Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የወንድማሞቹ ስጦታ

አቶ ሙላት ፎጌ የአማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው በማምረት፣ በትራንስፖርትና በወጪና ገቢ፣ እንዲሁም በሌሎች የንግድ ዘርፎች ላይ የተሠማራ ድርጅት ነው፡፡ ድርጀቱም በቤተሰብ የተቋቋመ ነው፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ድርጅታቸው ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ›› የእንቦጭ አረም መከላከያ ማሽን ከቻይና ከሁለት ሚሊዮን ብር በመግዛት አገር ውስጥ አስገብቷል፡፡ ማሽኑ የእንቦጭ አረምን በመከላከል ረገድ የተሳካ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ይወሳል፡፡ በዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዘመኑ ተናኘ ከአቶ ሙላት ፎጌ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት አቶ ሙላት ፎጌ ማን ናቸው? የት ተወለዱ? የት ተማሩ?

አቶ ሙላት፡- የተወለድኩት ጎንደር ውስጥ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት በእስቴ መካነ ኢየሱስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እስከ አሥራ አንደኛ ክፍል ደብረ ታቦር ነው የተማርኩት፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ደግሞ በባህር ዳር ጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደ ንግዱ ዓለም እንዴት ገቡ?

አቶ ሙላት፡- ወደ ንግዱ የገባነው ወላጆቻችን ጎንደር ሆነው ንግድና እርሻን ቀላቅለው ይሠሩ ነበር፡፡ እኛም እየተማርን ራሱ ከወላጆቻችን ጋር ሆነን ተጨማሪ የንግድ ሥራ እንሠራ ነበር፡፡ ዝንባሌያችን በሙሉ ንግድ ላይ ነበር፡፡ ከቤተሰቦቻችን የንግድ ልምድ ወስደናል፡፡ ተማሪም ነን፡፡ ነጋዴም ነበርን፡፡ አንዳንዴ ተማሪም ሆነን ወደ አዲስ አበባ ተልከን እንነግድ ነበር፡፡ ተማሪ ሆነን አስመራ ድረስ ሄደን ሥራ ሠርተን የተመለስንበት ጊዜም ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የንግድ ሥራው ልምድ ከዚያ የመጣ ነው፡፡ ባለን ልምድ ወደ ግላችን ሥራ ለመግባት የፈጀብን ጊዜ የለም፡፡ ቀሎናል ማለት ነው፡፡ ያ ልምድ ለአሁኑ ሥራችን ረድቶናል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህም ሳቢያ አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በወንድማማቾች የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጣና ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል ከቻይና የእንቦጭ አረም መከላከያ ማሽን ገዝታችኋል፡፡ ችግሩ መኖሩን በቅድሚያ እንዴት ሰማችሁ? እንዴትስ ወደ ማሽን ግዥ ልትገቡ ቻላችሁ?

አቶ ሙላት፡- በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን አረም የሰማነው እንደማንኛውም ሰው በሚዲያ ነው፡፡ ተደጋግሞ ችግሩ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በጋዜጣና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲነገር ሰማን፡፡ ለሐይቁ አደገኛ መሆኑን ተረዳን፡፡ በተለይ ወንድሜ አቶ ፍቅሬ ፎጌ ወደ ቻይና ብዙ ጊዜ ይመላለሳል፡፡ ችግሩን ሲሰማ በጣም ተጨነቀና ማሽኑን ማፈላለግ ጀመረ፡፡ በኢንተርኔት፣ በሰውና ቻይና ባሉ ደንበኞቻችን አማካይነት ሲያፈላልግ ቆየ፡፡ ከዚያ ማሽኑ ቻይና እንደሚገኝ አወቅን፡፡ ማሽኑን እንዳገኘን የክልሉ መንግሥት መግዛት ይችል እንደሆነ ሐሳቡን አቀረብን፡፡ ሐሳቡን ስናቀርብላቸው ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ግን ስናየው ጊዜው የሚጓተት ሆኖ አገኘነው፡፡ ከዚህ አኳያ ይህንን ማሽን እኛ ማቅረብ አለብን ብለን ወሰንን፡፡ የክልሉ ባለሥልጣናት ደስ አላቸው፡፡ በዚህ መሠረት እኛ ማሽኑን ልናዝዝ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሳቡን ስናቀርብላቸው ሊጓተት ይችላል የሚል ሥጋት ገባን ብለውኛል፡፡ እንደዚህ ልታስቡ የቻላችሁት ከምን አኳያ ነው? ከእነሱ ጋርስ የነበራችሁ ውይይት ምንድን ነበር?

