Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየመከነ ተስፋ

  የመከነ ተስፋ

  ቀን:

  ከዋናው መንገድ በታች የሚገኘው ኮረኮንች መንገድ ቁልቁለታማ ነው፡፡ በወጉ ባልተሠራው መንገድ ላይ ከሚገኘው የጅማው አጂፕ ኬላ ኮንዶሚኒየም ጐራ ለማለት መንገዱ አስቸጋሪ ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም ከሳይቱ መግቢያ ጀምሮ አካባቢውን መጥፎ ጠረን በክሎታል፡፡ ከየብሎኩ ሥር የሚገኙ ንግድ ቤቶችም ጭር ያሉና በአቧራ የተሸፈኑ ናቸው፡፡ በሳይቱ የሚገኙ የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ሴፕቲክ ታንኮች በሙሉ ሞልተዋል፡፡ በሚገባ ያልተዘጉ ፍሳሽ ማስወገጃዎችም ለቀናት የተጠራቀመውን ፍሳሽ ያሳያሉ፡፡ ሞልተው የፈሰሱም አሉ፡፡ አካባቢውን የበከለው መጥፎ ጠረንም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡

  አብዛኛው የኮንዶሚኒየሙ አካባቢ በሰገራ ተሸፍኗል፡፡ የተወሰኑ ሕንፃዎች መሠረታቸው በሰገራ ተበላሽቷል፡፡ እስከ ገአፉ የሞላውን ሴፕቲክ ታንክ ማስተንፈሻ የተበጀ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ ቦዮቹ ሞልተዋል፡፡ በየአካባቢው የግንባታ ድንጋይ ተቆልሎ መመልከት ቀሪ የግንባታ ሥራዎች መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡  

  በየብሎኩ የሚገኙ የዝናብ ማስወገጃ ቱቦዎች ከየአሸንዳቸው ተለይተዋል፡፡ የወረዙ፣ አልጌ የያዙ ግድግዳዎች ይታያሉ፡፡ ፀሐዩ እየጠነከረ በመጣ ቁጥር የአካባቢው ጠረን አስከፊ ይሆናል፡፡

  አካባቢው ፀጥ ብሏል፡፡ የሚንቀሳቀስ ሰውም አይታይም፡፡ አብዛኞቹ ብሎኮች ከታች (ግራንውድ) ላይ ክፍት ናቸው፡፡ ሰው አይኖርባቸውም፡፡ ከአንደኛው ብሎክ ከታች የሚገኙ ሦስት ቤቶችም ባለቤቶቻቸው ጥለዋቸው ከወጡ ሰነባብተዋል፡፡ መስኮቶቻቸው በጥቂቱ ገርበብ ብሏል፡፡ ከመሠረቱ ጀምሮ በሰገራ የተበከሉ ሲሆን የዝንቦች መዋያም ሆነዋል፡፡ አንደኛው ክፍል እስከ ግድግዳው ድረስ በፍሳሽ ተሞልቷል፡፡ ወለሉ ላይ ከወዳደቁ ፕላስቲክ ጠርሙሶች በቀር ምንም አይታይም፡፡

  በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ በግል ሥራ የተሰማራ ሲሆን፣ በሳይቱ መኖር ከጀመረ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቀደም ሲል በአካባቢው በሚገኝ አንድ ግቢ ውስጥ ተከራይቶ ይኖር ነበር፡፡ በከተማው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሲጀመርም በዕድሉ ለመካተት ተመዘገበ፡፡ ዕድል ፊቷን የሰጠችው ወጣት የቤት ዕጣውን አገኘ፡፡ አጋጣሚው ከኪራይ ቤት እንዲላቀቅ ከማድረጉ ባለፈም የራሴ የሚለው ነገር እንደሰጠው በማሰብ ተደስቶ ነበር፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ ቤቱን ከተረከበ በኋላ ግን ያላሰበው ነገር አጋጠመው፡፡ ፍሳሽ በፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ በመውጣት ፈንታ ቤቱን ያጥለቀልቀው ጀመር፡፡ ግራውንድ ላይ እንደመኖሩም ከላይ የሚወጣው ፍሳሽ ይበልጥ አስቸገረው፡፡

  የፍሳሽ ማጠራቀሚያው ሴፕቲክ ታንክ በመሙላቱ ይሆናል በሚል ግምት ከነዋሪዎቹ ጋር በመተባበር በየጊዜው ቢያስመጥጡም በማግስቱ ተመልሶ ይሞላ ስለነበር ግራ ገባው፡፡ ነዋሪዎቹም ከዛሬ ነገ ይስተካከላል በሚል ተስፋም ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ድንገት ከተፍ ብሎ የሚያጥለቀልቀውን ፍሳሽ ከቤት ማስወጣትና ማፅዳት ለጊዜው ያለው መፍትሔ ነበር፡፡ ‹‹በተለያዩ ጊዜያት ቤት ውስጥ ፕሮግራም አዘጋጅቼ ከጓደኞቼ ጋር እየተጫወትን ፍሳሹ ድንገት ቤቱን አጥለቅልቆት ያውቃል፤›› በማለት በቤቱ በቆየባቸው ጊዜያት ያጋጥመው የነበረውን ፈተና ያስታውሳል፡፡

  ትዳር መሥርቶ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል በሚል ተስፋ ቤቱ ውስጥ መኖር ቢጀምርም አልተሳካለትም፡፡ ይልቁኑ ሊቆጣጠሩት በሚያዳግት መልኩ ፍሳሽ ይፈትናቸው ገባ፡፡ በመካከል ባለቤቱ ጸነሰች፡፡ የ2007 ዓ.ም. ክረምትም መቋቋም በማይችሉት መጠን ቤታቸው በፍሳሽ ተጥለቀለቀ፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በቀላሉ ሊወጡት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ንብረቶቻቸውን ሸክፈው ቤቱን ለቀው ወጡ፡፡ በኪራይ ቤት ለመኖርም እንደተገደዱ ወጣቱ ተናግሯል፡፡

  የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲጀመር በአገሪቱ የሚታየውን ሥር የሰደደ የመኖሪያ ቤት ችግር እንደሚቀርፍ ታምኖ ነበር፡፡ የቤት ችግር ያለባቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በረዥም ጥበቃ ተፈትነዋል፡፡ የማያወላዳ ገቢ ያላቸው ሁሉ በዕጣው ለመካተት ብዙ ጥረዋል፡፡ ለዚህም የዕጣው ተካፋይ የሚያደርጋቸውን ወርኃዊ ክፍያ ከጀመሩ በኋላ የሚያቋርጡ አልያም ዕጣቸውን አሳልፈው የሚሸጡ ሰዎች መኖራቸው ይሰማል፡፡

  ሒደቱን ተከትለው የቤት ዕጣ የደረሳቸው በአጋጣሚው ቢደሰቱም፣ ከግንባታ ጥራት አልያም በሌላ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸው ጥቂት አይባሉም፡፡ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የውኃ አገልግሎት ያልተሟላላቸው ሳይቶች አሉ፡፡ ከፍሳሽ ጋር በተያያዘም በርካታ አቤቱታዎች ይሰማሉ፡፡ ከመሬት የሸሹም አሉ፡፡

  የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በአዲስ አበባ ቀደም ተብሎ ቢጀመርም በጅማና በሌሎች ከተሞች ግንባታው ከተስፋፋ ሰነባብቷል፡፡ በጅማ ጥቂት የማይባሉ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች አሉ፡፡ ለባለ ዕጣዎች ከተላለፉም ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ሳይቶች ባለባቸው የጥራት ችግር ነዋሪዎቹ እየተሰቃዩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ቢካተቱም በውሳኔአቸው የተጸጸቱ ጥቂት አይባሉም፡፡ በተለይም በየብሎኮቹ ምድር ላይ የሚኖሩ የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አቅም ያላቸው ቤታቸውን ጥለው ለኪራይ ሲዳረጉ፣ አቅም ያነሳቸው ግን ከፍሳሽ ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡

  ባለትዳርና የልጅ አባት ናቸው፡፡ በአጂፕ ኬላ ሳይት መኖር ከጀመሩ አራት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በሳይቱ የኮሚቴ አባልም ናቸው፡፡ ምድር ላይ ከሚገኙት ቤቶች በአንዱ ይኖራሉ፡፡ ሳይቱ የፍሳሽ ችግር ስላለበትም ከሌላው የሳይቱ ነዋሪ በበለጠ ችግሩ ያጠቃቸዋል፡፡ ‹‹ገንዘባችንን ሙጥጥ አድርጐ የበላ ቤት ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ አፍስሼበታለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ መኖር ከጀመርኩ ዕለት አንስቶ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ እንደ ኪሳራ ነው የምቆጥረው፤›› በማለት በወጉ ያልተዋቀረው የፍሳሽ ማስወገጃ ችግር እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡

  እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሳይቱ የግንባታ ችግር አለበት፡፡ ፍሳሽም ወደ ሴፕቲክ ታንኩ አይገባም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ነዋሪዎቹ በፍሳሽ ይቸገራሉ፡፡ በተለይም በታችኛው ቤቶች ላይ የተለየ ጫና እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ሁኔታው ግራ ያጋባቸው የሳይቱ ነዋሪዎችም ችግሩን ለመከላከል የፍሳሽ ማስኬጃ ፖሴቶዎችን ዘግተዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ የወሰዱት ዕርምጃ ትክክለኛ ባይመልስም ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ነገር ግን እኔ መዝጋት ሕጋዊ ባለመሆኑ አልዘጋሁም፡፡ በመሆኑም ፍሳሽ በሙሉ እኔ ቤት ጋር ይተኛል፤›› በማለት ጠረኑ በሕፃን ልጃቸውና በመላው ቤተሰቡ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

  ሁኔታውን ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቁም፣ ለረጅም ጊዜያት መፍትሔ ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማው መስተዳድር ከወራት በፊት በሳይቱ የጀመረው ሥራ የሚያበረታታ ቢሆምን፣ ችግራቸው በየብሎኩ ላይ ከሚገኘው የፍሳሽ ማስወገጃ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የተወሰደው ዕርምጃ ችግራቸውን እንደማይቀርፍ ያስረዳሉ፡፡

  በጅማ በሚገኙ ሌሎች ኮንዶሚኒየም ሳይቶች ላይ ተመሳሳይ ችግር ታይቷል፡፡ ዲፖ ኮንዶሚኒየም ሳይት ይባላል፡፡ ለነዋሪዎቹ ከተላለፈ ዓመት አልፎታል፡፡ በተሻለ ጥራት የተገነባ ቢመስልም፣ የፍሳሽ ችግር አለበት፡፡ ከየብሎኩ የሚወጣ ፍሳሽም ሜዳው ላይ ተኝቷል፡፡ ከጐኑ ሕፃናት ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ፍሳሹን ተሻግራ ከሕፃናቱ መቀላቀል የተሳናት ታዳጊም ከአንደኛው ጥግ ቆማለች፡፡ ሥፍራውን ባየንበት ወቅት ብዙዎቹ ሕፃናት የሚያስሉ ነበሩ፡፡

  በሳይቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ብሎክ ግራውንድ ላይ የሚገኙ ቤቶች ሰው አይኖርባቸውም፡፡ በራቸውም ተዘግቷል፡፡ ቤቶቹን የሞላው ፍሳሽም ከበሩ አልፎ በረንዳውን አርሷል፡፡ ከርቀት ለሚያይ መፀዳጃ ቤት እንጂ መኖሪያ ቤት አይመስልም፡፡ በክረምት ወራት ችግሩ እንደሚብስ የገለጹት የሳይቱ የጥበቃ ሠራተኛ፣ ከቀናት በፊት በጣለው ዝናብ ብዙዎቹ ቤቶች ተጥለቅልቀው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አደጋው የተከሰተው ሌሊት አካባቢ ቢሆንም፣ በሰዎችና በንብረት ላይ ችግር ከመፈጠሩ አስቀድሞ እንደተደረሰላቸው ጠቁመዋል፡፡

  ሌላው በተመሳሳይ ችግር የሚፈተነው ኩሎበር አካባቢ የሚገኘው የኮዶሚኒየም ሳይት ነው፡፡ ከሳይቱ መግቢያ ጀምሮ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ተኝቷል፡፡ ጠረኑን ለመከላከልም ነዋሪዎቹ ጥቁር ጋዝ ያፈሰሱ ቢሆንም ብዙ አልረዳቸውም፡፡ አቶ ሐሰን አብዱራህማን የሳይቱ ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ በሳይቱ መኖር ከጀመሩ ጥቂት የማይባሉ ጊዜያት አስቆጥረዋል፡፡

  ዕጣው ሲደርሳቸው ከቤት ችግር እንደሚላቀቁ እምነት ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከንቱ ተስፋ እንደነበር ይሰማቸው ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ጥሩ ኑሮ እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል፡፡ ቤታቸውን በጥሩ ጥሩ የቤት ቁሳቁሶች አስውበውታል፡፡ ነገር ግን ቄንጠኛ አምፖል ከሰቀሉበት ጣሪያ በኩል የሚወርደው ፈሳሽ ቤቱ በመጥፎ ጠረን እንዲበከል አድርጎታል፡፡ ጠረኑን ለመከላከል ልዩ ልዩ መዓዛ ያላቸውን ኤር ፍሬሽነሮች ይጠቀማሉ፡፡ ሰንደልም እንዲሁ፡፡ ይሁን እንጂ ጠረኑን መለወጥ አቅቷቸዋል፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ሰንደል ተለኩሶ የነበረ አይመስልም፡፡ ፀሐያማው ቀን በፈጠረው ሙቀትም ቤቱ ትንፍግ እንዲል አድርጐታል፡፡ ልጆቻቸውም በጠረኑ ተቸግረዋል፡፡ በየጊዜውም በጉንፋን እንዲጠቁ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡

  በጉዳዩ የከተማው አስተዳደር አቶ ሰለሞን አበበ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የተነሱት ችግሮች ከነዋሪዎቹ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ናቸው፡፡ በፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ውስጥ ያልተገቡ ነገሮች በመጨመር ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ብዙ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ ይህንን ማስተካከልም የነዋሪዎቹ እንጂ የመንግሥት ግዴታ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውጪ የሚከሰቱ ችግሮችን እንደሚያስተካከሉ ‹‹በአጂፕ ኬላ በሚገኘው ሳይት የታየውን ችግር 16 ሚሊዮን ብር መድበን እያስተካከልን እንገኛለን፤›› በማለት ከቤቶቹ ውጪ በሳይቱ ላይ ለሚታየው ችግር መፍትሔ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ከሳይቶቹ የውስጥ ክፍል ተከሰቱ የተባሉ የፍሳሽ ችግሮችን ለማስተካከል እንደማይገደድ ‹‹ሲረከቡ አይተውና መርምረው ነው፡፡ ከገቡበት በኋላ የሚከሰት ችግርን የማስተካከል ግዴታ የለብንም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡          

  አንድ ሰው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲረከብ የኤሌክትሪክ መስመር መሥራቱን አይቶ ሊረከብ ይችላል፡፡ የሕንፃውን ውጫዊ አካል እንዲሁም ውጭ ለውጭ የተዘረጉ የፍሳሽ መስመሮችንም እንዲሁ፡፡ ሆኖም ቤቱ በጥራት ይሠራ አይሠራ፣ ውስጥ ለውስጥ የሚዘረጉ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ይሠሩ አይሠሩ፣ ለቤቶቹ ግንባታ የዋለው ግብአት በሙሉ ጥራቱን ይጠብቅ አይጠብቅ መቆጣጣርና አረጋግጦ መስጠት ያለበት አሠሪው አካል ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት አኗኗር ለኢትዮጵያውያን አዲስ ከመሆኑ አንፃርም ቤቶቹን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት የመንግሥት ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በኮንዶሚኒየም ቤቶች የግንባታ ጥራት እንዲሁም በቤቱ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አሠሪው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img