የቀድሞው ሬዲዮ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ፣ በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተክሉ ታቦር ሕይወት ተራኪ መጽሐፋቸውን አሳተሙ፡፡
‹‹ተክሉ ታቦር በተክሉ ታቦር›› በሚል ርዕስ የቀረበው መጽሐፍ የጋዜጠኞችን ኅብረተሰብ ወቅታዊ ሕይወት ፈንጣቂ የሆነ፣ የራስን ሕይወት ተራኪ መጽሐፍ መሆኑ በማስታወቂያው ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ ዓርብ መጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በ8፡30 ሰዓት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቅም ታውቋል፡፡
አቶ ተክሉ በቀድሞው ሬዲዮ ኢትዮጵያ ለ10 ዓመት፣ ከ1967 ዓ.ም. በኋላ ለዘጠኝ ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሠርተዋል፡፡ በተለይም ‹‹የውይይት መድረክ›› በተሰኘው ፕሮግራማቸው ይታወቃሉ፡፡ ከሁለቱ የሚዲያ ተቋማት በኋላ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
*****
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዐውደ ርዕይ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው የታሪካዊ ጉዞ ዐውደ ርዕይ ሐሙስ መጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሙዚየም ይከፈታል፡፡ ዐውደ ርዕዩ ለተከታታይ 15 ቀናት ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ባንኩ አስታውቋል፡፡