ብዙዎች ጉብኝት ገንዘብ፣ ገንዘብና ጊዜ ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ከአገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነት አንፃር ይህ የበርካቶች ሐሳብ በመሆኑ እንኳንስ ከአገር ውጭ አገር ውስጥ እንኳ ይህን ቦታ ያኛውን ልጎብኝ ብሎ መነሳት እንደ ቅንጦት የሚታይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ቻይና፣ ዱባይ፣ ማሌዥያ አውሮፓም መጓዝ እየጀመሩ ነው፡፡ እነዚህ ተጓዦች ገንዘብ ያላቸው ሀብታሞች ብቻም ሳይሆኑ ደመወዝተኞችና ወጪያቸውን ደምረው፣ ቀንሰው ቆጥበውም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው የለውጡ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ጉብኝትን እንደ አንድ የሕይወታቸው ክፍል እያደረጉ ያሉም አሉ፡፡ ጎብኚ መሆን የተለመደው በበለፀጉ አገሮች ዜጎች በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር ዜጋ ጎብኚ መሆን ከገንዘብ ባሻገር ሌላ ብዙ ጥያቄም አለው፡፡
ከአገር ውጭ መጓዝና የተለያዩ ቦታዎችን የመጎብኘት ህልም ሁሌም ነበራት፡፡ በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኘው ፍሬወይኒ ገብረዋህድ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቅ ነች፡፡ የአገር ውጭ ጉብኝት የጀመረችው በ2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚያ በፊት አንድ ሁለት ቦታዎችን ለመጎብኘት አስባ የነበረ ቢሆንም አልተሳካላትም፡፡ ገንዘብም፣ መረጃም፣ በመጀመሪያ ልትሄድ ያሰበችው ዱባይ ስለነበር ዕድሜዋ ሃያ አምስት አለመሙላቱም ቪዛ ለማግኘት ችግር ሆኖባት ነበር፡፡ ታንዛኒያ ሄዳ ዛንዚባርን የመጎብኘት ህልሟም ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
‹‹ልክ ሃያ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ከአንዲት ከጓደኛዬ ጋር ወደ ዱባይ ሄድኩኝ፡፡ የት ማረፍ እንዳለብኝ ሊጎበኙ ስለሚችሉ ቦታዎች ዱባይ ደርሰው የተመለሱ ሰዎችን ጠየቅኩኝ በይበልጥ ግን በኢንተርኔት ብዙ ነገር አነበብኩኝ›› የምትለው ፍሬወይኒ የመጀመሪያ ጉዞዋ በመሆኑ ከጊዜ፣ ከገንዘብና ከሌሎች ነገሮች አንፃር ስትመለከተው ጉዞዋ ክፍተቶች ነበረው፡፡ በዝቅተኛ ወጪ የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን መጎብኘት እንደሚቻል የምትናገረው ፍሬወይኒ ታይላንድ ባንኮክን፣ አውሮፓ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ዴንማርክና ጀርመንን ጎብኝታለች፡፡
ጉዞ ለእሷ ገንዘብ ሲኖር የሚደረግ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም የመሄድ አዲስ ቦታዎችን የማየት ፍላጎት በውስጧ አለ፡፡ በፊትም ከጓደኞቿ ጋር በመሆን በአገር ውስጥ ኦሞን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኝታለች፡፡ ‹‹ጉብኝት ብር ስላለኝ ሳይሆን ቅድሚያ የምሰጠውና ገንዘብ አጠራቅሜ የሚደረገውም ነው፡፡ ብዙዎች ጉብኝትን የቅንጦት ነገር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ከእኔ የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች እኔን ገንዘብ ስላለሽ ነው የምትጓዢው ይሉኛል፡፡››
በአሁኑ ወቅት የግል ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰች ሲሆን የምትሠራው በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለጉዞ የምታውለው በየዓመቱ የምትወስደውን ፕሮቪደንት ፈንዷን እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እንሂድ የሚላት ካገኘችና ወጪውን እችለዋለሁ ብላ ካሰበች ወደኋላ አትልም፡፡ በዚህ መልኩ ነው የአውሮፓ ጉዞዋን ከጣልያን ሮም የጀመረችው፡፡
ባደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ጉብኝቶች በሙሉ የተጓዘችው በቱሪስት ቪዛ ሲሆን፣ እንደምትመለስ ለማሳመን ከመሞከር ውጪ የምታሳየው እንደ ቤት መኪናም ያለ ንብረት የላትም፡፡ ‹‹ከባንክ ቡክ ውጪ የማሳየው ነገር የለኝም›› ትላለች፡፡
የመጀመሪያ የአሮውፓ ጉዞዋ በሆነው በሮም ጐግል አድርጋ በሁሉ ነገር ተዘጋጅታ ከመሄድ ባሻገር ያሳያት፣ ሆቴል እንደመያዝ ባሉ ነገሮችም የረዳት ሰው አልነበረም፡፡ ለቀናት በከተማው ተዘዋውራ የጎበኘችው ብቻዋን ነው፡፡ ‹‹ጉብኝት ሲባል ወጪውን ስለምንፈራው ነው እንጂ እዚህ ከተማ ውስጥ ስናመሽ ከምናድርባቸው ሆቴሎች ዝቅ ያለ ዋጋ ያላቸው ሆስቴሎች አሉ በድንኳን የማደርም አማራጭ ያለባቸው እንደ ጣሊያኗ ቬነስ ያሉ ከተሞችም አሉ፡፡››
ፍሬወይኒ እንደምትለው በዚህ ጉዞዋ ሮምን ብቻ ሳይሆን ያወቀችው ራሷን ፈልጋ አግኝታለችም፡፡ ከሮም በኋላ የተሻሉ ሌሎች የአውሮፓ ከተሞችን ብታይም ለሮም ጉብኝቷ ልዩ ቦታ አላት፡፡
በረራ የሚረክስበትን ጊዜ ከመምረጥ፣ በርካሽ ሆቴሎች ከማረፍ ባሻገር በሚጎበኙ ቦታዎች ቀድሞ ቀጠሮ በማስያዝ፣ የአውቶቡስም ይሁን የባቡር ትኬት ቀደም ብሎ (እዚህ ሆና) መቁረጥ ወጪዋን የምትቀንስበት መንገዶች ናቸው፡፡ ለንግድ ሳይሆን የተወሰኑ ዕቃዎችን አምጥቶ ለጓደኞችና ለቤተሰብ አባላት መሸጥም ወጪዋን የምታቻችልበት ሌላው መንገድ ነው፡፡ ሁሌም ጉዞዋን የምታቅደውና ነገሮችን የምታመቻቸው ከሁለትና ሦስት ወር በፊት ነው፡፡
በዝቅተኛ ወጪ የፈለጉትን ቦታ የመጎብኘት መላው በደንብ ገብቶኛል የምትለው ፍሬወይኒ አሁን በየስድስት ወሩ የተለያየ አገር እንደምትጎበኝ ትናገራለች፡፡
ለጉብኝት አውሮፓ ለመሄድ ስትነሳ ሰዎች ነገሩን እንደቅንጦት መመልከት ብቻም ሳይሆን አትመለስም ብለውም ይደመድማሉ፡፡ በምትሄድበት አካባቢ የምታገኛቸው ኢትዮጵያዊያንም ነገሩን በተመሳሳይ መነፅር ይመለከቱታል፡፡ ‹‹ይህ ጉብኝት ለእኛ የሚታሰብ ነገር አይደለም ከሚል አመለካከት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ከገንዘብ ባሻገር የመረጃ ችግርም ስላለብን የውጭ አገር ጉብኝት የማይታሰብ ይሆንብናል›› ትላለች፡፡
መጎብኘት ለእሷ ራስን ፈልጎ ማግኘት፣ የተለያዩ የሕይወት ዘዬዎችን ማወቅ እንጂ አንድ ቦታ አይቶ የመመለስ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሕይወት ለነገሮች የምንሰጠውን ዋጋ፣ ስለ ሕይወት፣ ስለ ዓለም ስለ ሰዎች ያለንን አመለካከት የመቅረፅ የመቀየር ነገርም ነው ጉብኝነት ለእሷ፡፡ ማየት ነገሮችን እንድንጠይቅ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ መቀጠርን አቁማ የራሷን ሥራ መሥራት መፈለግ የዚህ ተፅዕኖ ውጤት ነው ብላ ታምናለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያየ ጉብኝቷ እንደ እሷ ለጉብኝት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን እያጋጠሟት መሆኑን ትናገራለች፡፡ ይህ በዱባይ ወይም በባንኮክ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ቦታዎች ያስተዋለችው ነው፡፡
ምንም እንኳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ለመሄድ ቢያስቡም ወደ ላቲን አሜሪካ መሄድ አልተሳካላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወደዚያ ርካሽ በረራ ማግኘት አለመቻሉ ነው፡፡ ለማየት ፈልጋ ቪዛ ማግኘት ያልቻለችባቸው የአፍሪካ አገሮችም አሉ፡፡ ከተመለከተቻቸው የአውሮፓ አገሮች በተወሰነ መልኩ ይለያዩ የምትላቸውን ስፔንንና ፖርቹጋልን በቅርቡ የመጎብኘት ዕቅድ አላት፡፡ ጉብኝት ቅንጦት ሳይሆን አንድ የሕይወት ክፍል ተደርጎ መታየት አለበት የሚል እምነት አላት፡፡
አዲስ ነገር ማየት ደስታ የሚሰጣት በመሆኑ ጉብኝት ለእሷ የገንዘብ ሳይሆን የፍላጎት ጥያቄ እንደሆነ ትናገራለች ትቅደም ሙሴ፡፡ በአንድ አገራዊ በጎ አድራጎት ድርጅት የምትሠራ ሲሆን ገቢዋ ራሷን ችላ እንድትኖር የሚያስችላት ባለመሆኑ የምትኖረው ከቤተሰቦቿ ጋር ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ብር አጠራቅማ ለጉብኝት ዱባይ ሄዳ ነበር፡፡ የመጓዝ ፍላጎት ካለ ወጪን መቀነስ የሚቻልባቸው በርካታ መንገዶች መኖራቸውን፤ በቆይታዋ ያወጣችው ወጪ ከጠበቀችውና ብዙዎች ከሚገምቱት በታች መሆኑን ትገልጻለች፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ባንኮክ ደርሳ ተመልሳለች፡፡ በዱባዩ ጉብኝቷ የመጀመሪያዋ እንደመሆኑ በደንብ አቅዳ ባለመሄዷ እሷም እንደ ፍሬወይኒ ማየት የሚገባትን ያህል ሳታይ ወጪዋንም በደንብ ሳትቆጣጠር መመለሷን ታስታውሳለች፡፡ የቦንኮክ ጉዞዋ ግን ጥሩ ፕላን የተደረገ ነበር፡፡ ‹‹የበረራ ወጪ የሚቀንስበትን ጊዜ መምረጥ፡፡ እንደዚህ ያሉ ጉዞዎችን የሚያመቻቹ ኤጀንሲዎችም ስላሉ አማራጮች በደንብ አሉ፡፡››
ጉብኝት የተለያዩ ባህሎችን፣ የአኗኗር ዘዬዎችን እንዲሁም አመለካከቶችን ለማወቅ በር በመሆኑ ገንዘብ ቢኖራት በረዥም ጊዜ ገንዘብ አጠራቅማ ሳይሆን በየጊዜው የምታደርገው ይሆን እንደነበር በቁጭት ትናገራለች፡፡
ብር እያጠራቀመች ለጉብኝት ማዋልዋ በዙሪያዋ ባሉ እንደ ቅንጦት የሚታይ ቢሆንም እሷም እንደ ፍሬወይኒ ሁሉ ጉብኝት እንደ ሕይወት ክፍል መታየት አለበት የሚል እምነት አላት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎች ለጉብኝት የንግድ አማራጮችን ለመመልከትም ቢሆን እየሄዱ መሆናቸው ስለ ጉብኝት የአመለካከት ለውጥ እየመጣ የመሆኑ ማሳያ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ በተለይም ገንዘብ ስላለቸው ወይም ስለተረፋቸው ሳይሆን እንደ እሷ በደንብ አቅደውና ወጪያቸውን የሚያቻችሉበትን መንገድ ቀይሰው የሚጓዙ እየበዙ መሆን ትልቅ ዕርምጃ ነው ትላለች፡፡
በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ኔትወርክ ኢንጂነር ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት ወደ ቻይና ጓንጁ ሄዶ ነበር፡፡ የሄደው አንድ ዕቃ ለማስጠገንና ሌላም ዕቃ ለመግዛት ነበር፡፡ ወጪውን ለመቀነስ እንደ በሶ፣ ጭኮና ቋንጣ ያሉ ምግቦችን ይዞ ነበር የተጓዘው፡፡ ‹‹ጉብኝት የሚባል ነገር ትዝ እንዲለኝ ሁሉ አልፈልግም›› በማለት እሱም ጉብኝት ቅንጦት እንጂ ለኢትዮጵያዊ ለዚያውም እንደሱ ላለ የሚታሰብ አይደለም የሚል አመለካከት እንደነበረው ይገልጻል፡፡
በሌላ በኩል እሱም የምግብና የመኝታ ወጪ እንደሚታሰበው ከፍተኛ አለመሆኑን በጓንጁ እዚህ ካለ አራት ወይም ሦስት ኮከብ ሆቴል ጋር በሚስተካከል ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል በ16 ዶላር ማደሩን በማስረጃነት ይጠቅሳል፡፡
