ሰላም! ሰላም! “ትናንትና ልጄን ዛሬ ደግሞ እናቴን፣ ጉድ ነው ዘንድሮ አለ አውራ ዶሮ፤” ሲባል ሰምታችኋል? ለነገሩ ዘንድሮ ዕድሜ ለካፒታል ዕድገትና ለኑሮ ውድነት ዶሮዎች በካራ ከመገዝገዝ በከረቫት አንገታቸው ወደ መላጥ አድገዋል። ‘ታዲያ በእንስሳት እንቀልድ እንጂ ሰው መሆን ካላማረብን’ አልኩና ሰው ሰምቶኝ እንደሆን ዘወር ስል ባሻዬ አጠገቤ ናቸው። “ጠሩኝ ባሻዬ?” ስላቸው፣ “እኔ ደግሞ አንተ የጠራኸኝ መስሎኝ ነበር፤” ብለው ሳቁ። ተባበርኳቸው። “እባብ ለእባብ ይታያያል ካብ ለካብ፤” አሉ አበው። “ግን እንዲያው አበው ብቻ ሲተርቱ የኖሩት እመው የት ሄደው ነው?” ብዬ ባሻዬን ብጠይቃቸው፣ “መቼ እንደ አሁኑ ፀሐይ ለሁሉም ፊቷን ማሳየት ጀመረች ያኔ?” ብለው መለሱልኝ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ፊት ሲሰጡኝ አልቻልም። የታመቀውን ሁሉ እዘረግፈዋለሁ። ጆሮ መርጬ ነው ታዲያ። አደራ ደግሞ ‘ጆሮ የየትኛው ፓርቲ ልዩ ምልክት ሆነ?’ ብላችሁ የምርጫ ካርድ ካላወጣን እንዳትሉ። የምርጫ ካርድ እንደ ሆስፒታል ካርድ በፈለጋችሁት ሰዓት የሚወጣ መሰላችሁ እንዴ? ሆ! “ሰው ሁሉ እንዳይሆን ፍፁም ደመኛዬ፣ እያጣራ ይስማ ስግብግብ ጆሮዬ፤” ብሎ ያዜመው ድምፀ መረዋ ጥላሁን ገሠሠ ግን በጣም ናፈቆኛል። ጥበብ፣ የሰው ወርቅ መዋዋስ አጓጉል ለመደችና ፈጠራ ናፈቀና ጎበዝ። እንጃለታችን ዘንድሮ!
እና ምን አልኳቸው፣ “ባሻዬ!” ስል “እ?” አሉ። “እ- የነገር ናት፤” ያለው ማን ነበር? “ፀሐይ ያኔ ፊቷን ለወንድም ለሴትም እኩል የማታሳይበት ጊዜ ከነበረ ማስተዛዘኛዋ ምን ነበር?” ብዬ መጠየቅ። “ማስተዛዘኛ ብትል በቀደም የቆረጥኩት ሎተሪ ማስተዛዘኛ እንዳለው እንጃ። እስኪ እንካ ሎተሪ አዟሪ ስታገኝ ጠይቅልኝ፤” ብለው መተጣጠፍ የበዛባት ለስላሳ ወረቀት አውጥተው ሰጡኝ። ያረሳሱኝ ስለመሰለኝ ቅር አለኝ። በቅሬታችን ልክ ቅራሪ መጠጣቱ ደግሞ ኪስ እያራቆተ አልቻልንም። “ይበሉዋ ማስተዛዘኛው ነበር አልነበረም?” ደግሜ ጠየቅኳቸው። “የፀሐይ ብርሃን ያልታደለ ማን ላይ ያለቅሳል? ያው ጨረቃ ላይ ነዋ! ምነው አደረቅከኝ ልጄ?” ብለው ሲሰላቹ መሰስ አልኩ። ‘ምን መሰስ አስባለህ እንደባለ ዕዳ?’ ላላችሁኝ፣ “ፀሐዩ መንግሥታችን በሚስጥር ኪሱ ጨረቃን ደብቆ ይዞ ፓርላማውን ሳይቆጣጠረው አልቀረም፤” ያለኝ ወዳጄ ትዝ ብሎኝ እላችኋለሁ። እስኪ አሁን ፍዝ ሆነ ደማቅ፣ ብርሃን ተደብቆ ይደበቃል? ኧረ እግዜር ይይለት!
