ወንድምን መናቅ ማለት አቃሎ እና ዋጋ እንደሌለው አድርጎ ማየት፣ ትኩረትና ግምት አለመስጠት ነው፡፡ ይህ ስሜት በሙስሊሞች መካከል ከተከሰተ ትስስራቸውን ክፉኛ የሚጎዳ በሽታ ነው፡፡ ምክንያቱም ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ወንድማማቾች በመልክ፣ በሀገር፣ በዘር ወይም በሌላ ነገር ቢለያዩም አንዱ ሌላውን ሊንቅ እና ሊያጣጥል ፈጽሞ አይገባም፡፡ የእምነት ትስስር ከየትኛውም ትስስር በላይና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነውና፡፡
አንድ ሰው ወንጀል በመፈጸሙም ሊንቀው አይገባም፡፡ ምክንያቱም የራሱንም ሆነ የሌላውን ፍጻሜ አላወቀምና፡፡ አላህ ትልቅ ወንጀል የሠራን ሰው አማኝ ሆኖ ከሞተ ሊምረው ይችላል፡፡ በትንሽ ወንጀል እሳት የሚያስገባው ሰውም ይኖራል፡፡ አላህ እንዲህ ሲል እውነትን ተናግሯል፡፡
‹‹አላህ ለርሱ ተጋሪ መደረጉን (ሽርክን) ፈጽሞ አይምርም፡፡ ከዚህ ባሻገር ያሉትን (ጥፋቶች) ግን ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡›› (አል ኒሣእ 48)
ሰውየው ወንጀለኛ ሲያይ ማድረግ ያለበት ወንጀል ፈጻሚውን መናቅ ሳይሆን ለአላህ ሲል መቆጣት፣ ከወንጀል እንዲታቀብ መምከርና መከልከል ነው፡፡ ወንጀለኛውን ማኩረፍና ማግለል ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን ወንጀለኛውን የመናቅ ስሜት ወደልቦናው እንዳይሰርጽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ይህ ስሜት ኩራት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ወደ ኩራት የሚያደርስ መንገድ ነው፡፡
- ሐሰን ታጁ ‹‹ኒዓም›› (2001)