አቶ ሙላት፡- እኛ ማሽን እንደሚኖር እንኳ አናውቅም ነበር፡፡ ግን ፍቅሬ ማሽኑን አገኘ፡፡ ማሽኑ ውጤታማ ነው ብለን ለክልሉ አመራሮችና ነገርናቸው፣ የመንግሥት ገንዘብ ዝም ብሎ እንደማይወጣና ይጠና በማለት ጊዜ ይወስዳል ብለን በመሥጋታችን እኛ ለመግዛት ወሰንን፡

ሪፖርተር፡- ከማን ጋር ነበር ውይይት ስታደርጉ የነበረው?

አቶ ሙላት፡- ከንግድ ቢሮ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ እንዲሁም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ተነጋግረናል፡፡ ሐሳቡን ወዲያውኑ እንዳቀረብን ደስ አላቸው፡፡ እነሱ ቢሆኑ ጥናት ምናምን ሲባል ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ኃላፊነቱን እኛ መውሰድ አለብን ብለን ነው ያሰብነው፡፡ እነሱም ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ገንዘብ ይገዛ ከተባለ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ያ ጥናት እስከሚጠና ደግሞ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የት ቦታ ነው የተሠራው? ማሽኑ እንዴት ነው? ሲባል የሆነ ጊዜ እንደሚወስድ ገመትን፡፡ በእርግጥ እነሱ ይቆያል አላሉንም፡፡ እኛ ገዝተን ብናቀርብ የሚል ሐሳብ አቀረብንላቸው፡፡ ፈቃደኛ ሆኑ፡፡ የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ በጣም ተባባሪ ናቸው፡፡ ደብዳቤ እየጻፉልን፣ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንድናገኝ አድርገዋል፡፡ በርካታ ሥራዎችን አገዙን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ፣ ገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣንና ሌሎች የፌዴራል ተቋማት እንዲተባበሩን አግዘውናል፡፡ ንግድ መርከብ ለምሳሌ በነፃ ነው ያመጣልን፡፡ የትራንስፖርት አላስከፈለንም፡፡ ገቢዎች ደግሞ ማሽኑ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ አግዘውናል፡፡   

ሪፖርተር፡- ማሽኑ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶበታል ተብሏልና በትክክል ምን ያህል ብር ወጪ አድርጋችሁበታል? ቻይና ካለው አምራች ኩባንያ ጀምሮ ጣና ሐይቅ ላይ አርፎ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል?

አቶ ሙላት፡- ማሽኑ የተገዛበት ገንዘብ፣ ከሃምሳ ሁለት ሺሕ ዶላር በላይ ነው፡፡ አንድ ባለሙያ ሙሉ ወጪ ሸፍነን ከቻይና አምጥተናል፡፡ ማሽኑ ሲመጣ የእኛ ተሽከርካሪዎች ጎርጎራ ድረስ ሄደዋል፡፡ በአጠቃላይ ለመከላከል ሲባል ማሽኑን ከቻይና አምጥተን ሥራ እስኪጀመር ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፡፡ በድምሩ ሁለት ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪ አድርገናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከቻይና ማሽኑን ብቻ ሳይሆን ባለሙያም እንዳመጣችሁ ተናግረዋል፡፡ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ያብራሩልን፡፡ ለምንድነው ቻይናዊ ባለሙያ ያመጣችሁት? ኢትዮጵያውያን ማሽኑን ማንቀሳቀስ አይችሉም ማለት ነው?

አቶ ሙላት፡- ባለሙያው ሻጩ ድርጅት የመደበው ባለሙያ ነው፡፡ እኛ ትራንስፖርቱንና የሎጂስቲክስ ወጪዎችን አውጥተን አመጣነው፡፡ ለአንድ ወር ጎርጎራ ወደብ ላይ ማሽኑን ሲሞክር ቆየ፡፡

ሪፖርተር፡- ማሽኑ በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ነው? አረሙን ሙሉ በሙሉ በዚህ ማሽን ማስወገድ ይቻላል?

አቶ ሙላት፡- በጣም ውጤታማ ነው፡፡ ነገር ግን በክልሉ መንግሥትም ሊቀርቡ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ማሽኑ አረሙን ከነቀለ በኋላ ዳር ላይ ነው እያመጣ የሚጥለው፡፡ የሚጣለው ቆሻሻ ወዲያውኑ ወደ ሩቅ ቦታ እየተጣለ እንዲደርቅና ከዚያም በኋላ በማቃጠል ወይም በሌላ መንገድ መወገድ እንዳለበት ሐሳብ አቅርበንላቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተወገደ ክረምት ሲመጣና ውኃው ሲሞላ እንደገና ያቆጠቁጣል፡፡ ይህን የተቀናጀ ሥራ ለክልል በሐሳብ ደረጃ አቅርበናል፡፡ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ መኪናዎች ተዘጋጅተው የወጣው ቆሻሻ ራቅ ወዳለ ቦታ መጣል አለበት፡፡ አረሙ ውኃ ሲያጣ በቀላሉ ነው የሚደርቀው፡፡

ሪፖርተር፡- እነሱ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጧችሁ?

አቶ ሙላት፡- የክልሉ ፕሬዚዳንት ፈቃደኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ እንዲያውም እሳቸው በርክክቡ ጊዜ ተፈጽሞ መታየት አለበት ብለው ነበር፡፡ በሥራ ምክንያት በወቅቱ አልነበሩም፡፡ ይህ የእንቦጭ መከላከያ ማሽን ብቻ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ተጨማሪ ማሽኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ከማሽኑ ውጪም ሌሎች ጥናቶች መደረግ አለባቸው፡፡ የጣና ችግር በዚህ ማሽን ብቻ ይወገዳል የሚል እምነት የለንም፡፡   

ሪፖርተር፡- ሪፖርተር ከአማራ ክልል ኃላፊዎች ባገኘው መረጃ መሠረት በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል ከአሥር ያላነሱ ተመሳሳይ ማሽኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ እናንተ ዓይነት የግል ድርጅቶች እንቦጭን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምን ይደረግ ይላሉ?

አቶ ሙላት፡- ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ እኛ ይህን ሐሳብ ስንጀምር ለማሳየት ያህል ነው እንጂ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ድጋፍ የሚያደርጉ ይኖራሉ፡፡ ከእኛ የበለጠ የተሻለ አድርገው ሊረዱ የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይኖራሉ፡፡ መረጃው ስለሌላቸው እንጂ ብዙ ሰዎች የበለጠ አድርገው ይህ ችግር ተቀርፎ እንደምናይ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ማሽኑን ለማስመጣት ካቀዳችሁ ጀምሮ ጣና ሐይቅ ላይ እስኪያርፍ ድረስ ችግር ገጥሟችሁ ነበር?

አቶ ሙላት፡- ብዙ የገጠመን ችግር የለም፡፡ መጀመርያ ማሽኑን ለማግኘት ተቸግረን ነበር፡፡ ከስሙ ራሱ የእኛ አገር አጠራርና ውጭ ላይ ያለው አጠራር የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ ከስሙ ጀምሮ ችግር ነበር፡፡ ስሙን ለመጠየቅ ራሱ ችግር ነበር፡፡ ከተገኘ በኋላ ብዙም የገጠመን ችግር የለም፡፡ ማሽኑ ከተገኘ በኋላ ወንድሜ በአካል ቻይና ሄዶ አየው፡፡ በትክክል እንደሚሠራ አረጋገጠ፡፡ ምክንያቱም ለሕዝብ ነግረን ውጤታማ ካልሆነ ከባድ ነው፡፡ ለእኛ ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ለሕዝብ ነግረህ ውጤት ሳይሰጥ ቢቀር ያሳፍራል፡፡  ያ እንዳይሆን ቻይና ድረስ ሄዶ ውጤታማ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ነው የተገዛው፡፡ ስለዚህ የከፋ ችግር አላጋጠመንም፡፡ የክልሉ አመራሮች ቀና ትብብር አድርገውልናል፡፡   

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ እንደዚህ ዓይነት ማኅበራዊ ግዴታዎችን ከመወጣት አኳያ ምን ሠራ?

አቶ ሙላት፡- እንደዚህ ማሽን የጎላ አይምሰል እንጂ በተቻለ መጠን በየጊዜው ድርጅታችን የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ያደርጋል፡፡ የጤና ጣቢያ ሕንፃ አሠርተን የሰጠንበት ጊዜ አለ፡፡ ትምህርት ቤት ሠርተናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ከማቋቋም አኳያ የስምንት አባወራዎች ቤት ለመሥራት ቃል ገብተን እየሠራን ነው፡፡ ከአንድ ወይም ሁለት ዓመት በፊት አዳማ አካባቢ በጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ወገኖቻችን ከሦስት መቶ በላይ ፍራሽ ሰጥተናል፡፡ ብዘረዝረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ውኃ ጉድጓድ እያስቆፈርን ነው፡፡ በውኃ የተቸገረ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ የምንችለውን እያደረግን ነው፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ እየሠራንም ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ግዴታችን ስለሆነ ይህንን አደረግንም አንልም፡፡ ወደፊትም ባለንና በምንችለው መጠን ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...