ይገርማችኋል በሥራዬ ፀባይ የተነሳ ወዲያ ወዲህ ስል ብዙ ያጋጥመኛል። ገጠመኝ ደግሞ ነፍስና መንፈሴን ሰቅዞ ይዞ በሐሳብ ያጉላላኛል። መቼስ “ከበጣም መጥፎ፣ መጥፎ ይሻላል፤” እንዳሉት ባለራዕዩ መሪ፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በቢሮክራሲ ጣጣ ከመጉላላት በሐሳብ መጉላላትን እመርጣለሁ። ቀላቀልኩት? ይብላኝ ዘይትና ውኃ እየቀላቀለ ሥራዬ እንደ እንዶድ የነጣ ነው ለሚለን እንጂ የእኔስ ብዙ አያሳጣም። እናም እናትና ልጅ በውርስ ክፍፍል ተጣልተው ነው አሉ ለዓመታት ፍርድ ቤት ተመላልሰው አሻሽጠው የተባልኩትን ቪላ ቤት ያገኘሁት። ልጅዬው በጎን ‘እንዲህ አድርገው እንዲህ በለው’ ብሎኝ ዘወር ሲል እናትዬው በጎን ይመጡና ‘እንደሱ አትበል እንዲያ እንዳይሆን’ እያሉ አስጨነቁኝ። ደመኝነቱን በስምተኛው ሺሕ ትዕንቢት ፈትቼ (ትዕንቢት አንዴ ይፈጸማል እንጂ እንደ ህልም ተደጋግሞ ይፈታል እንዴ? ምነው ታዲያ ትዕንቢቱ መደጋገሙ?) ባልፈውም ሥራዬን እንዴት ልሥራ? ለአንዱ የነገርኩትን ዋጋ ወይ ልጅዬው ወይ እናትዬው ያፈርሱታል። በመሀል እንኳን የቤቱ የእኔም ምርጊት ሊከዳኝ ሆነ። “ሃይ ባይ አስማሚ ዘመድ የላቸውም እንዴ እነዚህ ሰዎች?” ብዬ ሳላስበው ሐሜት ጀመርኩ። “ዛሬ ጊዜ ምንስ ብትሆን ማን ይገደውና? ‘ዋሽቶ አስማሚ’ እኮ ተረት ሆኖ ቀርቷል፤” አሉኝ። ተረቱን ማን ነበር የተረተው? የኖረው መስሎኝ። እንግዲያስ ተረቱ ተረት ሆኖ ከቀረ ተራቹ ምን ሆኗል ሊባል ነው? አጣሩልኝ! ‘ፌስቡክ’ ላይ የሰው ‘ፎቶ’ ስናገላብጥ መዋል ብቻም እኮ ያስተዛዝባል!
እኔስ አንዳንዴ ናላዬ ሲዞር “ምነው ሰማይ ዝም አለ?” እላታለሁ። ያው ማንጠግቦሽን ነዋ። እኔ እኮ የቱ ተምርጦ የቱ ይተዋል እንደሚሉት ዙሪያዬን ብዙ አንቺዎች የሉኝም። ታዲያ በዚህ ስመካ አንዳንድ ወዳጆቼ ሰይፍ ይመዙብኛል። ያው የዘንድሮ ነገር አመዛዘዝ ከሰይፍ አይተናነስም በሚል ነው። “አንበርብር ሁለት ዓይና ሆኖ ‘አልማትርም’ ይላል፤” ይሉኛል። ‘ያየ አመነዘረ’ በሚለው ፍርጃ ሁለት ዓይና ሆኖ እንዴት ይረጋል እኮ ነው። አይ ሰው! እህ ለመወሰን ብለን እንታወር? እንዴት ያለ ነገር ነው እናንተ? ሌላው ይቅር በምሪት ልማት ነው መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የምንደርሰው? ‘ዓይኔን ግንባር ያርገው ብላችሁ አትማሉ፣ ይቸግር የለም ወይ መሪ ማባበሉ’ ቢል አገር ሁሉ መሪዎቻችንስ ቅር አይላቸውም? አይገርማችሁም ግን? “እኔማ በየት በየት አድርጎ በየጎጇችን የሌለን ታማኝነት፣ በአደባባይ አምጡት ባይ ጉድ ከመቼ ወዲህ እንደሆንን አላውቅም፤” ስለው የባሻዬን ልጅ፣ “መቀበል ብቻ የለመደ ታዲያ ሌላ ምን ያውቃል?” ብሎኛል። ነገር ማሾር ይችልበት አይደል?