ስለጉብኝት የነበረው ሐሳብ እንዴት እንደተለወጠ ጠየቅነው፡፡ ሥራውን ወደ ማጠናቀቁ ላይ ሳለ እንደነገሩም ቢሆን የተወሰኑ ቦታዎችን ጎብኝቶ ነበር፡፡ በዚያ አጋጣሚ በውስጡ የመጎብኘት ፍላጎት እንዳለ ተረድቷል፡፡ መጓዝ መጎብኘት የሚያስደስተኝ ሰው መሆኔን አላውቅም ነበር፡፡ አሁን እስከዛሬ የተለያዩ ቦታዎችን ያለመጎብኘቴ ይቆጨኛል›› ይላል፡፡
እሱ እንደሚለው ከዚህ ወዲህ ግን የተለያዩ ቦታዎችን መመልከት አንድ የሕይወቱ ክፍል ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ የተጓዘ ሰው ጉብኝት የቅንጦት ነገር አለመሆኑን ይረዳል የሚል እምነት አለው፡፡ እንደ ፍሬወይኒና ትቅደም መጓዝና መጎብኘት ለሚያስደስተው ሰው ወጪን የመቀነስ አማራጮች መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡ ‹‹ለምሳሌ ብዙ የቤት ዕቃ የሚገዛ ሰው ቻይና ሄዶ ቢገዛ፣ ሰዎች አንድ ሁለት እንደ ሞባይል ያሉ ነገሮችን ይዘው ቢመጡና ቢሸጡ በሌሎችም አማራጮች የጉዞ ወጪን መሸፈን ይቻላል›› ይላል፡፡
ከገና በፊት ባንኮክን የመጎብኘት ዕቅድ አለው፡፡ አሁን ለሱ ጉብኝት ትምህርት ቤት ሳይገቡ የመማሪያ መንገድ፣ ሕይወትን በተለየ መንገድ የመመልከቻ መነፅር፣ ሕይወትን ማጣፈጫ ቅመምም ነው፡፡
በዓመት ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ በርካታ ሰዎችን በዝቅተኛ ወጪ ወደ ዱባይ፣ ባንኮክ፣ ማሌዥያ፣ ኬንያ፣ ሲሸልስና የመሳሰሉት አገሮች የትኬት፣ ሆቴልና ቪዛ ሁኔታን አመቻችቶ የሚወስድበት ፓኬጅ እንዳለው የፎር ዊንድስ ቱር ኤንድ ትራቭል ቱር ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ አየነ በላይ ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱን ፓኬጅ የሚያዘጋጁት ከተጓዦች የሚያገኙትን ትርፍ አስበው ሳይሆን ኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ከሌሎች አየር መንገዶች ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ለንግድ ከሚሄዱ ባሻገር ለመጎብኘት የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን፤ ለጫጉላ መሄድም እየታየ መሆኑን ይናገራሉ አቶ አየነ፡፡ ብዙዎቹ ተጓዦች ሴቶች መሆናቸውንም አስተውለዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያለ ታዳጊ አገር ከበለፀጉ አገሮች በሚመጡ ቱሪስቶች መጎብኘቱ እንጂ ዜጎቹ ቱሪስት ሆነው የተለያዩ የዓለም ክፍልን ለመጎብኘት መንቀሳቀሳቸው የተለመደ አይደለም፡፡ ይህ የብዙ ኢትዮጵያውያን የጉብኝት ጉዞ ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ምንም እንኳ አስፈላጊ ነገሮችን ቢያሟሉ ቪዛ ይከለከላሉ፡፡ ቪዛ አግኝተው ሲሄዱም በሚደርሱበት ማንነታቸውን መሠረት ያደረገ ተፅዕኖ ይደርስባቸዋል፡፡
ፍሬወይኒ በሁለቱም አጋጣሚዎች አልፋለች፡፡ በመጀመሪያ የአውሮፓ ጉዞዋ ጣልያን አየር ማረፊያ ላይ ጥቁሮች ተለይተው ስለ ጉዟቸው አጠቃላይ ሁኔታ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደያዙ ሁሉ መጠየቃቸውን ታስታውሳለች፡፡ እናርፍበታለን ያሉት ሆቴል ተደውሎ ሁሉ ተጣርቷል፡፡ ‹‹ደስ አይልም ግን ብዙ ጥቁር ቱሪስት ስለሌለ የዚህ ዓይነት አጋጣሚን መጠበቅ አለብን››
በሌላ በኩል ቻይና ለጉብኝት የሄዱ ሰዎች ነገሮች የሚታዩት ከገበያ አንፃር በመሆኑ የገንዘብ ምንጭ መሆን እስከቻለ ድረስ ሁሉም ሰው እኩል ነው የሚል ዓይነት አመለካከት እንደሚንፀባረቅ ገልጸውልናል፡፡