Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባን ጠቅላላ የምርት አቅርቦት 176 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በአምስት ዓመት በ20/80 ፕሮግራም 250 ሺሕ ቤቶች ይገነባሉ ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ በከተማው የሚገኙ የኢኮኖሚ ተዋናዮች አጠቃላይ የማምረት አቅም 176 ቢሊዮን ብር ይደርሳል አለ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ረቂቅ ሰነድ፣ በ2007 ዓ.ም. የከተማው አጠቃላይ ምርት 90.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ረቂቅ ሰነዱ ከአምስት ዓመት በኋላ ለእጥፍ ትንሽ የቀረውን 176 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ዕቅድ ለማሳካት በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም ለማኑፋክቸሪንግ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑንና በዘርፉ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት የወጪ ንግድ በማሳደግ፣ የገቢ ንግድ መተካት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአገልግሎት ዘርፍም እንዲሁ ቱሪዝም በተለይም ከሆቴል፣ ከትራንስፖርትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ መታቀዱን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 15.4 በመቶ በ2012 ዓ.ም. ወደ 18.12 በመቶ ከጠቅላላው የከተማ ምርት ድርሻ እንደሚኖረው ትንበያ ሰፍሯል፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ድርሻ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 37 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ 40.2 በመቶ እንደሚደርስ ተተንብይዋል፡፡ ይህ የሚሆነውም የኢንዱስትሪ ዘርፍ በአማካይ 15 በመቶ ዕድገት ሲያሳይ መሆኑን በረቂቅ ሰነዱ ተገልጿል፡፡

የአገልግሎት ዘርፍ ድርሻ በዕቅድ ዘመኑ ከ65.9 በመቶ በ2012 ዓ.ም. ወደ 59.04 በመቶ ዝቅ የሚል ቢሆንም፣ ከጠቅላላው የከተማ ምርት ያለውን ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ የአምስት ዓመት ዕቅድ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዕቅድ ዘመኑ ከሚያካሂዳቸው በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል፣ የመኖርያ ቤት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በአዲስ አበባ ከ900 ሺሕ በላይ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ አካሂደው ዕድላቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

አስተዳደሩ በረቂቅ ሰነዱ ላይ እንደገለጸው፣ በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ያሉትን 50 ሺሕ ቤቶች ጨምሮ፣ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 250 ሺሕ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ ነድፏል፡፡ ከተገነቡት ቤቶችም 190,000 ቤቶችን ለማስተላለፍ አቅዷል፡፡

በ40/60 ፕሮግራም በመገንባት ላይ ያሉትን 22,678 ቤቶች ግንባታ ለማጠናቀቅና 62,322 አዲስ ቤቶችን ለመገንባት፣ እንዲሁም ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ መታቀዱን ሰነዱ አስታውቋል፡፡

መሀል ከተማ እየተካሄደ ያለውን የመልሶ ማልማት ዕቅድ እንዲጓተት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ለተነሺዎች ቤት ማቅረብ አለመቻል ይገኝበታል፡፡

በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አምስት ሺሕ የኪራይ ቤቶችን በመገንባት ይህንን ችግር ለመፍታት ታቅዷል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ 50 ሺሕ የሚሆኑ ነዋሪዎች በልማት ምክንያት እንደሚነሱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለተነሺዎቹ መኖርያ ቤት ለማቅረብ የተለያዩ አማራጮች ይዘጋጃሉ ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ በቅርቡ በተለያዩ መድረኮች ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ በከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አማካይነት የተዘጋጀ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች