Sunday, September 24, 2023

አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መንግሥት መዋቅር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በአምስተኛ ዘመን የመጀመሪያ ጉባዔው፣ አገሪቱን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚያስተዳድር መንግሥት መሥርቷል፡፡

ይህንን የምክር ቤቱን ጉባዔ የመሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አፈ ጉባዔ ካስመረጡ በኋላ በድጋሚ የተመረጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ፣ የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት እንዲመሠረት መድረኩን ከፍተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኰንን ፓርቲው ያጫቸውን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን አቅርበው በሙሉ ድምፅ አፀድቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቀጣዩ ቀን በፓርላማው ተገኝተው ካቢኔያቸውን የመሠረቱ ሲሆን፣ በፓርላማውም 30 የካቢኔ አባላትን አሹመዋል፡፡

የካቢኔ ሹመቱ ከመካሄዱ በፊት የካቢኔ አባላቱ የሚወከሉበት የመንግሥት መዋቅርን አቅርበዋል፡፡ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበው አዋጅ መግቢያ የልማታዊ መንግሥት መርሆዎችን የተከተለ ጥብቅ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራርን መፍጠር፣ ጠንካራና ውጤታማ የአስፈጻሚ ተቋማት መዋቅርን መፍጠር፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተገቢ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችል አደረጃጀት ትኩረት መስጠት፣ በውድድር ውስጥ ተፎካካሪ መሆንን ታሳቢ ያደረገ መዋቅር ለመፍጠር መዋቅሩ እንደተዘጋጀ ያስረዳል፡፡

የመንግሥት መዋቅር ሊያካትታቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለያዩ መሆናቸውን የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር የሚወስነው የረቂቅ አዋጁ መግቢያ ያስረዳል፡፡

በአብዛኛው ተቀባይነት ያላቸው አደረጃጀቶች የመንግሥት አስተዳደር አካላትን (በኢትዮጵያ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትርና የካቢኔ ጽሕፈት ቤቶች)፣ የውጭና የደኅንነት ጉዳዮችን (መከላከያ፣ የአገሮች ግንኙነት፣ ኢሚግሬሽን)፣ ኢኮኖሚና መሠረተ ልማትን (ንግድ፣ የንግድ ግንኙነቶች፣ ፋይናንስ፣ ኮንስትራክሽን፣ ስፔሻል ፕላኒንግ፣ ቱሪዝም)፣ አካባቢያዊ ሁኔታና የተፈጥሮ ሀብትን የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት አስተዳደር፣ ውሃ፣ ኃይል፣ ዓሳ፣ ደን፣ መስኖ፣ ማዕድን፣ የተፈጥሮ መስህቦች እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶችንና ማኅበራዊ እሴቶችን (ትምህርት፣ ባህል፣ ጤና፣ መረጃ፣ የውስጥ ጉዳዮች፣ ፍትሕ፣ የሰው ኃይል፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ስፖርት፣ ቱሪዝም) ያካትታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት አወቃቀር ከዚህ ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀት የተለየ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ መዋቅር ውስጥ ሆኖ የተለያዩ ድርጅቶች ሲዋሀዱና ሲፈርሱ በተለያዩ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ ለአብነት ያህል የግብርና ሚኒስቴር ወደ ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር፣ እንደገና ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ተብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሹመታቸው ማግሥት ያቀረቡት የመዋቅር ለውጥ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ

በአዲሱ የሥራ አስፈጻሚው መዋቅር መሠረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት 20 ናቸው፡፡

ዋና ዋናዎቹ የደኅንነት ተቋማት ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ባንክና ሌሎችም ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ከነባሮቹ ውጭ ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ እንዲቋቋምና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ይህ ኤጀንሲ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በፍጥነት ለተጐጂዎች መድረስና አደጋ ከመከሰቱ በፊትም ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠትን ያካትታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና ለዚህ ተጠሪ የሆኑት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቦርድ የሚተዳደርና ተጠሪነቱም ለፓርላማ ነበር፡፡ ይህ የቀድሞው አወቃቀር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትማቸው አዲስ ዘመንና ሌሎች ጋዜጦች አስፈጻሚውን አካል በነፃነት ለመከታተል የሚያስችለው ነበር፡፡

የአሁኑ አደረጃጀት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትንም ሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲን በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሥር ሆነው ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን መደረጉ፣ አስፈጻሚውን አካል በነፃነት የመከታተልና እንከኖችን የመንቀስ ተልዕኳቸው ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የሥራ አስፈጻሚው አፍ ብቻ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

ሌላው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ እንዲሆን የተደረገው ተቋም ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር የነበረው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ይህ ተቋም አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ኃላፊነት ከተጣለባቸው ተቋሞች አንዱ ቢሆንም፣ ወታደራዊ ባህሪው የፋይናንስ አጠቃቀሙን ኦዲት ለማድረግ አስቸጋሪ አድርጐት ነበር፡፡ በመሆኑም የተቋሙ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ኮርፖሬሽኑ የሚያንቀሳቅሰውን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ግብርና

መሠረታዊ የመዋቅር ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል ዋናው የግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሁሉንም የግብርና ዘርፎች በሰብል ምርት፣ በእንስሳት ልማት፣ በዓሳ ሀብት፣ በደን ልማት፣ በአፈር የተፈጥሮ ይዘት ጥበቃና የመሳሰሉትን ሰፋፊ ተግባሮችን በአንድ ተቋም ውስጥ ያጨቀ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ተገቢውን ትስስር በግብርናውና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መፍጠር ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ይህንን ውስብስብ ሥራ በአንድ ተቋም ውስጥ ከማጨቅ ግብርና ሚኒስቴርን ለሁለት እንዲከፈል ተደርጓል፡፡ እነዚህም የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ናቸው፡፡

ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተጠሪ የሚሆኑ ተቋማት የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ፣ የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ በአዲስ መልክ የሚቋቋመው የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ኤጀንሲ፣ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና (አዲስ የሚቋቋም ነው) ብሔራዊ የአፈር ምርምር ማዕከል፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጅ፣ የስትራቴጂክ ምግብ መጠባበቂያ ክምችት ኤጀንሲ ናቸው፡፡

ሌላው የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከተሰጡት ከፍተኛ ኃላፊነቶች መካከል የአንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ፣ ለአንስሳት ሀብት ልማት የግብዓት አቅርቦት፣ በሽታን የመከላከል፣ የኳራንቲን ሥራ ማከናወን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለዚህ ሚኒስቴር ተጠሪ የሚሆኑ ተቋማት የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደር ባለሥልጣን፣ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል፣ ብሔራዊ ሰው ሰራሽ የእንስሳት ማርቢያ ዘዴዎችም ይገኙበታል፡፡

ኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ዘርፍ

በኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ዘርፍ ከሚካተቱ ተቋማት መካከል የቀድሞው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይገኝበታል፡፡

ይህ ተቋም ለሁለት እንዲከፈል ተደርጐ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴርና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተፈጥረዋል፡፡ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሥር ከተካተቱ ተቋማት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መሬት ኤጀንሲ፣ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ተብሎ የሚቋቋም አዲስ መሥሪያ ቤት፣ እንዲሁም የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተብሎ የሚመሠረት አዲስ መሥሪያ ቤት ተጠሪ ይሆናሉ፡፡

ሌላኛው ተቋም የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሲሆን፣ ይህ ተቋም የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ የሚያስፈጽምና ሬጉላቶሪ ፕሮግራሞችን በበላይነት ተከታትሎ የሚመራ አዲስ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥር የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ነው፡፡ በዚሁ የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት የመንግሥት መዋቅር ውስጥ አዲስ የተፈጠረው ተቋም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ነው፡፡

ይህ ተቋም በንግድ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማትና ግንባታ፣ በትራንስፖርት፣ እንዲሁም በሌሎች አገልግሎቶች የተሰማሩ ድርጅቶች ከሚያስተዳድሩት ሀብትና ከሚጠበቅባቸው ውጤት አንፃር መንግሥት በተሟላ ሁኔታ የቅርብ አመራር፣ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግባቸው ናቸው፡፡

ለዚህ ተቋም ተጠሪ የሚሆኑ መሥሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተብሎ በአዲስ መልክ የሚደራጅ ተቋም፣ በተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅና ጋዝ ምርትና አቅርቦት ኮርፖሬሽን፣ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተብለው በአዲስ መልክ የሚደራጁ የልማት ድርጅቶች ተጠሪ ይሆናሉ፡፡

ይህ ተቋም በዋነኝነት የሚደራጀው የመንግሥት የውጭ ብድር ጤነኝነትን ለመከታተል መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም ማለት መንግሥት ዋስትና እየሰጠ የሚያመጣውን ገንዘብ ሥራ ላይ የሚያውሉ የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ አጠቃቀምንና አስተዳደርን መከታተል ነው፡፡ በዚህም መሠረት በቀጥታ ለዚህ ተቋም ተጠሪ ያልሆኑትን ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ያላቸውን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ማንኛውንም የመንግሥት የልማት ድርጅት ይቆጣጠራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንዲፈርሱ፣ ከሌላ ድርጅት ጋር እንዲዋሀዱ ወይም እንዲከፋፈሉ ወይም እንዲሸጡ ለመንግሥት ውሳኔ ያቀርባል፡፡ ይህንን የተመለከተ ግልጽ መመርያ ያዘጋጃል፡፡ በዚህም መሠረት ይህ መዋቅር ሲፈጠር ኪሳራ ላይ የሚገኘው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ይፈርሳል፡፡

በዚሁ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ዘርፍ አዲስ አደረጃጀት ያገኘው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ነው፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በአዋጅ ተለይተው የሚሰጡት ተግባራት እንዳሉ ሆኖ፣ ከኢነርጂ ክፍሎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ብቻ አተኩሮ በመሥራት በዘርፉ የሚታየውን እጥረት ማስወገድ እንዲችል የተዋቀረ ነው፡፡ በተጨማሪም የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን መሠረተ ልማት፣ የከርሰ ምድር ውኃ ልማት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡ በዚህ ተቋም ሥር የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን፣ የዓባይ ተፋሰስ ባለሥልጣን፣ የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለሥልጣን፣ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣ የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት እንደገና ተዋህደው የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን እንዲሆኑ ዕቅድ ስለተያዘ፣ የሚፈጠረው ኮርፖሬሽን ተጠሪነት ለማን እንደሚሆን ገና አልተወሰነም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተብለው ለሁለት ከተከፈሉ ገና ዓመቱ ነው፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ያስተዳድር የነበረው የህንድ የማኔጅመንት ኩባንያ በ20 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥሮ ኮንትራቱ የተጠናቀቀው በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶ በድጋሚ የማዋሀድ ሥራ ውስጥ መገባቱ መንግሥትን ለትችት ዳርጎታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ መዋቅር በልዩ ባህሪያቸው ምክንያት በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዲቆዩ የታሰቡ ተቋማትንም ይፋ አድርጓል፡፡

የአዶላ ወርቅ ልማት ድርጅት፣ የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት፣ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ይገኙበታል፡፡

ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የማዕድን ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህ ተቋም ከማዕድን ውጪ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲያካትት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ተብሎ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተፈጥሮ ሀብቶችን የማልማት ኃላፊነት ነው የተሰጠው፡፡ በተለይ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ የሚለው ስያሜ ድግግሞሽ አስገራሚ ነው እየተባለ ነው፡፡

በዚህ ተቋም ሥር የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ፣ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የገጠር ኢነርጂ ልማት ማስፋፊያ ማዕከል ይገኙበታል፡፡

ከነዳጅ ጋር የተያያዙት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ተጠሪነት ለማዕድን፣ ነዳጅና ጋዝ ሚኒስቴር መሆኑ ቀርቶ አዲስ ለሚቋቋመው የኢትዮጵያ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ምርትና አቅርቦት ኮርፖሬሽን ይሆናል፡፡ ቀሪዎቹ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከሞላ ጐደል በዚያው የሚቀጥሉ ይሆናሉ፡፡               

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -