ ለወጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሪፖርት እጅግ ጠቃሚ መረጃ በመስጠቱ ጥርስ ውስጥ ገብቷል፡፡

  አሁን ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚያደርገው ጥረት ቀንሶ የተቃውሞ ድምፆችን ለማፈን እየሞከረ ነው፡፡ በተለይ እንደ ፌስቡክና ትዊተር ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ተቃዋሚዎቹን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ እንዲገለሉ በማድረግ እሳቱን ሊያጠፋ እየሞከረ ነው፡፡ በግብፅና በሶሪያ የሠለጠኑትና እጅግ የተካኑት የሻዕቢያ የደኅንነት ፕሮፓጋንዲስቶች አንዱን የኢትዮጵያ ብሔር ከሌላው ለማቀያየም፣ በተለያዩ የኢንተርኔት መድረኮች ሲለቁት የነበረውን መርዝ አሁን በራሳቸው ዜጋ ላይ አጧጡፈውታል፡፡

  ኤርትራ – አፍሪካዊ ሰሜን ኮሪያ

  በ2003 በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የሚታተመውና የዓለም አገሮችን ፖለቲካና ኢኮኖሚ የሚተነትነው መጽሔት (Foreign Policy) ዘጋቢ ናትናኤል ሜየርስ (Nathaniel Mayers) ስለ ኤርትራ በጻፈው ጽሑፍ ላይ፣ ኤርትራን አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ በማለት የዳቦ ስም አውጥቶላታል፡፡

  ይህ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ አገረ ኤርትራ ይህ የዳቦ ስም እንዲያውም ሲያንሳት ነው፡፡ ኤርትራ ሕገ መንግሥት አያውቃትም፣ የፍትሕ አካሏ ተሽመድምዷል፣ ነፃ ሚዲያ የሌለባት፣ አንድም እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲ የሌለባት፣ ምርጫ ተካሂዶ የማያውቅባት፣ ዓመታዊ በጀቷ ስንት እንደሆነ የማይታወቅባት፣ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ለመሄድ ፈቃድ የሚያስፈልግበት፣ በልማት ስም ዜጎች ለባርነት የሚዳረጉበትና አንጋፋውንና ብቸኛውን የአስመራ ዩኒቨርስቲ የዘጋች፣ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የሞባይል ሲም  ካርድ ለማውጣት እንኳን ዓመታት የሚፈጀውን የግዴታ የልማት ዘመቻ መካፈል የግድ ነው፡፡  

  ኤርትራ የባድመ ጦርነትን በሽንፈት መጨረስ ተከትሎ የቁልቁለት ጉዞዋን ያፈጠነ አዋጅ አወጀች፡፡ ‹‹ዋርሳይ ይካአሎ›› በሚል ስያሜ የተጀመረው ዘመቻ ማንኛውም ከ18 እስከ 50 ዕድሜ ክልል የሚገኝ ኤርትራዊ ዜጋ አገሩን ማገልገል እንዳለበት የሚደነግግ ነው፡፡ ይህ ዘመቻ ለስድስት ወራት የሚሰጥ ወታደራዊ ትምህርትን ጨምሮ የሻዕቢያ መገልገያ የሚሆኑ ግንባታዎችንና በጦሩ ሥር የሚተዳደሩ እርሻዎችን በነፃ ማገልገል ያካትታል፡፡

  ሲጀመር ለ18 ወራት በሚል የተጀመረው ባርነት የሚመስል ዘመቻ ዓላማውን በማሳት ነው ዜጎችን ከአምስት እስከ አሥር ዓመት አፍኖ በመያዝ ወደ ማሰቃያ ዘዴነት የተለወጠው፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም የጦሩ አዛዦች የግል እርሻቸውን ወይም ቤታቸውን  በእነዚህ ዜጎች ነፃ ጉልበት ማሠራት ጀመሩ፡፡ ለልማት ብለው በየበረሃው  የወጡ  ወጣት ሴቶች የጦር ኃይሉ አዛዦች መጫወቻ ሆኑ፡፡ ይህንን የባርነት ዘመቻ የተቃወሙ ወይ ተረሽነዋል ወይም በኮንቴይነር ውስጥ ታሽጎባቸው ዓመታትን እየቆጠሩ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ400,000 እስከ 900,000 የሚሆኑ  ኤርትራውያን በዚህ የግዴታ  ባርነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

