Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቱሪዝም ቀንና የተዘነጋው የአፄ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት

የቱሪዝም ቀንና የተዘነጋው የአፄ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት

ቀን:

ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ የዓለም የቱሪዝም ቀን ወደሚከበርበት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ለመጓዝ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሰባስበዋል፡፡

በዓሉ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች አስተናጋጅነት ተከብሯል፡፡ ዘንድሮም በበዓሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን መጐብኘትና በቱሪዝም አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ  ጥቅሞች ላይ የሚያተኩር ምክክር ላይ ለመካፈል ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከሚኒስቴሩ እንዲሁም ከየክልሉ የተውጣጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን ጓዛቸውን ሸክፈው በስፍራው ተገኝተዋል፡፡

ዘንድሮ የተከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን ዓለም አቀፍ መሪ ቃል ‹‹አንድ ቢሊዮን ቱሪስቶች አንድ ቢሊዮን ዕድሎች›› የሚል ሲሆን፣ ብሔራዊ መሪ ቃሉ ግን ‹‹ሚሊዮን ቱሪስቶች ሚሊዮን ዕድሎች›› የሚል ነበር፡፡ ይህንን መሪ ቃል ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ከበዓሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ያስረዱት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ‹‹ሚሊዮን ሳይባል ቢሊዮን አይባልም ስለዚህ አቅማችንን አደራጅተን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማገባደጃ ላይ አንድ ሚሊዮን 40 ሺሕ ቱሪስቶችን ለመሳብ ጠንክረን የምንሠራ መሆኑን ለማመልከት ነው›› በማለት ገልጸው ነበር፡፡ እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ዕቅዶች የተለጠጡ እንዲሆኑ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ መሪ ቃልን የተመጠነ ለማድረግ መጠበብ አላስፈላጊ ጭንቀት እንደሆነ የገለጹ አሉ፡፡

በዚህ መነሻነት ጉዞውን ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ያደገው ልዑካን ቡድን አዳሩን ሐረር ላይ አድርጐ በነጋታውም በሐረር ከተማ የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ መስህቦችን በመጐብኘት ጉዞውን በመቀጠል አዳሩን ጅግጅጋ ላይ አደረገ፡፡

ወደ ጅግጅጋ የተደረገውን የልዑካን ቡድኑን ከሐረር ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው የባቢሌ አካባቢ ድረስ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በመገኘት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡ የልዑኩ ቡድንም በተደረገለት አቀባበል መደሰቱን በመግለጽ ጉዞ ወደ ጅግጅጋ ሆነ፡፡

እሑድ አመሻሽ ላይ ጅግጅጋ የደረሰው የልዑካን ቡድኑ እንዲሁ በከተማዋ መግቢያ ላይ በከተማው ነዋሪዎች አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹም በደስታ የእንኳን ደህና መጣችሁ መዝሙርና ባህላዊ ዘፈኖችንና ጭፈራዎችን በማቅረብ የአቀባበል ሥርዓቱን ድምቀት ሰጥተውታል፡፡ የበዓሉ አከባበር፣ የዝግጅቱ አጠቃላይ ሁኔታ መጨረሻው እንደአቀባበሉ የሚጨበጨብለት በእልልታ የሚዘጋም ዓይነት አልነበረም፡፡

ከሰኞ መሰከረም 17 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ዓርብ መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚካሄዱትን ፕሮግራሞች በዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የክልሉ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እድሪስ ኢስማኤል፣ የክልሉ ርዕሰ መሰተዳድር አቶ አብዲ መሐመድና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፕሮግራሙ ሰኞ መስከረም 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በይፋ ተጀመረ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁለት በቱሪዝም ልማት፣ ጥቅምና አጠቃቀም እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሚገኙ እምቅ የቱሪስት መዳረሻዎችንና መስህቦችን የሚያስቃኙ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ አዘጋጆች አማካይነት በተዘጋጀው ዝርዝር የፕሮግራሙ መርሀ ግብር መሠረት በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጐብኘት የሚጀምረው ወነበርካ ግድብ፣ መለስ ፓርክ፣ የትምህርት ተቋማትንና የአውሮፕላን ማረፊያውን በመጐብኘት ነው የሚል ሲሆን፣ በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት ደግሞ ድርብ፣ ደንበል፣ ባቢሌ የዳብታ ድንጋዮች፣ እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሚጐበኙና የቁንጅና ውድድር እንደሚካሄድ የተገለፀ ቢሆንም መጐብኘት የተቻለው ግን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያስገነቡትን ቤተ መንግሥትና የመሠረተ ልማቶችን ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና የሚኒስቴሩ አስተባባሪዎች ያለመናበብ ችግር መሆኑ በግልጽ ይስተዋል ነበር፡፡

በየአውቶቡሱ እንዲያስተባብሩ ተመድበው የነበሩት የሚኒስቴሩ አስተባባሪዎች ከጋዜጠኞች ይቀርብላቸው የነበሩ ጥያቄዎችና ስለሚከናወኑ ቀጣይ ፕሮግራሞች ማብራሪያና ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩም ተስተውሏል፡፡

በኤረር ከተማ የሚገኘው የአፄ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ተነሥተው በስተሰሜን ምዕራብ 214 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወይም ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ተነሥተው በስተ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በሁርሶ በኩል 62 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ የምትገኘው ከተማ ውስጥ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በ1940 ዓ.ም. ያስገነቡት ቤተ መንግሥት ይገኛል፡፡

ቤተ መንግሥቱ በተለይ አፄ ኃይለሥላሴ ከነሐሴ 1 – 16 የሚውለውን የፍልሰታ ፆምን እየፆሙ ያሳለፉበት እንደነበር የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ዙበይዳ ኢብራሒምና በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገመቱት ወ/ሮ ዘሐራ ፈረጃ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ቤተ መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ክፍሎችም በአካባቢው ካለ የፍል ውሀ መስመር ተዘርግቶላቸው ለጤና ጠቃሚ እና ተስማሚ ነው የሚባለውን ፍል ውሀ መጠቀም እንዲቻል ሙሉ ሰውነትን መያዝ የሚችሉ ገንዳዎች ያሏቸው ክፍሎች፣ ከአንገት በላይ በእንፋሎት የሚታጠኑበትንና የእግር መታጠቢያ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡

ቤተ መንግሥቱ አሁን ያለበት ሁኔታ አሳዛኝም አሳፋሪም ሊባል ይችላል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የተነሳ ተስፋቸው ዳግም ማንሠራራቱን ገልጸዋል፡፡

የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ያስወገደው የደርግ መንግሥት ቤተ መንግሥቱን ለጦር ሠፈርነት ይገለገልበት እንደነበር ያስታወሱት በስፍራው ከ40 ዓመታት በላይ የኖሩት ወ/ሮ ዘሐራ ሲሆኑ፣ ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ ግን ቤተ መንግሥቱን ዞር ብሎ ያየው አካል እንደሌለ በቁጭት ይገልጻሉ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ወ/ሮ ዙብይዳ ኢብራሂምም የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ግለሰቦች የቤተ መንግሥቱን የተለያዩ ቁሳቁሶች ገነጣጥለው መውሰዳቸውን አስታውሰው ‹‹አሁን ይህ ጉብኝት ለቤተ መንግሥቱ የተሻለ ቀን የሚያወጣለት ይመስለኛል›› በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ አባታቸው ሀጂ ኢብራሂም ሑሴን የቤተ መንግሥቱ ጠባቂ እንደነበሩ የገለጹት ወ/ሮ ዙበይዳ በስፍራው ተገኝተው ስለ ቤተ መንግሥቱ ማብራሪያ ለመስጠት አባታቸው የነገሯቸውን ታሪኮች ለታዳሚው ከማስረዳት ባለፈ ‹‹የኢትዮጵያ ሰው፣ እኛ እናንተን እንወዳለን ስለዚህ ይህን ቤት አድሱት መስታወት አድርጉበትና ለመዝናኛ እንዲሆን አድርጉት እኛ እንዳንሠራው አቅም የለንም አገር ውስጥም ያላችሁ ውጭም ያላችሁ ወገኖች ልክ እንደ ዓባይ ኑና ሥሩልን፡፡ የኃይለሥላሴ ታሪክ እንዳይሞት አደራ እላለሁ›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቤተ መንግሥቱ አብዛኛው ክፍል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ በሮቹ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተነቃቅለዋል፡፡ የዋናው ቤት የጣሪያ ክዳንም እንዲሁ በንፋስ ይሁን በሰው ተገንጥሏል፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ባለቤታቸው እቴጌ መነንና ልጆቻቸው ይጠቀሙት የነበረው የሙቅ ውሀ ገንዳው እንዲሁ አቧራና የሸረሪት ድር ወሮታል፡፡ ዋናው ቤት መግቢያ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የነበሩ የተለያዩ አገሮችን የጊዜ አቆጣጠር የሚገልጹ ሰዓቶችም እንዲሁ ወላልቀው እዚህ ነበርን የሚል አሻራቸው ብቻ ይስተዋል፡፡  

በተመሳሳይ በአካባቢው ከ40 ዓመት በላይ የኖሩትና ንጉሡን በአካል አግኝተው የሁለት ብር ሽልማት ተቀብለው እንደነበር የሚያስታውሱት ወ/ሮ ዘሐራ በበኩላቸው ‹‹የንጉሡ መውረድን ተከትሎ ጊዜውም እየወደቀ መጣ እኛም ቅስማችን ተሰበረ መብታችንም ቀረ›› በማለት ከቤተ መንግሥቱ መፈራረስና መዘንጋት ጋር ተያይዞ በስፍራው ይኖሩ የነበሩ ሰዎችም ጥቅማቸው መቅረቱን በፀፀት ይገልጻሉ፡፡

ከንጉሡ ጋር በተገናኘ አስገራሚ አጋጣሚ እንዳላቸው የሚገልጹት ወ/ሮ ዘሐራ ‹‹ከንጉሡ በአንድ ወቅት የሁለት ብር ስጦታ ተበርክቶልኝ ነበር፡፡ እርሳቸው የሰጡኝን ሁለት ብር ምንም ነገር ሳላደርጋት ለ6 ወር ያህል አስቀምጫት ነበር›› በማለት በትዝታ ወደኋላ ተጉዘው ቅዝቅዝ ባለ አነጋገር ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡

የወ/ሮ ዘሐራም መልዕክት ቤተ መንግሥቱ ታድሶ እንደቀደመው ጊዜ መሪዎች እንኳን ባይሆን ጐብኚዎች እየሔዱ በቀደመ ጊዜ ይገኝ የነበረው ዓይነት ጥቅማቸውን የማግኘት ተስፋ የሰነቀ ነው፡፡

ቤተ መንግሥቱ የተገነባባት ከተማ ኤረር የዛሬን አያድርገውና ከዓመታት በፊት ከጂቡቲ በድሬዳዋ አዲስ አበባ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በነበረበት ወቅት ዋና የንግድ መስመርና መናገሻ እንደነበረች በከተማዋ እምብርት ተንጋሎ የሚታየው የባቡር ሀዲድ አፅምና ታሪካዊ ድርሳናት ምስክሮች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን አዲሱ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር አሁንም ከተማዋን አቋርጦ ማለፉ ለከተማዋ ዳግም ማንሰራራትና ለቤተ መንግሥቱም ጐብኚዎችን ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም በአካባቢው ምንም ዓይነት አገለግሎት መስጫ ተቋማት አለመኖራቸው እንደ ችግር የሚጠቀስ ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ቢቻልና በአካባቢው የመሠረተ ልማት ቢሟላ ቦታው ታላቅ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ማገልገል ከመቻሉም ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድም ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ቀጣይ አቅጣጫቸው መሆን ይኖርበታል፡፡

የበዓሉ አከባበር ሒደት   

የቱሪዝም በዓል በየክልሉ መከበሩ ፋይዳው በየክልሎቹ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅና ከዘርፉ ሊገኙ የሚችሉ ጠቀሜታዎችን ለሕዝቡ ማሳወቅና መነቃቃት መፍጠርን ያለመ እንደሆነ ተገልፆ ነበር፡፡

ነገር ግን በዘንድሮው የበዓሉ አከባበር ላይ ያለመቀናጀት ችግርን ማስተዋል ተችሏል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በዓሉ በሚከበርበት ክልል የሚገኙ አጠቃላይ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጐብኘት የጉዞው ዋነኛ ዓላማ የነበረ ሲሆን፣ መጐብኘት የተቻለው ከቱሪስት መዳረሻነት ጋር ቀጥታ ተያያዥነት የሌላቸው የተወሰኑ መሠረተ ልማቶችንና አንድ የቱሪስት መዳረሻን ብቻ ነው፡፡ በፕሮግራሙ ለመጐብኘት ዕቅድ ተይዞላቸው የነበሩ ስፍራዎች ያለምንም ማብራሪያ ታጥፈዋል፡፡ በዚህ የተነሳ የልዑካን ቡድኑም ከታቀደለት ጊዜ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ወደየመጣበት ስፍራ ተመልሷል፡፡

የመገናኛ ብዙሐንንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ቡድን ወደ ስፍራው ሲያቀና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያሉትን መዳረሻዎች በሙሉ በማስጐብኘት ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ጅግጅጋ ግን ከዚህ አጋጣሚ መጠቀም የቻለች አይመስልም፡፡ በዕቅዱ የተያዙትን መዳረሻዎች እንኳን መጐብኘት አልተቻለምና፡፡

በሁለተኛነት የሚኒስቴሩ በየክልሎች የሚሰጠውን ድጋፍ በማጠናከር ሁሉም በዘርፉ የነቃ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚሠራ የተገለፀ ቢሆንም የአቅጣጫዎቹ ግልጽ አለመሆንን በስፍራው ማስተዋል ተችሏል፡፡ የክልሉ የቱሪዝም ቢሮና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንደ አንድ ተቋም በአንድ ግለሰብ የሚመሩ መሆንም ለነገሩ የተሰጠውን ትኩረት ይናገራል፡፡

ሌላው ለ28ኛ ጊዜ በአገሪቱ በተከበረው በዘንድሮ የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓል አከባበር ላይ የተስተዋለው መዘበራረቅ ደግሞ ሚኒስቴሩ ‹‹አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶች አንድ ሚሊዮን ዕድሎች›› የሚለው መሪ ቃል በብሔራዊ ደረጃ በዓሉ የሚከበርበት እንደሆነ በመግለጽ የተለያዩ የጽሑፍና የምሥል ማስታወቂያዎችን የሠራ ቢሆንም የተወሰኑ አካላት ደግሞ ‹‹አንድ ቢሊዮን ቱሪስቶች አንድ ቢሊዮን ዕድሎች›› የሚለውን መሪ ቃል ይጠቀሙ እንደነበረ ተስተውሏል፡፡

ለዚህ ዓብይ ማሳያ እንዲሆን ደግሞ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ አጥር ላይ የተሰቀሉት ሁለት ማስታወቂያዎችን መመልከት በቂ ነው፡፡ የሚኒስቴሩ መግቢያ በር ላይ አንድ ሚሊዮን የሚለው ብሔራዊ መሪ ቃልን የሚገልጸው ማስታወቂያ የተሰቀለ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አማካይነት ተዘጋጅቶ እዚያው ሚኒስቴሩ አጥር ላይ የተንጠለጠለው ማስታወቂያ ደግሞ አንድ ቢሊዮን የሚለውን ዓለም አቀፍ መሪ ቃል ይዟል፡፡ ይህ ካለመናበብና ምናልባትም ከቸልተኝነት የመጣ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

በሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ እየሠራች እንደሆነ በተደጋጋሚ ከመገለጹ አንፃር እንዲህ ያሉ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን መሠረታዊ አሠራሮችን በማስተካከል የዕቅዱን ተፈጻሚነት መጀመር መልካም ይሆናል፡፡

የሚቀጥለውን ዓመት የቱሪዝም በዓል በብሔራዊ ደረጃ ለማስተናገድ አዲስ አበባ የተመረጠች ሲሆን፣ በክልል ሲደረግ የነበረው የበዓል አከባበርም የክልል ጉዞውን ጨርሶ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡ ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት አዲስ አበባን ለቆ ወደ ጅግጅጋ የተጓዘው የጋዜጠኞችና የልዑካን ቡድንም እንዲሁ በሳምንቱ ወደተነሳበት ተመልሷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...