Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚያዋጣንን ማብቀል አልቻልንም ያሉ የኦሮሞ ዞን አርሶ አደሮች ኡኡታ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዲስ አበባ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ሲጓዙ የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንን ያገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ዞኖች ሞቃታማና ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ የውኃ ሀብት ያላቸው ናቸው፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ከሚበቅሉ የግብርና ምርቶች መካከል በቆሎ፣ ማሽላ፣ ማሾ፣ ሽንኩርትና ትምባሆ ቅጠል ይገኙበታል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ላለፉት 70 ዓመታት የትምባሆ ቅጠል ሲያመርቱ የቆዩ ሲሆን፣ ይህንን ቅጠል ለብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት በተቆረጠ ዋጋ ያስረክባሉ፡፡

እነዚህ አርሶ አደሮች በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሸዋሮቢት አካባቢ ያሉት ዘንድሮ ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሲናገሩ፣ በአንፃሩ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ የሚገኙ ገበሬዎች በወረዳ አስተዳደሩ ትምባሆ እንዳይተክሉ በመከልከላቸው ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

አቶ ኑርሁሴን ዓሊ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በባልጭ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው፡፡ አቶ ሲራጅ አቡበከር ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ሸዋሮቢት ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው መርዬ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው፡፡

የዘንድሮ ዓመት የትምባሆ ምርት ለሁለቱ ገበሬዎች የተለያየ ስሜት ፈጥሯል፡፡ ሁኔታው አቶ ኑርሁሴንን ሲያበሳጭ፣ አቶ አቡበከርን አስደስቷል፡፡ አቶ ኑርሁሴን በባልጭ ቀበሌ ውስጥ ከባለቤታቸውና ከሰባት ልጆቻቸው ጋር ባላቸው አራት ሔክታር መሬት የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ሕይወታቸውን ይገፋሉ፡፡

‹‹መሬቱ ከደጋ ምርቶች በስተቀር ለሁሉም ይሆናል፤›› የሚሉት አቶ ኑርሁሴን ሽንኩርት፣ ማሾ፣ በቆሎና ትምባሆ ቅጠል በሰፊው እንደሚያመርቱ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አቶ ኑርሁሴን በዘንድሮ ምርት ዘመን ካላቸው መሬት ውስጥ አንድ ሔክታር የሚሆነውን ትምባሆ ቅጠል ለማልማት ሙሉ ዝግጅት ቢያጠናቅቁም፣ የጂሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳደር ማንኛውም አርሶ አደር ትምባሆ ቅጠል ማልማት እንደሌለበት በማዘዙ ከፍተኛ ችግር እንደተፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ኑርሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት 15 ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ ዘንድሮም የትምባሆ ቅጠል ለማልማት መሬታቸውን ከማዘጋጀታቸው በተጨማሪ ችግኝ፣ ማዳበሪያና ኬሚካል ከብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ተረክበው ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም ከማዕከል በሚለቀቅላቸው መስኖ ችግኙን መትከላቸውን ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን የወረዳው አስተዳደር የተከሉትን የትምባሆ ችግኝ እንዲነቅሉት ትዕዛዝ ማስተላለፉን አቶ ኑርሁሴን ገልጸው፣ የተከሉትን ችግኝ ላለመንቀል ጥረት ቢያደርጉም፣ በደረሰባቸው ከፍተኛ ማስፈራራትና ወከባ ችግኙን ነቃቅለው መጣላቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ኑርሁሴን እንደሚናገሩት፣ የትምባሆ ልማት የሚያካሂዱት በአንድ ሔክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ በተቀረው ሦስት ሔክታር መሬት ላይ ማሾ፣ በቆሎና ሽንኩርት ይለማሉ፡፡ በአንድ ሔክታር መሬት ላይ የሚያለሙትን የትምባሆ ቅጠል በእርጥብነቱ በኪሎ አራት ብር ከሰባ ሳንቲም ሽያጭ ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ምርት በጥቂት ወራት ውስጥ እስከ መቶ ሺሕ ብር ድረስ እንደሚያገኙ አቶ ኑርሁሴን ተናግረዋል፡፡

አቶ ኑርሁሴን እንደሚሉት ከሚያለሟቸው የግብርና ምርቶች ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኙት ከዚሁ የትምባሆ ምርት ነበር፡፡ ቤተሰባቸውም የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ይህ ምርት ወሳኝ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

‹‹ለምን እንደተከለከልን ግልፅ አይደለም፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያሉ ወዳጆቻችን እያለሙ ነው፡፡ የእነሱ አጎራባች የሆነው የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የጂሌ ጥሙጋ ወረዳ አርሶ አደሮች ለምን ተከለከልን?›› በማለት አቶ ኑርሁሴን ጉዳዩ ግልፅ እንዳልሆነላቸው ይጠይቃሉ፡፡

ወይዘሮ ዘይነባ ያሲን የአቶ ኑርሁሴንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ወይዘሮ ዘይነባ በዚሁ ወረዳ በጥቁሬ ቀበሌ የሚገኙ እማወራ አርሶ አደር ናቸው፡፡

ወይዘሮ ዘይነባ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ላለፉት 20 ዓመታት ቤተሰባቸው በአብላጫው ሲተዳደር የቆየው ከትምባሆ በሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ‹‹መሬታችንን ሽጠን እንድንሰደድ ካልተፈለገ በቀር ትምባሆ እንዳንተክል ልንከለከል አይገባም፤›› በማለት ምሬታቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ ዘይነባ፣ ትምባሆ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዋነኛ መንቀሳቀሻ ሞተር ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን የወረዳ አስተዳደሩ እንዳንተክል በመከልከሉ የእርሻ መሬቱ ጦሙን አድሯል ይላሉ፡፡

የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አርሶ አደሮች ሲያዝኑ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ገበሬዎች በአንፃሩ ደስተኞች ናቸው፡፡ አቶ ሲራጅ አቡበከር ሸዋሮቢት አካባቢ በምትገኘው ቀወት ወረዳ ውስጥ ማርዬ ቀበሌ በአንድ ሔክታር መሬት ላይ ከሌላ አርሶ አደር ጋር የእኩል ትምባሆ ቅጠል ያለማሉ፡፡ ‹‹ዘንድሮ ምርቱ ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ ገቢ ያስገኝልናል፤›› በማለት አቶ አቡበከር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ አቡበከር ከትምባሆ የሚያገኙት ገንዘብ ጥሩ በመሆኑ በአባታቸው መሬት ላይ መኖርያ ቤት በመገንባት ትዳር ከመሠረቱ ሦስት ዓመት ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡ አቶ አቡበከር የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ለእሳቸውና ለአካባቢው አርሶ አደሮች የትምባሆ ልማት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል፡፡

አቶ አቡበከር ከትምባሆ በተጨማሪ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በጋራ ማሾ፣ ማሽላና ሽንኩርት እንደሚያለሙና ትልቅ ገቢ የሚያገኙት ግን ከትምባሆ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ዞኖች የተገኘው የሪፖርተር ዘጋቢ በሮቢት ወንዝ ላይ በተካሄደ የመስኖ ግድብ በርካታ አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ልማቶችን እያካሄዱ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በአካባቢው ሽንኩርት፣ ማሾና የትምባሆ ቅጠል በመልማት ላይ ሲገኝ፣ አርሶ አደሮችም በምርት ሒደቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአንፃሩ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በባልጭ ከጥቁሬና በወሰን ቆርቆር ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የትምባሆ ቅጠል እንዳያመርቱ በመከልከላቸው የመስኖ ውኃ በመባከን ላይ ይገኛል፡፡ የመስኖው ውኃው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመፍሰስ ላይ ይገኛል፡፡ በትምባሆ ቅጠል ልማት በተፈጠረው አለመግባባት ዘግይቶ የተዘራው ማሽላና በቆሎን እየጠወለገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ትምባሆ በመትከልና ባለመትከል፣ በወረዳው አስተዳደርና በአርሶ አደሮቹ መካከል ሲካሄድ የቆየው አለመግባባት በወረዳው አስተዳደር አሸናፊነት በመጠናቀቁ በርካታ የእርሻ መሬት ጦም ማደሩም ታይቷል፡፡

ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማኅበር በ1935 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነት ኢምፔሪያል ኢትዮጵያ የትምባሆ ሞኖፖል ተብሎ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ አልፎ በአዋጅ ቁጥር 37/1992 ብሔራዊ የትምባሆ ኢንተርፕራይዝ ተብሎ የተቋቋመ ሲሆን በአገር ውስጥ ትምባሆና የትምባሆ ውጤቶችን የማምረት፣ የማቀነባበር፣ በፋብሪካ የመሥራት፣ የማከፋፈል፣ ወደ አገር ውስጥ የማስገባትና ወደ ውጭ አገር የመላክ ብቸኛ መብት አለው፡፡

ብሔራዊ ትምባሆ በአሁኑ ወቅት 33 በመቶ በየመኑ ኩባንያ ሼባ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተያዘ ሲሆን፣ ቀሪው 67 በመቶ በመንግሥት የተያዘ ተቋም ነው፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አራት እርሻ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፣ ጣቢያዎቹ በደቡብ ክልል ብላቴ፣ ሐዋሳና ወላይታ አካባቢዎች፣ በአማራ ክልል ደግሞ ሸዋሮቢት ከተማ መሠረቱን ጥሏል፡፡

በብላቴ የሚገኘው ጣቢያ የራሱ እርሻና ትምባሆ ቅጠል መጥበሻ ማሽኖች ያለው ሲሆን፣ በተቀሩት ጣቢያዎች የትምባሆ ቅጠል መጥበሻ ጣቢያዎች አሉት፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች የትምባሆ ቅጠል የሚያገኙት የአካባቢው ገበሬዎች አምርተው ሲያስረክቡት ነው፡፡

ከእነዚህ አራት ጣቢያዎች በተጨማሪ ድርጅቱ በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ አካባቢ የትምባሆ እርሻ ጣቢያ ለማቋቋም በሒደት ላይ ነው፡፡ የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት የሥነ ምግባር መኮንንና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ ተወካይ አቶ ጌቱ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለትምባሆ ልማት አመቺ የአየር ጠባይና ሰፋፊ መሬቶች ቢኖሯትም ድርጅታቸው በውጭ ምንዛሪ ከህንድ፣ ከብራዚልና ከቻይና የትምባሆ ቅጠል ያስመጣል፡፡

ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ልፋት በሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ድርጅቱ የትምባሆ ምርቱን በአገር ውስጥ ለማሟላት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መሥሪያ ቤታቸው የተለያዩ ሲጋራዎችን ለማምረት የሚጠቀምበትን የትምባሆ ቅጠል ግማሹ ከውጭ እንደሚያስገባና ለዚህም ሰባት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ትምባሆ ድርጅቱ በዓመት ለመንግሥት ከ880 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስገባ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ከታክስ በፊት 377,405,974 ብር ገቢ አስገብቷል፡፡ ድርጅቱ ለመንግሥት የሚያስገባውን ዓመታዊ ገቢ ለማሳደግና ከውጭ የሚያስገባውን የትምባሆ ቅጠል በአገር ውስጥ ለማምረት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም ጥረቱ ግን እንቅፋት አላጣውም፡፡

የብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ሐጎስ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ግብርና ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ድርጅታቸው የመንግሥት ገቢ ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ወጪ ለማስቀረት ከጀመራቸው ፕሮጀክቶች መካከል ዋነኛ ትኩረት የተሰጠው የሮቢ ትምባሆ እርሻ ልማት ድርጅት ተጠቃሽ ነው፡፡

የሮቢ ትምባሆ እርሻ ልማት ድርጅት በ1949 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ ይህንን ተቋም በማደራጀትና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ በመደገፍ የበለጠ ምርታማና ውጤታማ በማድረግ ዕቅዱን ለማሳካት አቅዷል፡፡ ከክልሉ መንግሥት በተፈቀደው መሠረት አዲስ እርሻ ጣቢያ አጣዬ ላይ መከፈቱን፣ ሮቢና ጀውኃ ላይ ያሉትን እርሻ ጣቢያዎች ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የማደራጀት ሥራ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የሥራ አስኪያጁ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ነገር ግን ደብዳቤው እንደሚገልጸው በ2007 መኸር፣ የሮቢ ትምባሆ እርሻ ልማት እንደተለመደው በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በባልጭ፣ ጥቁሬና በወሰን ቆርቁር ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ትምባሆ በመትከል ላይ በነበሩበት ወቅት ከሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በጂሌ ጥሙጋ ወረዳ በባልጭ ጥቁሬ ቀበሌ አስተዳደር የግብርና ባለሙያዎች፣ ትምባሆ እንዳይተከል፣ ለተተከለውም ትምባሆ የመስኖ ውኃ እንዳይሰጥ ከልክሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትምባሆ የተከሉ አርሶ አደሮች የተከሉትን ትምባሆ እንዲነቅሉ መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ለክልሉ ግብርና ቢሮ በጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህ ሒደት በ20.5 ሔክታር መሬት ላይ በ106 ገበሬዎች የተተከለ ትምባሆ በውኃ እጥረት ደርቋል፡፡ 50 ሔክታር መሬት የሚሸፍን በውጭ ምንዛሪ የተገዛ የትምባሆ ዘር ከጥቅም ውጭ ሆኗል፤›› በማለት ሥራ አስኪያጁ ለክልሉ ግብርና ቢሮ ቅሬታቸውን በደብዳቤ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለኬሚካል፣ ለማዳበርያና ምርጥ ዘር ተገዝቶ በተነቀለው ችግኝ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ አራት ሚሊዮን ብር ሊያወጣ የሚችል ምርት ታጥቋል፡፡

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በሦስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርቱን ለማምረት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በወረዳ አስተዳደር ተደናቅፏል በማለት አቶ ጌቱ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ኦሮሞ ዞን ጄሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳደር አቶ ሞሄ ኡመር በስፍራው የተገኘው የሪፖርተር ዘጋቢ የወረዳው አርሶ አደሮች የትምባሆ ቅጠል እንዳይተክሉ የተከለከሉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም፣ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ነገር ግን ምንጮች እንደገለጹት ትምባሆ ቅጠል የማልማት ዕቅድ ከማዕከል የወረደ ባለመሆኑና ከክልሉ የወረዳውን ሰብል ብቻ አርሶ አደሮቹ እንዲያመርቱ በሚል ምክንያት አርሶ አደሮች ሌሎች ተክሎችን እንዳይተክሉ እያስገደደ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ቅሬታ የቀረበለት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስቸኳይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ዋለ ለኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ አርሶ አደሮች በየትኛውም መንገድ ቢሆን በእርሻ መሬታቸው ላይ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝላቸውን ሰብል የማምረት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

የትምባሆ ተክል ለማልማት የፈለጉ አርሶ አደሮችን፣ በጫና የተከለከሉትን የትምባሆ ተክል እንዲነቅሉ የማድረግ፣ ድርጅቱ ከአርሶ አደሮች ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ስምምነት በማቋረጥ ልማቱ እንዲቆም ከማድረግ ይልቅ ድርጅቱ እየሠራ ያለው የልማት ሥራ ያለውን አገራዊ ፋይዳ ለአርሶ አደሩም የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሮች ከውጫዊ ጫና ነፃ ሆነው የመረጡትን ሰብል የሚያለሙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው የክልሉ ግብርና ቢሮ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ይህንን ትዕዛዝ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተቀበለው የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በሥሩ ለሚገኘው የወረዳ መዋቅር ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ውሳኔው በወረዳና በቀበሌ አስተዳደር አካላት አለመከበሩ ታውቋል፡፡

‹‹በወረዳና በቀበሌ አስተዳደር አካላት ውሳኔው አለመከበሩ በድርጅታችን ዕቅድ ላይ የራሱን ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፤›› በማለት አቶ ጌቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ኑርሁሴንና ወይዘሮ ዜይነባን ጨምሮ በሦስት የኦሮሞ ዞን ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የጂሌ ጥሙጋ ወረዳና የቀበሌ አስተዳደሮቹን ይሁንታ በጉጉት ቢጠብቁም፣ እስካሁን ጠብ ያለ በጎ ምላሽ የለም፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች የአማራ ክልላዊ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች