የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ባካሄደው የአሥረኛ መደበኛ የጠቅላይ ምክር ቤትና 12ኛ መደበኛ የጠቅላላ ጉባዔ ላይ በፌዴሬሽኑ የታቀፉ አባል ኩባንያዎች ዓመታዊ መዋጮአቸውን ከአምስት ሺሕ ብር ወደ አሥር ሺሕ ብር ከፍ እንዲያደርጉ በሙሉ ድምፅ ወሰነ፡፡ ጉባዔው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በግዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ስብሰባ ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የግል ድርጅቶች ክፍያ በሚገባ ተጠንቶ አንድ ደረጃ ላይ እስከሚደረስ ድረስ ከዚህ በፊት ሲከፍሉት በነበረው መጠን ዓመታዊ ክፍያቸውን እንዲያከናውኑ ከጉባዔው ውሳኔ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኩባንያዎቹ የክፍያ መጠን ሊያድግ የቻለው ከፌዴሬሽኑ የሚያገኙት የአገልግሎት ደረጃ እየተሻሻለና እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡ ይህም ማለት ፌዴሬሽኑ የአሠሪና ሠራተኛ ክርክሮችን በሁለትዮሽ፣ ከዚህም ባለፈ በሦስትዮሽ ስብሰባ መፍታት ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄድ ክርክር ከሆነ ኩባንያው የፌዴሬሽኑ አባል እስከሆነ ድረስ በአነስተኛ ወጪ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ተከታትሎ ያስፈጽምለታል፡፡
ፌዴሬሽኑ እንደ ገቢ ምንጭ የሚያገለግል የራሱን ሕንፃ እንዲገነባና ባንክም እንዲያቋቁም፣ እንዲሁም የግል ትምህርት ተቋማት ባለንብረቶች ማኅበር በፍላጎቱ ከፌዴሬሽኑ ጋር የሚቀላቀልበትንና የአሠሪዎቹ ፌዴሬሽን ወደ ኮንፌዴሬሽን የሚለወጥበት ሁኔታ እንዲመቻች ጉባዔው ወስኗል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔውም ከላይ ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን ተግባሮች የማደራጀት ኃላፊነትን ለጠቅላይ ምክር ቤቱ ሰጥቷል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱም ውሳኔዎችን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲቻል የፌዴሬሽኑ ቦርድ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ምክር ቤቱን እንዲጠራ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር ፌዴሬሽኑ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ሕጉና አዋጁ እንደሚፈቅድለት፣ ለዚህም ዕውን መሆን መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ያለ አራት ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ በነፃ መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
ጉባዔው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አገራዊ ዕቅድ ውስጥ ለባለሀብቱ የተሰጠው ድርሻ እንዲተገበርና ግቡን እንዲመታ፣ እንዲሁም ባለሀብቱ ወደሚጠብቀው ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲገባ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጿል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ ልማታዊ ባለሀብቱ ለአገሪቱ ዕድገትና ለለውጥ ዕርምጃ ዋነኛው አቅም መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የተነሳ አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማላቀቅ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ አስተዋጽኦውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዚዛ መሀመድ ‹‹ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመ በርካታ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ በዚህም ሒደት አያሌ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ ለአባላቱም መብትና ጥቅም መከበር፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሰላምና ልማት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአሠሪውንም ድምፅ ወደሚያስተጋባ ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) የኢትዮጵያና የሶማሊያ ተጠሪ ሚስተር ጆርጅ አኩቱ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን አስባለች፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ያለውን 500 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ 2017 ዓ.ም. ላይ ወደ 1000 ዶላር ከፍ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የሚቻለው ደግሞ የሥራ ዕድል የሚያስገኙና ትርፋማ የሆኑ ኢንተፕራይዞችን በስፋት እንዲቋቋሙ በማድረግ መሆኑን ተጠሪው ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ረገድ የቀጣሪዎችና የሠራተኞች አስተዋጽኦ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ጉባዔያችን ለልማታችንና ለዕድገታችን›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚሁ ጉባዔ ላይ ከሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ፌዴሬሽኑ ያከናወናቸውን ተግባራት የዳሰሰ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከቀረበውም ሪፖርት ለመረዳት እንደቻለው ቀደም ብለው ከተመሠረቱትም ሆነ ከአዳዲሶቹ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የሚቀርበው የድጋፍ ይደረግልን ጥያቄ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የአባላት ቁጥር እጅግ የጨመረ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ የሒሳብ ቋት ውስጥ እየገባ ያለው ገንዘብ ከዋናው ጽሕፈት ቤት የሚሰበሰበው ብቻ መሆኑን፣ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የጠባቂነት አዝማሚያ መታየቱ፣ ካጋጠሙ ችግሮች ተጠቃሽ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሞ በርካታ የሥልጠና ወጪ የተደረገባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የሚጠበቀውን ያህል መጠናከር አለመቻላቸውም እንደ ክፍተት መታየቱን አመላክቷል፡፡