Sunday, December 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በድርቅ ለተጎዱትም ሆነ ለከተማ ድህነት ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል!

ካለፈው ዓመት የበልግ ወቅት ጀምሮ በተከሰተው የኤልኒኖ ተፅዕኖ ምክንያት ዝናብ በመስተጓጎሉ፣ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ በከተሞች ውስጥ በሚታየው ጥልቅ የሆነ ድህነት ምክንያትም በርካቶች የምግብ እጥረት አጋጥሞአቸዋል፡፡ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች በተለይ በድርቁ ምክንያት የደረሰውን ችግር ለመቋቋም ጥረት እያደረጉ መሆኑን ቢገልጹም፣ አሁንም ችግሩ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ መንግሥት በከተሞች ውስጥ የሚታየውን ችግር እንዲሁ መላ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ ለዚህም ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ቀደም ሲል አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 4.5 ሚሊዮን ዜጎች በተጨማሪ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕርዳታ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት እነዚህ ተጨማሪ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት የሚገባቸው ተማሪዎች ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው መሠረታዊ የሚባለውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው፣ እንኳን ትምህርት ቤት ሊልኩዋቸው ለዕርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞችም ሆነ በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ጽኑ የምግብ እጥረቶች አሉ፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ያሻል፡፡

አሁን ይፋ በተደረገው ሪፖርት መሠረት በአጠቃላይ 7.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ የአስቸኳይ ምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ በትንሹ 450 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ገንዘብ ለማግኘት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የለጋሽ አገሮች አምባሳደሮች ገለጻ ተደርጎላቸው፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተዋጽኦቸውን  እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በጥሪውም መሠረት በፍጥነት በሚወሰደው ዕርምጃ ተጨማሪ ወጪን ማዳን እንደሚቻልና ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ መታደግ ይቻላል ተብሏል፡፡ መንግሥትም ይህንን የሰብዓዊ ድርጅቶች ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ ማስተባበር አለበት፡፡

አሁን ያለንበት አስቸጋሪ ጊዜ በበልግ ወቅት ይገኝ የነበረውን ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚገመት የግብርና ምርት በማጣት ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ በደካማ የዝናብ ሥርጭት ምክንያት ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚገመተው የክረምት የግብርና ምርት መጠን በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ችግር በመፍጠር በርካታ ቁጥር ያላቸው የአገሪቱን ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያጋልጣል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በአገሪቱ የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ያደረሱትን ጥፋት ስናስብ፣ አሁን የተጠናከረ ምላሽ የመስጠት ጥረትን አስፈላጊነት እንረዳለን፡፡ በፍጥነት፡፡

በገጠር ለድርቅ የተጋለጡ በርካታ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችና እንስሳት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎችን ይፈልጋሉ፡፡ የውኃና የመድኃኒት አቅርቦትም እንዲሁ፡፡ መንግሥት ይህንን አሳሳቢ ወቅት ሙሉ ጊዜና ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ መዘግየቶችና ችላ ባይነት የተነሳ የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ቢቀጠፍ ፀፀቱ የአገር ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ የድርቅ አደጋ ያንዣበባቸው ሥፍራዎችን በተቀናጀና በፈጣን እንቅስቃሴ መታደግ የወቅቱ ጥሪ ነው፡፡ መንግሥታዊም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ርብርብ ያድርጉ፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውንና ትኩረታቸውን ችግሩን ለመቅረፍ ያውሉ፡፡

በሌላ በኩል በከተሞች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመታየት ላይ ያለው ለምግብ እጥረት መጋለጥ ሌላው ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ በከተሞች ውስጥ የሚታየው የሥራ አጥነትና የድህነት መጠን በተወሰነ ደረጃ መሻሻል ቢታይበትም፣ ብዙዎቹ በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በመንግሥታዊ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በምግብ እጥረት የተነሳ ሲወድቁ ይስተዋላሉ፡፡ በግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ግለሰቦች አማካይነት ቁርስ ወይም ምሳ የሚመፀውቱ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ጥረት ደግሞ ዘላቂ ባለመሆኑ መንግሥት ይህንን ችግር በፍጥነት አስጠንቶ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ የከተማው ድህነት አንዱ ገጽታ ልጆችን መመገብ፣ ዩኒፎርም ማልበስና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ አለመቻል ነው፡፡ በነጋ በጠባ በሚዲያዎች ይህንን ችግር ለመቅረፍ በግለሰቦች የሚደረገው ጥረት በስፋት ይነገራል፡፡ ነገር ግን አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

በከተሞች ውስጥ የሚታየው መጠነ ሰፊ ልመና በራሱ የሚናገረው አለው፡፡ በተለይ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱ ብዛት ያላቸው ዜጎች ልመና ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ በዋና ዋና ጎዳናዎች፣ በቤተ ዕምነቶች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎችና በተለያዩ ቦታዎች ለልመና የሚወጡ ዜጎች ቁጥር መበራከት የድህነት መጠኑን ማሳያ ነው፡፡  ልመናን እንደ መደበኛ ሥራ ተያይዘው ሀብት የሚያፈሩበት ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ ግን የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ምንዱባን ናቸው፡፡ አገሪቱ ከባዶ ተነስታ መጠነኛ መንጠራራት እያሳየችበት ባለችበት በዚህ ጊዜ ከተሞች በልመና ሠራዊት መወረራቸው አሥጊ ነው፡፡ በከተማ ውስጥ ከእጅ ወደ አፍ የሚኖሩ ዜጎች ተስፋ በመቁረጥ ልመናን አማራጭ እያደረጉ ናቸው፡፡ ይህም ያስፈራል፡፡ የመንግሥትንና የሚመለከታቸውን አካላት ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡

በአዲስ አበባና ትልልቅ በሚባሉ ከተሞች ጎዳናዎች ላይ የሴተኛ አዳሪዎች መበራከት ለከተማ ድህነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በምሽት እንጀራቸውን ፍለጋ ከተሞችን የሚያጥለቀልቁ ዜጎች፣ ከጤናም ሆነ ከሞራል አንፃር ታይቶ መፍትሔ ካልተበጀላቸው ጉዳቱ የአገር ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ የሆነ ኑሮ ወጥተው አምራች ኃይል እንዲሆኑ ካልተደረገ በስተቀር፣ ችግሩ የእያንዳንዱን ዜጋ ቤት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማንኳኳቱ አይቀርም፡፡ የጎዳና ላይ ሴተኛ አዳሪነት ለወንጀልና ለመሳሰሉ ሕገወጥ ተግባራት ሽፋን ከመስጠቱም በላይ፣ የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ያናጋል፡፡ በድህነት ምክንያት ጎዳና ላይ ወጥተው አካላቸውን የሚቸረችሩ ዜጎችን መንግሥትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሊደርሱላቸው ይገባል፡፡ ዘለቄታዊ መፍትሔም ይሻሉ፡፡ ይህም የተለየ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

ከድህነት ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ሱሶች መጋለጥ፣ ሕገወጥ መሆንና ተስፋ አስቆራጭ ኑሮ የመምራት አሳዛኝ ዕድል የሚገጥማቸው ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳትና መሰል መሠረታዊ አቅርቦቶችን ስለማያገኙ መማር አይችሉም፡፡ በቀላሉም ለደባል ሱሶች ይጋለጣሉ፡፡ ሱሶቹን ለማርካት ሲሉም ወንጀል ይፈጽማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ለኅብረተሰቡ ህልውና አደጋ ስለሚደቅኑም፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት ያዳግታቸዋል፡፡ ሕገወጥነት በሰፈነበት የሰው ልጅ ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ነገር ግን ወጣቶቹ ከእንዲህ ዓይነቱ ተስፋ አስቆራጭና የዘቀጠ ሕይወት ውስጥ እንዲወጡ ሲደረግ፣ የተረጋጋ ማኅበረሰብ ይኖራል፡፡ ድህነቱ በተቀናጀ አኳኋን ሲቀረፍ ሰላም ይሰፍናል፡፡ ስደት ይቆማል፡፡ እሮሮ አይኖርም፡፡ ይኼም የተለየ ትኩረት ይሰጠው፡፡ በአነስተኛ ገቢ ኑሮን መምራት ያቃታቸው ዜጎች ጉዳይም ይታሰብበት፡፡

በአጠቃላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የተጠናከረና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር መስፈን አለበት፡፡ በዘገምተኛነትና በችላ ባይነት ምክንያት አጣዳፊ ጉዳዮች ሲጓተቱ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስከፍላሉ፡፡ በተለይ እጅግ ዘገምተኛ የሆነው የመንግሥት ቢሮክራሲ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ካልተደረገበት አደጋው ከሚታሰበው በላይ ይሆናል፡፡ ችግሮችን መሸፋፈንና ራስን ማታለል አገሪቱን የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ይከታታል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳሳቢ ችግሮች ሲያጋጥሙ የአደጋ ዝግጁነቱና የመከላከሉ ብቃት በተቻለ መጠን በአሳማኝ ሁኔታ ይታይ፡፡ ምላሽ የመስጠቱ ብቃት ይመዘን፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የሚመለከታቸውን አካላት መንግሥት ያንቀሳቅስ፡፡ በድርቅ የተጎዱትም ሆነ በከተማ ውስጥ የሚታየው ድህነት ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሹ መንግሥት ትኩረት ይስጥ! በፍጥነት ይንቀሳቀስ! ፈጣን ምላሽ ይስጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...