  ‹‹ባርነቱ ምንም የማለቅ አዝማምያ አላሳይ ሲል በጨለማ ጠፋሁ፤›› በማለት የተናገረው ሮቤል የተባለ ወጣት ሲሆን፣ ለማምለጥም ሁለት ዓመት እንደፈጀበት ተናግሯል፡፡ ሮቤል በዚህ ግዴታ ስድስት ዓመታት ያገለገለ ሲሆን፣ አሁን ጣሊያን ይገኛል፡፡ አሁን በኔዘርላንድ የምትኖረው ሊዲያ ስትናገር፣ ‹‹ብዙዎቹ ጓደኞቼ ባርነቱን ለማምለጥ ሲሉ ከማያውቁት ሰው ጭምር አርግዘው ልጅ በመውለድ አደጋ ውስጥ ይገባሉ፤›› ብላለች፡፡ ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ በየወሩ ከ5,000 በላይ ባርነት የሚሸሹ ዜጎቿ ድንበር በመሻገር ወደ ኤትዮጵያና ሱዳን ይወጣሉ፡፡

  ይህ ተሰልቶ የተቀመረ የሚመስል ዘመቻ ኤርትራውያንን ለከፋ መከራ አጋልጧቸዋል፡፡ በወጣትነቱ ተምሮ ሥራ ይዞ ቤተሰቡን ለመርዳትና የራሱን ቤተሰብ ለመመሥረት ህልም የነበረው ኤርትራዊ በየበረሃው እየተንከራተተ ነው፡፡ ብስጭት ውስጥ የገቡት ራሳቸውን እያጠፉ ነው፡፡ ብዙዎች ለአዕምሮ ሕመም ተዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሽመልባ ስደተኞች ጣቢያ የአዕምሮ ሕሙማን ኤርትራውያን ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ ራሳቸውን ወደ ሱስ ዓለም በመክተት ስቃያቸውን ለመርሳት የሚሞክሩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ከተሞች ኤርትራውያን በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በተለይ በመቐለ ከተማ በአሥራዎቹ መጨረሻ የሚገኙ ኤርትራውያን ልጃገረዶች አስከፊውን የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እየገፉ ይገኛሉ፡፡

  ይህን የዜጎች በየበረሃው መውደቅና ብሔራዊ ውርደትን አስመልክቶ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ሲጠየቁ መልሳቸው ሁልጊዜም አንድ ነው ‹‹They are not Eritreans›› (ኤርትራዊ አይደሉም) የሚል ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ኃላፊነት

  አሁን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኤርትራ በሰዓት እንደተሞላ ቦምብ ለመፈንዳት ተቃርባለች፡፡ ፕሬዚዳንቱም መፈንቀለ መንግሥት ቢነሳ እንኳን ጦሱ ለኔ ብቻ አይተርፍም በማለት የአስመራንና የምፅዋን ሕዝብ በቤተሰብ ደረጃ አንዳንድ ክላሽ እንዲታጠቅ በማድረግ እርስ በርሱ እንዳይተማመን አድርገውታል፡፡ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የተባለው ተቋም በሪፖርቱ 25 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ እንደታጠቀ ገልጿል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደ ብዙዎቹ አምባገነኖች አገሪቷን ይዘው ለመጥፋት እንደወሰኑ  በመጠጥ ተገፋፍተው በአንድ ወቅት የትግል አጋራቸው ለነበረው አምደ ብርሃን ገብረ ጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አምደ ብርሃን ››Eritrea at Crossroad››  በሚለው  መጸሐፍ ውስጥ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የመገለልና የመናቅ ስሜት እንደሚሰማው ገልጾ በአንድ ወቅት እንዲያውም ‹‹አጋሜ እያላችሁ ከጀርባዬ እንደምታሙኝ አውቃለሁ፡፡ አሳያችኋለሁ!  ይህችን አገር እንድትፈጠር እንዳደረGኩ ሁሉ ይዣት ነው የምጠፋው፤›› ብሎ ተናግሯል ይለናል በመጽሐፉ፡፡ ሻዕቢያን ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ ለሚያውቀውና ኤርትራን ሁለተኛ ቤቴ ናት ለሚለው ዳን ኮኔል (Dan Connel) ፕሬዚዳንቱ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎት ነበር፡፡ (When I am Challenged, I Become More Stubborn) ‹‹ሰዎች እኔ የምለውን ካልተቀበሉኝ፣ ከተከራከሩኝ የፈለጋ ቢመጣ እውነትም ቢሆን አልቀበልም፤›› እንደ ማለት ነው፡፡

  እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በባድመ ጦርነት አያያዝ ኢሳያስንም ከሥልጣን የማስወገድ አቅም ነበራት፡፡ ይህን አድርጋ ቢሆን ኖሮ ይኖራት የነበረው ስም  የወራሪነት ሆኖ የሻዕቢያን ተወረርኩ ባይነት ክስ ማረጋገጥ ይሆን ነበር፡፡ በዚያ ጦርነት ኢትዮጵያ የተወረረባትን መሬት አስመልሳ ሻዕቢያን አቅባ ማስቀመጧ ሁለት ነገሮችን አሳክቷል፡፡ የመጀመርያው የኤርትራ ሕዝብ በራሱ ጊዜ የሻዕቢያን ባህሪ እንዲረዳ በማድረግ ተወረርኩ ለሚለው ክስ ጆሮ ነፍጓል፡፡ በዚህ መሠረትም በሕዝቦች መካከል ይፈጠር የነበረውን ዘመን የማይሽረው ጥላቻ ቢያንስ ማሰወገድ ተችሏል፡፡ ሁለተኛው ጦርነቱ የሻዕቢያን የመዋጋት አቅም በሁሉም መልኩ ስለቀነሰውና ከጦርነቱ በኋላ በነበረው ጊዜ፣ እውነተኛ ባህሪው በዓለም አገሮች ታውቆ ራሱን በራሱ እንደ ካንሰር በልቶ እንዲጨርስ መደረጉ ነው፡፡

  ታዲያ ኢትዮጵያ አሁን ሻዕቢያን ከሥልጣን ለማስወገድ ዕርምጃ ብትወስድ እንደ ወራሪ ወይስ እንደ ፍትሐዊ አገር ነው የምትወሰደው? ለመሆኑ ፍትሐዊ ጦርነት ምን ማለት ነው? አንድ ጦርነት ፍትሐዊ መሆኑን ለማስረዳት የተወሰኑ መለኪያዎች አሉ፡፡ እስቲ እነዚህን የፍትሐዊ ጦርነት መለኪያዎች (Just War Principles) ከኤርትራ አንፃር እንያቸው፡፡

  የመጨረሻ አማራጭ

  አንድ ጦርነት ፍትሐዊ የሚሆነው ሁሉም የሰላም አማራጮች ተሞክረው ውጤት ሳይመጣ ሲቀር ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኤርትራን ስናይ ለሰላም የቀረቡላትን የተለያዩ የእንደራደር ጥቄዎች በተደጋጋሚ ወደ ጎን በማለትዋና ተንኳሽ ባህሪዋን መለወጥ አለመቻሏ ለፍትሐዊ ጦርነት ተገቢ ያደርጋታል፡፡

  ሕጋዊ አካል

  ጦርነት ዕውቅና ባለውና በሕጋዊ አካል ከተፈጸመ እንደ ፍትሐዊ ጦርነት ይወሰዳል፡፡ በዚህ መለኪያ መሠረት ግለሰቦችና ቡድኖች ስለታጠቁ ብቻ ጦርነት ቢያንስ  ተጠያቂ የሚሆኑበት ሕጋዊ መሠረት ስለሌለ ፍትሐዊ ጦርነት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ታዲያ በኤርትራ ላይ ጦርነት ብታስነሳ በየትኛውም ወገን የሕጋዊነት ጥያቄ አይነሳባትም፡፡

  እውነተኛ ዓላማ)

  ኢትዮጵያ በሻዕቢያ ላይ የምታካሂደው ጦርነት የራሷን አገራዊ ደኅንነት ከማስከበር አልፎ ኤርትራውያንን ከጭቆናና ከባርነት የሚያላቅቅ በመሆኑ፣ ፍትሐዊነቱና እውነተኛነቱ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

  የማሸነፍ ዕድል

  ሻዕቢያ የሚፈጸምበትን ጦርነት የማሽነፍ ቀርቶ የመመከት ችሎታው ከከዳው ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ጦርነቱን የማሸነፍ ዕድሏ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

  በእነዚህና በሌሎች መለኪያዎች ሻዕቢያን ከሥልጣን ለማውረድ የሚወሰደው ዕርምጃ ለሁለቱም አገሮችና ዜጎች ዕድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ ከተጠቀሰው ሻዕቢያን በጦር ኃይል ማስወገድ አማራጭ የበለጠ መታየት ያለበት የአገራችን ዘላቂ ሰላም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢችል የሥርዓቱ ቁንጮዎች ተወግደው ሥርዓቱ ግን ሳይፈርስ ለውጥ በሒደት የሚመጣበትን መንገድ በግድ መፈለግ አለበት፡፡ ካልሆነም የሥርዓቱ ተቃዋሚዎቸ መልፈስፈሳቸውን ትተው ተተኪ ኃይል እንዲሆኑ አስፈላጊውን ዕርዳታ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሁሉ ካልተሳካ ኤርትራ ሰሜናዊ – ሶማሊያ መሆኗ የማይቀር ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

   

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles