Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎች ኪንግናምን እየመረመረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኪንግናም የተሰኘውን የደቡብ ኮሪያ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ከማሽነሪዎች ሽያጭ ጋር በተያያዘ እየመረመረው እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ኪንግናም በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ለሚያካሂዳቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የሚሰጡ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በብዛት በጊዜያዊ የጉሙሩክ ቦንድ ወደ አገር አስገብቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ የቦንዱ ቀነ ገደብ ከማብቃቱ በፊት ማሽነሪዎቹንና ተሽከርካሪዎቹን በአገር ውስጥ መሸጥ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ምንጮች ኪንግናም ማሽኖቹን እየሸጠ ያለው ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ አይደለም የሚል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የኪንግናም ኃላፊዎች በበኩላቸው ማሽኖቹን እየሸጡ ያሉት ሕጋዊ አሠራር ተከትለው ተገቢውን የጉምሩክ ቀረጥና ግብር ከፍለው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሕግ ማስከበር ዘርፍ አቶ አለባቸው ንጉሤ፣ ባለሥልጣኑ ጥቆማው እንደደረሰውና በኩባንያው ላይ ምርመራ መጀመሩን ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለኪንግናም መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ባለሥልጣኑ ኪንግናም ባካሄዳቸው ሽያጮች ላይ የጀመረውን ምርመራ እስከሚያጠናቅቅ የኩባንያውን ንብረቶች መሸጥና መለወጥ እንዲያቆም አሳስቧል፡፡

አቶ አለባቸው የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጊዜያዊነት ዋስትና የሚያስገቧቸው የተለያዩ ማሽነሪዎች እንዳሉ፣ ይህ አሠራር በገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅና በገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መመርያዎች የተፈቀደ ሕጋዊ አካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ ችግር የለውም፡፡ በርካታ ድርጅቶችም በዚህ መንገድ እያስገቡ ሕግ በሚፈቅድላቸው መሠረት የሚሠሩ አሉ፡፡ ሥራቸውን ከሠሩ በኋላ አገር ውስጥ እንዲቀሩና እንዲሸጡ የሚፈልጓቸው ካሉ የሚያስፈጽሙበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ መጀመሪያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ይጠይቃሉ፡፡ ባለሥልጣኑ አካሄዶችን ፈትሾ የሚፈቅድበት ወይም የማይፈቅድበት ሁኔታ አለ፡፡ ለዚህም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያስቀመጠው መመርያ አለ፤›› ብለዋል አቶ አለባቸው፡፡

ኩባንያዎች ይህን አሠራር ተከትለው የሚሄዱ ከሆነ ችግር እንደማይኖር የገለጹት አቶ አለባቸው፣ ኪንግናም የተጠቀሱትን አሠራሮች ሳያሟላ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሄዷል የሚል ጥቆማ ለባለሥልጣኑ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼንን ትክክል ነው፣ ትክክል አይደለም፣ ሕግ ጥሰዋል፣ ሕግ አልጣሱም የሚለውን አጣርተን የመጨረሻ ውሳኔ እስከምንሰጥ ድረስ ድርጅቱ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለበት እንዲያቆም ታዟል፡፡ ኩባንያው የሕጉን ቅደም ተከተል አሟልቶ መሄዱን ለማረጋገጥ የጀመርነውን ምርመራ ሳናጠናቅቅ ተሳስቷል፣ አልተሳሳተም፣ ትክክል ነው፣ ትክክል አይደለም ብዬ የምሰጠው መረጃ የለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አለባቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጉዳዩን በመመርመር ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ምርመራው ሲጠናቀቅ ውጤቱ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ያለው መረጃ መጥቷል፡፡ መረጃውን መሠረት አድርገን ሕጉን በተከተለ መንገድ መሄድ አለመሄዱን መርምረን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ጥፋት ካለ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እንዲታረም እናደርጋለን፡፡ ትክክል ከሆነ ደግሞ በትክክል በሕግ የተሰጠውን መብት እንዲጠቀም እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አለባቸው በጉዳዩ ዙሪያ ከኪንግናም ማኔጅመንት ጋር መወያየታቸውንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከውይይታችን ተነስተው በአግባቡ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይኼን ይኼን ቀረጥና ታክስ ከፍለን አገር ውስጥ እንዲቀሩ ይፈቀድልን ብለው አመልክተዋል፡፡ ከውይይታችን በኋላ የሚመለከተው ክፍል ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥ ተላልፏል፡፡ ሕጉ አገር ውስጥ መሸጥ አይከለክልም፡፡ ነገር ግን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ተመሳሳይ ክትትል በሌሎች በርካታ ኩባንያዎች ላይ በመካሄድ ላይ መሆኑን አቶ አለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኩባንያዎቹን ስምና ብዛት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ሌሎችም የሚመጡ ጥቆማዎች አሉ፡፡ እኛም በክትትል የምንደርስባቸው አሉ፡፡ እንደየባህሪው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ለማስተካከል እየሞከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኪንግናም ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻሉ፡፡ የኪንግናም የማቴሪያል ክፍል ኃላፊ ሚስተር ሊ ሚዩንግ ቹል ለሪፖርተር እንደገለጹት ኩባንያቸው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

ኪንግናም ማሽኖቹን የሚሸጠው አስፈላጊውን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ከፍሎ እንደሆነ ሚስተር ሊ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሚስተር ሊ ገለጻ ኪንግናም በመስከረም 2007 ዓ.ም. ብቻ 56 ሚሊዮን ብር የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ከፍሏል፡፡ ‹‹የጉምሩክ ቀረጥ የምንከፍለው ለቃሊቲ ጉምሩክ ነው፡፡ ሙሉ መረጃ ይጠይቁናል፣ አስፈላጊውን መረጃ ከሰጠን በኋላ ቀረጥና ታክስ እንከፍላለን፡፡ ከዚያም የመልቀቂያ ትዕዛዝ እናገኛለን፡፡ ማሽኖቹ በሕጋዊ መንገድ መሸጣቸውን የሚያስረዱ ትክክለኛ ሰነዶች አሉን፤›› ያሉት ሚስተር ሊ፣ ኪንግናም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን እንደሆነ፣ የአገሪቱን ሕግ እንደሚያውቅና እንደሚያከብር፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ ኩባንያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ሊ ከአቶ አለባቸው ጋር ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸው፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ያለመረዳት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልና ይህንንም በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የምርመራው ውጤት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይገለጽላችኋል እንደተባሉ፣ ይህ ከተነገራቸው ሁለት ሳምንት ማለፉንና ውጤቱን በትዕግሥት እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ሊ ያገለገሉትን ማሽኖች እንዲሸጡ በኪንግናም ዋና መሥሪያ ቤትና በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ፈቃድ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ ሽያጩ እንዲካሄድ ማፅደቃቸውን የሚናገሩት ሚስተር ሊ፣ ኩባንያቸው የጉምሩክ ዋስትና ጊዜ ሳያልቅ ማሽኖቹን ለመሸጥ ጥረት ላይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ኪንግናም ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 18 ዓመታት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፣ ኩባንያቸው የገጠመውን ችግር ፈትቶ በመንገድ ግንባታ ሥራ የመቀጠል ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እናሸንፋለን፡፡ በዚህ አገር የመሠረተ ልማት ግንባታ የምናደርገው ተሳትፎ ይቀጥላል፡፡ እዚህ አገር ይሳካልናል፤›› ብለዋል፡፡ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቅርቡ በጎ ምላሽ እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኪንግናም ኢትዮጵያ ውስጥ 1,300 ያህል ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ ኩባንያው 45 ያህል ማሽኖች መሸጡንና ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ለመንግሥት መክፈሉን አስታውቋል፡፡

ኪንግናም በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እ.ኤ.አ. በ1997 ሲሆን፣ የመጀመሪያ ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያና ማቆሚያ ግንባታ ነበር፡፡ በመቀጠል የሞጆ-አዋሽ-ገዋኔ፣ ሂርና-ቁልቢ፣ አዘዞ-ገነቴ-መተማ፣ ሆሳህና-ሶዶ፣ አላባ-ሁምቦ፣ አፖስቶ-ኢርባሙዳና ጂማ-ቦንጋ ሚዛን መንገዶችን ገንብቷል፡፡ በአጠቃላይ ኩባንያው 1,500 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 12 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ የጅማ-ቦንጋ መንገድ ፕሮጀክትን በቅርቡ አጠናቆ ያስረክባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የጂማ-ቦንጋ መንገድ 97 በመቶ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች