Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቀይ ቀበሮን ያሰጋው የእብድ ውሻ በሽታ

ቀይ ቀበሮን ያሰጋው የእብድ ውሻ በሽታ

ቀን:

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በእብድ ውሻ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቁ አገሮች አንዱዋ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ከ100 ሺሕ ሰዎች መካከል 1.6 ያህሉ በበሽታው ይያዛሉ፡፡ በየዓመቱም በበሽታው ምክንያት 1500 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ከኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮግራም የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሆኑትን እንስሳትም በብዛት የሚገድል ሲሆን፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ ላይም ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ለሚገኙ ቀይ ቀበሮዎችም የእብድ ውሻ በሽታ ዋንኛ የሕልውና ተግዳሮት ከሆነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ዶክተር ዘላለም ተፈራ የቦርን ፍሪ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተርና በኢትዮጵያ የቀይ ቀበሮ ጥበቃ አማካሪ የቦርድ አባል ናቸው፡፡ እንደ ዶክተር ዘላለም፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀይ ቀበሮዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በእብድ ውሻ በሸታ መጠቃታቸው ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት ሲባል በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በተለይም ቀይ ቀበሮዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚዘዋወሩ የቤት ውሾችን በመከተብ ላያ ያተኮረ ስትራቴጂ በ1989 ዓ.ም. እንደወጣ፣ በዚህ ስትራቴጂ መሠረት በቀበሮዎቹ መኖሪያ አካባቢ ሲዘዋወሩ የተገኙ ውሾች እንደተከተቡ ዶክተር ዘላለም ይናገራሉ፡፡

ይህም ሆኖ ግን በሽታውን መግታት አልተቻለም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሽታው መልሶ በመከሰት በቀይ ቀበሮዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ተብሎ ሲፈተሽ፣ ራቅ ብለው የሚገኙና ከደጋማዎቹ የባሌና አርሲ ተራራዎች አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች፣ በክረምት ወራት ከብቶቻቸውንና ያልተከተቡ ውሾቻቸውን ይዘው ወደ ባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ስለሚገቡ ነው፡፡

ቀይ ቀበሮዎች አኗኗራቸው በሕብረት ስለሆነም፣ አንድ ውሻ በሽታው ካለበት፣ ለበሽታው በቀላሉ ይጋለጣሉ፡፡ ችግሩን ለመፍታት የእብድ ውሻ መከላከያ ክትባቱን በምግብ ውስጥ አድርጎ ቀበሮዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በማስቀመጥና ቀበሮዎቹ እንዲመገቡት በማድረግ ከበሽታው እንዲጠበቁ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ የቀይ ቀበሮ ክትባት ስትራቴጂ ተቀርጿል፡፡

ዶክተር ዘላለም እንደገለጹት፣ የዚህ አይነቱ የክትባት አሰጣጥ በተለያዩ አውሮፓ አገሮች የተለመደ ሲሆን በኢትዮጵያም በሚገኙ 100 ቀይ ቀበሮዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል፡፡

አቶ አስቻለው ጋሻው የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ናቸው፡፡ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ካሬ ሜትር ስኩዌር ስፋት ባለውና በ1962 ዓ.ም. በተቋቋመው ፓርክ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 250 ያህል ቀይ ቀበሮዎች እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ በፓርኩ ያሉትን እንስሳት ለመታደግ ሕግና መመርያ ያለ ቢሆንም፣ ላለፉት 40 ዓመታት የነበረው አስተዳደር የማስፈጸም ብቃት እንዳልነበረው፣ ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን አሠራሮች እንደተቀየሩ ይናገራሉ፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ 100 ሕገወጥ ቤቶች እንዲፈርሱና ሰፋሪዎቹም ፓርኩን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

ሰፋሪዎቹ ውሾቻቸውን አስከትለው ወደ ፓርኩ እንዳይገቡ፣ ከገቡ ደግሞ እንዲያስከትቡ በፓርኩ ሠራተኞች ይነገራቸዋል፡፡ ይህንን ሳያደርጉ ፓርኩ ውስጥ ቢገቡ ግን ሕጉ ላይ ይህንን አስመልክቶ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስለሌለ የሚደርስባቸው ቅጣት የለም፡፡

አቶ ሙክታር አቡቴ የቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮግራም ባለሙያ፣ በዓመት ከ400 እስከ 600 የሚጠጉ ውሾችን እንደሚከትቡ፣ በ2002 ዓ.ም.  የነበሩት 466 ውሾች በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ወደ 864 ከፍ ማለቱንና ለዚህም ምክንያቱ አንድ አባወራ ብዙ ውሾችን በማሳደጉ እና ወደ ፓርኩ የሚገቡ ሰዎች ብዛትም ከፍ እያለ በመምጣቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮግራም ቀይ ቀበሮዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ይተገበራል፡፡ ከአገሪቱ ቀይ ቀበሮዎች መካከል 50 ከመቶ ያህሉ በዚሁ ፓርክ ውስጥ ስለሚገኙ ላለፉት አሥር ዓመታት በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ላይ በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቷል፡፡

ቀይ ቀበሮዎች “በሰሜንና በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮች፣ በሰሜን ወሎ አቡነ ዮሴፍ ተራራ ላይ እና በመንዝ ገሳ አካባቢ ይገኛሉ፡፡ በሰሜንና በባሌ አካባቢ ቆጠራው የተካሄደ ቢሆንም በሌሎቹ ላይ ባለመሠራቱ ኢትዮጵያ ምን ያህል ቀይ ቀበሮ እንዳላት መግለጽ እንደማይችሉ አቶ ዳውድ ሙሜ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...