Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያገረሸው የጊኒ ዎርም

ያገረሸው የጊኒ ዎርም

ቀን:

ንፅህናው ያልተጠበቀና በጥገኞች የተበከለን ውኃ በመጠጣት የሚከሰተው የጊኒ ዎርም በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የተለያዩ የዓለም አገሮችን በአንድ ወቅት አዳርሶ ነበር፡፡ በጊኒ ዎርም የተበከለን ውኃ በሚጠጣበት ጊዜ ዕጩ ወደ ሰው አካል ይገባል፡፡ ዕጩ በሰውነት ክፍል ውስጥ ወደ ትልንት የሚያድግ ሲሆን፣ እስከ አንድ ሜትር ይረዝማል፡፡

የጊኒ ዎርም በሽታ አስከፊነት ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን የሚያውቁት በሰውነታቸው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ተሸሽጎ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ከባድ የስቃይ ስሜት የሚሰማው በታችኛው የእግር ክፍል ነው፡፡ በተደረጉ የዘመቻ ሥራዎች በሽታውን ከ187 አገሮች ማጥፋት እንደተቻለ ቻድ፣ ማሊ፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ግን ከበሽታው ነፃ እንዳልነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2016 ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

በእነዚህ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያ በተሠሩ የዘመቻ ሥራዎች ከጊኒ ዎርም ነፃ ለመሆን ጫፍ ላይ ደርሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑን የወረርሽኙ ማገርሸት ዜና ከወደ ጋምቤላ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ወቅት ዳግመኛ የተከሰተው የጊኒ ዎርም ወረርሽኝ እንግዳ ነገር አሳትይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ወረርሽኙ ከሰዎች ላይ በስተቀር በእንስሳት ታይቶ የማይታወቅ ቢሆንም በውሻና ዝንጅሮዎች ላይ መታየቱ ግርታን ፈጥሯል፡፡

ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረው የጊኒ ዎርም በሽታ በጋምቤላ ክልል በሁለት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የእርሻ ቦታዎች ላይ ነው የታየው፡፡ እንደ አዲስ ያገረሸው ጊኒ ዎርም  ከሰዎች ባሻገር በውሾችና ዝንጆሮዎች ላይ እንደተገኘ የተናገሩት በክልሉ በሚገኘው ካርተር ማዕከል የጊኒ ወርም በሽታ ማጥፊያ ቢሮ ኃላፊው አቶ ኒና ኦኬሎ ናቸው፡፡

አቶ ኒና እንዳብራሩት ድርጅታቸው ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ወረርሽኙን ከክልሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሰዎችን ማዕከል ያደረገ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ግን በሽታው ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በውሾች ላይ ሊከሰት ችሏል፡፡ በውሾች ላይ በተደረገው ምርመራም በሽታው በሰዎች ላይ ከሚከሰተው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በ2008 ዓ.ም. በክልሉ ጎግና አበቦ በተባሉ ወረዳዎች በእርሻዎች ላይ የተከሰተውን በሽታ ተከትሎ በተደረገው አሰሳ ዝንጆሮዎች ከዚሁ በሽታ ጋር በተገናኘ ሞተው መገኘታቸውንና በቅርቡም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የጊኒ ዎርም በሽታ ወደ በኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ጨርሶ ለማጥፋት የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ 26 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት የታየ ቢሆንም ወረርሽኙ ዳግመኛ ተከስቶ በአገር ደረጃ ሥጋት ሆኗል፡፡ በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠፋ ሲሆን፣ እስካሁን መጥፋት ያልቻለው ከቻድና ከኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ በሽታው ዳግመኛ የተከሰተው አገሪቱ ከበሽታው ነፃ መሆኗን የሚያሳይ ሰርተፍኬት ልታገኝ ከተቃረበች በኋላ ነው፡፡  በቅርቡ በጋምቤላ እርሻዎች ላይ በተከሰተው ወረርሽኝ እንደገና ወደ ኋላ ልትመለስ ችላለች፡፡ ዳግመኛ በተከሰተው የጊኒ ዎርም ወረርሽኝ 15 ሰዎች ተይዘዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኦማን አኳይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በእርሻ ቦታዎቹ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሲሆን፣ በአንድ እርሻ ጣቢያ እስከ 300 የሚደርሱ ሠራተኞች ይቀጠራሉ፡፡ ለሠራተኞቹ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሌሎች የመጀመርያ ዕርዳታ መስጠት የሚችሉ ክሊኒኮች በየእርሻዎቹ እንዲኖሩ ግድ ቢሆንም ኢንቨስተሮች ይህንን ሳያሟሉ ፈቃድ ስለሚሰጣቸው ችግሩ ሊከሰት መቻሉን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ከበሽታው ነፃ የመሆናችን ጊዜ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል፤›› ሲሉ ዳግመኛ መከሰቱ ነገሮችን ውስብስብ እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡ አቶ ኦማን በተጨማሪም አሁንም ጥብቅ ቁጥጥር ካልተደረገ ጉዳዩ ከአቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ ኡቦንግ አንድ ኢንቨስትመንት የሚጠበቅበትን ሳያሟላ ፈቃድ እንዴት ሊሰጠው ይችላል? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹በመጀመርያ በክልሉ ከ600 የሚሆኑ ኢንቨስትሮች ፈቃድ ወስደው ወደ እርሻ ኢንቨስትመንት የገቡ ሲሆኑ፣ ፈቃዱን የወሰዱት የተጠየቀውን እንደሚያሟሉ በመግለጽ ነበር፡፡ ባደረግነው ክትትል ግን እንደማይተገብሩት ለመገንዘብ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡ ዕርምጃ ለመውሰድም ተወካዮቻቸው እንጂ ባለቤቱ ስለማይገኝ ለቁጥጥር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ዳግመኛ ያገረሸው በሽታው ባለው የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር ምክንያት መሆኑን በመገንዘብ ባደረግነው አሰሳ ካሉት 600 እርሻዎች ውስጥ ንፁህ ውኃ ለሠራተኞቻቸው የሚያቀርቡት 16ቱ ብቻ እንደሆኑ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡

 የጊኒ ወርም በሽታ ለመጀመርያ ጊዜ በጊኒ የተገኘ ሲሆን፣ ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህም አንዱ የንፁህ ውኃ መጠጥ አለመኖርና አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ቫይረሱ ክፍት በሆኑ ኩሬዎች እንቁላሉን የሚጥል ሲሆን፣ ከዚያ ኩሬ የጠጣ ሰው እንቁላሉን አብሮ በመጠጣት ትሉ ወደ ሰውነቱ እንዳይገባ ይሆናል፡፡ በሰውነቱ ውስጥም ለአንድ ዓመት ያህል ምንም ሕመም ሳያሳይ በመቆየት በብዛት ከወገብ በታች በማሳከክና በማቁሰል ረዥም ትል ይወጣል፡፡ በዚህ ወቅት ታማሚ በአፋጣኝ ሕክምና ካላገኘም ለሞት ይዳረጋል፡፡

የጊኒ ዎርም በሽታ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1978 ነበር በትሮፒካል አካባቢ የሚገኝና መድኃኒት የሌለው፣ ከ20 ወረርሽኝ በሽታዎች መካከል አንዱ ሆኖ በዓለም ጤና ድርጅት የተመዘገበው፡፡

ከኩፍኝ ቀጥሎ ያለ መድኃኒት የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር ብቻ ሥርጭቱን መከላከል የሚቻል፣ ለድህነት የሚዳርግና ከድህነት ጋር በተያያዘ የሚከሰት በሽታ በመሆን ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም. ስለ በሽታው በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በወቅቱ 1,129 ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውና በ99 አካባቢዎች መስፋፋቱ ታውቋል፡፡

በወቅቱም የጋምቤላ ክልል ከተጠቀሱት አካባቢዎች 70 የሚሆኑትን የደቡብ ክልል ደግሞ 29ኙን በመያዝ በሽታውን በከፍተኛ ቁጥር በማስተናገድ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት በተደረገ ጥረት የበሽታውን ሥርጭት በ99 በመቶ መግታት ተችሎ ነበር፡፡ በበሽታው አዲስ የተያዘ ሰው ሪፖርትም ላለፉት ዓመታት ከሁለት አኃዝ በታች ሆኖ ቆይቷል፡፡

የጊኒ ዎርም በሽታ አምጪ ትል ቁመቱ እስከ አንድ ሜትር ሊደርስ እንደሚችልና ትሉ በባለሙያ እገዛ ከበሽተኛው አካል እስኪወጣ ድረስ ግለሰቡ በጊዜያዊ ቤት እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...