ብቻ የቤተሰብ አደረጃጀትና አያያዝ እየተዘባረቀ እሱን ሳናስተካክል ዘለን የመንግሥት ሕፀፅ ላይ ብቻ መንገብገብ። እና አሁን ይኼን ሁሉ በምን አነሳሁት? . . . አዎ፣ “ምነው ሰማይ ዝም አለ?” አልኳት ስል ‘ማነች አላችሁኝ’ ብዬ ነገር ፈልጌያችሁ ነው ያነሳሁት። “ምን ይሁን ታዲያ?” ጠየቀች ማንጠግቦሽ። “ምናለበት ተቀዶ ቁጭ ብዬ እሱን ብሰፋ ብዬ ነዋ። መሬትማ ወስፌያችንን አዶለዶመችው እኮ?” ስላት፣ “ቁናህን መስፋት ነዋ። እሱ ካቃተህ በመሬት ቅድ ገብተህ መጥፋት ነው፤” አትለኝ መሰላችሁ? ወይ ትዳር? እያደር ስንቱን ይገልጣል? መቼ እኔ ባለ ቅኔ ማግባቴን አውቄ? ሰው ለካ ነገር ሲቀደድ መስፋት ያቃተው አገባብና አወጣቱን መጀመርያ አላጠና እያለ ነው። ደግሞ ፖለቲካ እንዳይመስላችሁ የማወራው!
መቼ ዕለት ደግሞ ውልውል ያለች አዲስ ‘ኤግዝኪውቲቭ’ አሻሽጬ ገዥው ደንበኛዬ የሊብሬ ጣጣውን ለመጨረስ ይዞኝ መንገድ ትራንስፖርት ሄድን። ስለተግባባን በቀላሉ ሊለቀኝ አልፈለገም። አብሬው ልሠራቸው ስለምችላቸው ሥራዎች በየመሀሉ ያወራኛል። ብዙ የጠበቅኩባቸው ጉድ ሲያደርጉኝ ስለኖሩ በሰው ተስፋ ማድረግ ትቻለሁ። ‘ይሁን’ እያልኩ አዳምጠዋለሁ። “በዕድሜዬ ሰውን ከሰውነት ተራ ሲያስወጣው የታዘብኩት ነፃነትን ማጣትና አጉል ተስፋ ሰው ላይ መጣል ነው፤” ይሉኛል ባሻ አዘውትረው። ምናልባት ይኼን ለመረዳት የእሳቸውን ያህል ዕድሜ ዛሬ የሚያስፈልገን አይመስለኝም። “ዕድሜ ለሲስተሙ!” ይላል አንዱ ካጠገቤ ቆሞ እየሳቀ። “አቤት?” ስለው በራሴ ዛቢያ ስሽከረከር እያየኝ ነው የሚያላግጥ እያልኩ፣ “አይ አንተን አይደለም ‘ሲስተሙን’ ነው፤” ብሎ ለበጣውን ቀጠለ።
“ይኼው ስንተኛ ቀኔ ነው ዛሬ። እመጣለሁ ‘ሲስተም’ ተበላሽቷል ነው። ፋይል እስኪወጣ መጠበቅ ማለት የምፅዓት ቀን ለማየት ከመጓጓት ጋር እኩል ነው፤” እያለ ያጉተመትማል። ሳቁ ቦግ ቦግ በሚለው የተገታተረ ደም ሥሩ ተደበቀ። አንዱ ይመጣና ደግሞ፣ “በዚህ ‘የዲጂታል ዘመን’ በ‘ማንዋል’ ሲሠሩ ትንሽ አይደብራቸውም? ቢያንስ ለራሳቸው እንኳ፤” ይላል። “እነሱ ምን ያድርጉ? ‘ሲስተሙ’ ነው አልኩህ እኮ፤” ይላል የወዲያኛው። እኔ ግራ ገባኝ። ‘ሲስተም’ የሚሉት ቃል ሌላ የማላውቀው ትርጉም ይኖረው ይሆን? ብዬ አንዷን የተማረች የምትመስል ቀዘባ (በምን ቀን እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚችልን አዋቂ እንዳልነው አይታወቅም) “ሲስተም’ ምን ማለት ነው?” ብዬ ብጠይቃት ሌባ ጣቷን ጭንቅላቷ ላይ ቀስራ “ጤነኛ ነህ?” ብላ ገላመጠችኝ። ብዙ ሴቶች የትንሽ ትልቁን ጥያቄና ንግግር ለምን ለከፋ እንደሚያደርጉት አልገባህ ብሎኝ ይኼው ላረጅ ነው። ‘ሲስተም’ አጣራለሁ ብዬ ‘ሲስተሜ’ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገባና ዝም አልኩ። ወይ አፍሪካ! ቅርጿ ራሱ የጥያቄ ምልክት እንደሚመስል ልብ ብላችኋል ግን?
በሉ እንሰነባበት። ጉዳዬን ጨራርሼ አንዳንድ ቀጠሮችን ለበነጋው አስተላልፌ የባሻዬን ልጅ ደወልኩለት። ሳይመሽ ግሮሰሪ ተሰይሟል። የተለመደችዋ ግሮሰሪ። ገሰገስኩ። “ገዳይ ቢያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል” ዓይነት ግስጋሴ በሉት። ለነገሩ ዘንድሮ ውስጣችን እየጨለመብን በቁም የሞትነው ልቀናል። ‹‹In My Opinion›› የሚል ጨምሩበት። ከአገር በቀሉ፣ የባዕዳኑ ቋንቋ ጥሩ እያስተላለፈንና ሳንግባባ እያግባባን ስለሆነ ማለቴ ነው። እናም ስደርስ የባሻዬ ልጅ በቀልድ ተቀበለኝ። “በርከት ያሉ የቤት እንስሳት የሚያረቡ ባልና ሚስት ናቸው…” አለ። “ . . . እና በትዳር የቆዩባቸውን የተቀደሱ ዓመታት ድል ባለ ድግስ ለመዘከርና ለመጪው ጥሩ ለመመኘት አሰቡ። እንስሳቱም በዕለቱ ምን ስጦታ ይዘው እንደሚሄዱ መወያየት ጀመሩ። አሳማና ዶሮ ጥጋቸውን ይዘው ይጠያየቃሉ። ‘መቼም ጌቶቻችን መልካምነታቸው የበዛ ነው። እንክብካቤያቸውም ልዩ ነው። ታዲያ ስለፍቅራቸው ይህን በመሰለ ቀናቸው ምን ይዘህ ለመሄድ አስብሃል?’ ትላለች ዶሮ።
አሳማ ይመልሳል። ‘አንድ 20 እንቁላል ይዤ ብሄድ ያንሳል? ይልቅ አንቺ ምን ይዘሽ ለመሄድ አስበሻል?’ ተራውን ይጠይቃል። ‘ሁለት ኪሎ የአሳማ ሥጋ ብያለሁ፤’ አለች ዶሮ ሆዬ እልሃለሁ። ይኼው ነው ገበያው አንበርብር!” አለኝና ከት ብሎ ሳቀ። ነገሩ ስላላማረኝ ከቀልዱ ባሻገር ሊነግረኝ ያሰበውን እንዲነግረኝ ሳውጣጣው፣ “ራስ ወዳድነት አላስቀምጠን አለ አንበርብር። ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝብ የሚያገለግል ጠፋ። ከራሱ አውጥቶ የሚሰጥ ሰው እጅግ በጣም ኢምንት ሆነ። ዕውቀት ያለው ዕውቀቱን ይቆጥባል። ገንዘብ ያለው ቆጥቦ አልጠግብ ብሏል። ሥልጣን ያለው ተገልጋይነቱ እስካልተነካበት ድረስ አገለግላለሁ ብሎ ለይስሙላ ይምላል። ነጋዴው በአምላኩ ስም የንግድ ፈቃድ ያወጣ ነው የሚመስለው። ‘ይድፋኝ! ያጨልምብኝ!’ እያለ ያጭበረብራል። ራሱን የሚሰጥና ያለውን የሚካፍል ሰው ጠፋ እኮ!” ብሎ ሌላ ደብል አዘዘ። አያያዙ እንደማያዋጣ ስላሰብኩ ‘መጣሁ’ ብዬ ወጥቼ በዚያው ቀረሁ። ይኼ ምን ይባላል ታዲያ? ስም አውጡለት እስኪ። እኔ በበኩሌ የሲስተም መናጋት ብዙ ያሳየናል ብየዋለሁ፡፡ መልካም ሰንበት!